በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ቡራኬ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ተከናወነ
ግንቦት ፲፭ ቀን ፳፻፲ወ፰ ዓ.ም
በቡራኬ ቤተክርስቲያን መርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን ድርጅት የበላይ ሓላፊ የሰሜንና ምሥራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ጨምሮ ሌሎችም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል።
በተጨማሪ የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎች ፤ መልአከ ገነት መምህር ኤርምያስ ውብሸት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ፤ አገልጋይ ካህናትና ፤ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣ ዘማሪያንና በርካታ ምእመናን በቡራኬ ቤተክርስቲያን በዓሉ ላይ ታድመዋል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት “ለበርካታ ዓመታት ደክማችሁ ይህንን ሕንጻ ቤተክርስቲያን በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ በማስመረቃችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ” ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ እንጦንስ የምዕራብ ሐረርጌ ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው ቤተመቅደሱ እውን እንዲሆን የደከሙ ምእመናን ፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት ፣ የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴዎች በሰማይም በምድርም ትልቅ ክብር የሚያገኙበትን ቅዱስ ሥራ ማከናወናቸውን ገልጸዋል።
“ዐይኖቸና ልቤ በዚህ ሥፍራ ለዘለዓለም ይሆናሉ” የሚለውን ቅዱሱን የእግዚአብሔር ቃል መነሻ አድርገው ፤ ለምርቃት የበቃው የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ሥጋውን የምንበላበት ደሙን የምንጠጣበት ፣ የካህናት ጸሎት የሚያርግበት ነውና “እንኳን ደስ አላችሁ” ያሉት ደግሞ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ቡራኬ ላይ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን ድርጅት የበላይ ሓላፊ የሰሜንና ምሥራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ትምህርት “ቤተመቅደሱ እግዚአብሔር የሚመሰገንበት ፣ ካህናት የሚዘምሩበት ፣ ምእመናን የሚጸልዩበት ፣ ሕጻናት የሚቆርቡበት ፣ አረጋዊያን የሚማፀኑበት ፣ በመጨረሻም ደግሞ የኦርቶዶክሳዊያን ዘላቂ ማረፊያ ነው” ብለዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሲሰጡ ሸገር ከተማ በሀገረ ስብከት ደረጃ ተቋቁሞ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ መመራት ከጀመረ ወዲህ እየተስተዋለ ያለው ለውጥ እንዳስደሰታቸው ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ በመርሐ ግብሩ ይህ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ለበርካታ ዓመታት ከግንባታ ውጭ ሁኖ መቆየቱን በማስተዋል በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ መመሪያ ሰጥተው ዛሬ ግንቦት 15 ቀን 2018 ዓ.ም ለምርቃት እንዲበቃ ላደረጉት ለብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ምስጋና ቀርቧል።
በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንፃ ቤተክርስቲያን ጥር 29 ቀን 2002 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንት፣ የዓለም የሰላም አምባሳደር የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለት ግንባታው መጀመሩ ይታወቃል።©Eotc.tv.