የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም 76ኛ ዓመት ቅዳሴ ቤት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በድምቀት ተከበሮ ዋለ

ሚያዝያ 27 ቀን 2018 ዓ.ም
በየዓመቱ ሚያዚያ 27 ቀን በዓመት እንድ ግዜ ብቻ ታቦተ ሕጉ ወጥቶ በአውደ ምሕረት ምዕመናን የሚባርክበት ዕለት እና የኢትዮጵያ የነጻነት በዓል በምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም በድምቀት ተከብሮ ውሏል ።
በበዓሉ ላይም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የመንበረ ፓትርያርክ ዋና ስራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም የበላይ ኃላፊ ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ የራያ አላማጣ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የማኅበራት ማደራጃ የቤተ መዛግብት ወመጻሕፍት መመሪያ ኃላፊ ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣የመንበረ ፓትርያሪክ የመመሪያ የሥራ ኃላፊዎች ፣ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ባቱ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ ፣ ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ የማኅበራዊ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ ፣ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሴ የአዲስ አበባ ዋና ስራ አስኪያጅ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመምሪያ የሥራ ኃላፊዎች ፣ መጋቤ ኅሩያን አባ ኤልያስ በልሁ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ዋና አስተዳዳሪ ፣ የገዳማት አድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ፣ በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል።
ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ታቦት ከኢየሩሳሌም ዴር ሱልጣን ገዳም ሀገር በጠላት ወረራ ውስጥ በሆነችበት ጊዜ በንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ጥያቄ ለጸሎት ማድረሻ እና ለመማጸኛ ከጥቂት አገልጋዮችጋር በ 1929 ዓ ም ተጓዘ ።
በእንግሊዝ ለንደን ባት በተባለ ቦታ አርፎ እስከ1933 አገልግሎት እየሰጠ ቆይቷል በቀድሞ ስሙ ገነተ ልዑል ቤተ መንግስት የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ2 ዓመታት ከቆየ በኃላ በቀድሞ ስሙ ቤተ ሳይዳ ወይም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሆስፒታል የአሁኑ የካቲት 12 ሆስፒታል ማረፊያ ተዘጋጅቶለት ከቆየ በኃላ ሚያዚያ 27 1942 ዓ.ም ወደ አሁኑ ያለበት ስፍራ በመምጣት በገዳምነት እያገለገለ ይገኛል።
በዚህ ቦታም ምስካየ ኅዙናን ተብሎ የተሰየመው በንጉሡ ሲሆን በቀድሞው ቤተ ሳይዳ ሆስፒታል በነበረበት ወቅት ነው የኃዘንተኞች ሁሉ መፅናኛ በመሆኑ ስያሜውን አግኝቷል ፣ ዴር ሱልጣን መድኃኔ ዓለም በኢየሩሳሌም በንጉሳውያን ገዳም በነበረበት ነው።
ስደተኛው መድኃኔ ዓለም መባሉ ደግሞ ኢትዮጵያ ነፃነቷን እስክታገኝ ለንጉሡና ለሰራዊቱ መፅናኛ በመሆን በስደት ከንጉሱ ጋር ከሀገር ሀገር መሰደድ ነው ።
በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ የድል ቀን እና የምስካ የኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቅዳሴ ቤት 76ኛ ዓመት በድምቀት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በበዓሉ የታደሙትንብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና የክብር እንግዶች እንዲሁም ምዕመናንን የእንኳን አደረሳችሁ በማለት የበዓሉን የአከባበር ሁኔታ እና የታቦቱን ታሪካ የገለፁ ሲሆን በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የስዊድን ግሪክ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ትምህርተ ወንጌል ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ በመስጠት የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።
©ም/ስ/ኀ/ዙ/መ/ገዳም ሚዲያ፤

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ለምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም የ76ኛ ዓመት ቅዳሴ ቤት እና በጀግኖች አባቶቻችን ለተገኘው 85ኛው የኢትዮጵያ የድል በዓል ያስተላለፉት መልዕክት

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን — በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን
አሰሮ ለሰይጣን — አግአዞ ለአዳም
ሰላም — እምይእዜሰ
ኮነ — ፍሥሐ ወሰላም
​”ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር”
“ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ” መዝ. 68፡31
• ​ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤
• ​የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመመሪያ ኃላፊዎች፤
• ​የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የመመሪያ ኃላፊዎች፤
• ​ክቡራን የገዳሙ አስተዳደር ቦርድ አባላት፤
• ​የገዳማት እና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፤
• ​ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና የገዳሙ አበው መነኮሳት አኃው ዲያቆናት እንዲሁም የገዳሙ ተቋማት ልዩ ልዩ ሠራተኞች፤
• ​የተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት፤
• ​ከሩቅም ከቅርብም የመጣችሁ የመድኃኔዓለም ወዳጆች ምዕመናንና ምዕመናት፤
• ​እንዲሁም ሕፃናት በቅድሚያ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ።
​በድጋሚ ዛሬ ለምናከብረው ለምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም የ76ኛ ዓመት ቅዳሴ ቤት እና በጀግኖች አባቶቻችን ለተገኘው 85ኛው የኢትዮጵያ የድል በዓል እንኳን አደረሳችሁ።
• ​ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
• ​ክቡራንና ክቡራት የበዓሉ ተካፋዮች
​በዛሬው ዕለት የምናከብረው በዓል ሁለት መልክ ያለው ድርብ በዓል ነው።
​አንደኛው በዚህ ታላቅ ገዳም የጌታችንና የአምላካችን የመድኃኔ ዓለምን ታቦተ ሕግ ከመንበረ ክብሩ አውጥተን ቅዳሴ ቤቱን በማሰብ የምናከብረው በዓል ሲሆን፤
​ሁለተኛው በኢትዮጵያውያን ካህናት፣ ምዕመናን እና በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ጸሎት እንዲሁም በኢትዮጵያውያን አርበኞች ተጋድሎ የተገኘው የድል በዓል ነው።
​ይህ የኢትዮጵያውያን ድል ይገኝ ዘንድ ጀግኖች አባቶቻችንን የረዳ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ታቦተ ሕግ በመሆኑ ስለ ታቦተ ሕጉ እንዲሁም ስለ ገዳሙ ጥቂት ለማለት እንወዳለን።
​የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ታቦተ ሕግ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና በንግሥት ጣይቱ መልካም ፈቃድ በመምህር ፈቃደ እግዚአ እንቁላላዊ አማካኝነት በ1895 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። ከዚያም በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ላሉ ኢትዮጵያውያን ምዕመናን በዴር ሱልጣን ገዳም አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
​የመድኃኔ ዓለም ታቦት አገልግሎት መስጠት የጀመረው ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት በ1895 ዓ.ም ሲሆን ታቦተ ሕጉ እስከ ዛሬ ድረስ የምዕመናን…
​ልመናና ጸሎት በመስማት፣ ያዘኑትን በማጽናናት፣ የተቸገሩትን በመርዳት መጠጊያ ለሌላቸው መጠጊያ በመሆን ለ123 ዓመታት አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛል።
​የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ታቦተ ሕግ ከ1895 ዓ.ም ጀምሮ በሦስት የተለያዩ ሀገሮች ላይ አገልግሎት ሰጥቷል።
​1ኛ. በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ለ34 ዓመታት ከኢትዮጵያውያን ምዕመናን ጋር፤
2ኛ. በእንግሊዝ ሀገር ለ4 ዓመታት ከጃንሆይ ጋር፤
3ኛ. በኢትዮጵያ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀድሞ ስሙ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት በአባ ኃይለ ማርያም እየታጠነ ለ2 ዓመታት፤ እንዲሁም የካቲት 12 ሆስፒታል በቀድሞ ስሙ ቤተ ሳይዳ ለ7 ዓመታት።
​አሁን ባለንበት የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለ76 ዓመታት፣ በአጠቃላይ እስከ ዛሬ ድረስ 123 ዓመታት ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
​የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም የሄደበት ዓላማ በዚያ ላሉ ምዕመናን መድኃኔ ዓለምን መማጸኛና መንፈሳዊ አገልግሎትን ማከናወኛ ይሆን ዘንድ ነበር።
​ነገር ግን ወራሪው ጠላት ፋሽስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ተኝቶ ለመግዛት ወረራን ፈጽሞ በነበረበት ወቅት ግርማዊ ጃንሆይ ለተባበሩት መንግሥታት አቤቱታቸውን ለማሰማት ወደ እንግሊዝ ሀገር ተሰደዱ።
​እንግሊዝ ሀገር በስደት በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያ ጉዳይ በምድራዊ ዳኞች ፍትሕ ሊያገኝ ስላልቻለ ጥር 13 ቀን 1929 ዓ.ም ግርማዊነታቸው በኢየሩሳሌም ወደሚገኙት ብፁዕ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ በመጨረሻ የሚመራ ስማቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ እንዲህ የሚል መልዕክት ላኩ፦
​ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ
​ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
​ይድረስ ለብፁዕ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ እግዚአብሔር የኢትዮጵያን ነገር እስከሚያሳየን ድረስ በዚህ ስለምንቆይ ቤተሰቦቻችንም ሃይማኖታቸውን እንዳይዘነጉ አምላካችንን የምንማጸንበት ታቦት ያስፈልገናል።
​ስለዚህ አባ ሐናን መልዕክተኛ አድርገን ስለላክን ከመምህር ገሪማ ጋር ተነጋግራችሁ አንድ ታቦት እና ንዋያተ ቅዱሳት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከውሉን አገልጋዮች ጋር ላኩልን በማለት መልዕክታቸውን አደረሱ።
​መልዕክቱን የተቀበሉት ብፁዕ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ በወቅቱ የአገልጋይ እጥረት እንዳለ ገልጸው የመድኃኔ ዓለም ታቦትንና ንዋያተ ቅዱሳቱን በማሟላት ከአራት አገልጋይ መነኮሳት ጋር መልዕክተኛው አባ ሐናን መሪ በማድረግ ወደ እንግሊዝ ሸኝተዋል።
​ግርማዊ ጃንሆይም ከኢየሩሳሌም የመጣላቸውን የመድኃኔ ዓለም ታቦት የእንግሊዝ መንግሥት በሰጣቸው ባት በሚባል የአምልኮ ስፍራ ሚያዝያ 27 ቀን 1929 ዓ.ም ከኢየሩሳሌም በመጡት መነኮሳት እና በአባ ሐና አማካኝነት ከመላው ቤተሰባቸው ጋር ለሀገራቸው እና ስለ ኢትዮጵያውያን ሱባኤ ይዘው መድኃኔ ዓለምን መማጸን ጀመሩ።
​በወቅቱ ከሚጸልዩት ጸሎት መካከልም፦
​ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 8፥35 በጻፈው መልዕክት የሚገኘውን ኃይለ ቃል በመጠቀም ነበር።
​ቃሉም፦
​”ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይንስ ስደት ወይንስ ራብ ወይንስ ዕራቁትነት ወይንስ ፍርሃት ወይንስ ሰይፍ ነው?” የሚል ሲሆን
​ከሚዘምሩት መዝሙሮች መካከልም፦
“ኢትዮጵያ ሆይ በረከሸ ቀኝ ትርሳኝ” የሚል ይገኝበታል።
​ይህ ኃይለ ቃልና መዝሙር እስከ ዛሬ ድረስ በገዳሙ የሰርክ ጸሎት እየተጸለየ ይገኛል።
​ከ4 ዓመታት በኋላም በ1933 ዓ.ም የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የግርማዊነታቸው እና የኢትዮጵያውያን ጸሎት ተሰምቶ በመድኃኔ ዓለም ተራዳኢነት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ጣሊያንን ድል አደረጉ።
​በዚህ ጊዜ ግርማዊነታቸው “መድኃኔ ዓለም ጸሎታችንን ሰምቶናል፣ በጠላቶቻችን ላይ ድል እንድንቀዳጅ አድርጎናል” አሉ።
​ስለዚህ ጸሎት እና ልመናችንን የሰማን የመድኃኔ ዓለምን ታቦት ይዘን ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መሄድ አለብን በማለት የመድኃኔ ዓለምን ታቦት እና ንዋያተ ቅዱሳት እንዲሁም አገልጋይ መነኮሳትን ከቤተሰቦቻቸው ጋር አንድ ላይ አድርገው በ1933 ሚያዝያ 27 ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።
​በዚህ ዕለትም ግርማዊነታቸው ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በአዲስ አበባ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቅለው በመውለብለብ የድል በዓሉን አክብረዋል።
​ይህ የድል በዓል ዘንድሮ ለ85ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
​የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ታቦት ከአገር ወደ አገር ሲንቀሳቀስ ያረፈባቸው ቦታዎች 5 ናቸው።
​እነሱም፦
• ​ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም
• ​ከኢየሩሳሌም ወደ እንግሊዝ
• ​ከእንግሊዝ ወደ ካርቱም
• ​ከካርቱም ወደ አሜድላ
• ​ከአሜድላ ወደ አዲስ አበባ መሆኑን ታሪክ ያስረዳል።
​የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ታቦት በሦስት ስሞች ይጠራል።
​1ኛ. ዴር ሱልጣን መድኃኔ ዓለም፦ ዴር ሱልጣን መባሉ በኢየሩሳሌም አገልግሎት ሲከናወንበት የነበረው ቦታ ዴር ሱልጣን በመሆኑና ትርጓሜውም የንጉሥ ገዳም ማለት ስለሆነ፤
2ኛ. ስደተኛው መድኃኔ ዓለም፦ ስደተኛ መባሉ ከጃንሆይ ጋር ከአገር አገር አብሮ በመሰደዱ፤
3ኛ. ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም፦ ምስካየ ኅዙናን መባሉ የኅዙናን መመኪያ በመሆኑ ነው።
​ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም የሚለውን ስያሜ ያገኘው የመድኃኔ ዓለም ታቦት በቤተ ሳይዳ ቆይቶ አሁን ያለበት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በ1940 ሚያዝያ 27 በግርማዊነታቸው የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ።
​በኋላ በ1942 ሚያዝያ 27 ተጠናቆ ታቦተ ሕጉ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ወቅት ግርማዊነታቸው ምስካየ ኅዙናን የሚል ሥያሜ ሰጥተውታል።
ቅዳሴ ቤቱም ዘንድሮ ለ76ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
​ይህ የመድኃኔ ዓለም ታቦት እስከ ዛሬ ድረስ በአጠቃላይ ለ123 ዓመታት አገልግሎት ሰጥቷል በመስጠት ላይም ይገኛል።
​በአሁኑ ሰዓት ገዳሙን በበላይነት በመምራት ላይ የሚገኘው የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም አስተዳደር ቦርድ ቀደምት አባቶቻችን በገዳሙ ያስቀመጡትን ሥርዓት በማስጠበቅ በሁሉም መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፎች ምዕመናን በባለቤትነት ይገለገሉ ዘንድ ጥብቅ ክትትል እያደረገ ይገኛል።
​የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም የመንፈሳዊ እና የዓለማዊ ትምህርትን በሚያከናውንባቸው ተቋማት ውስጥ የገዳሙ አስተዳደር ቦርድ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት በመንፈሳዊ እና በዓለማዊ ትምህርት ለሀገር የሚጠቅሙ ትውልድን እያፈራ ይገኛል።
​ገዳሙ በመንፈሳዊው የትምህርት ዘርፍ፦
የንባብ፣ የቅዳሴ፣ የቅኔ፣ የመጻሕፍት ሐዲሳት፣ ብሉያት ተማሪዎችን እያስተማረና ለመምህርነት እያበቃ ለቤተ ክርስቲያን ተተኪ መምህራንን በማፍራት ላይ ይገኛል።
​እንዲሁም በተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲጠነክሩ፣ መስማት ለተሳናቸው በራሳቸው ቋንቋ ቃለ እግዚአብሔርን እንዲማሩ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
​በዓለማዊ ትምህርት ​የገዳሙ ዘመናዊ ትምህርት ቤት በበቁ አመራሮች እና የማስተማር ብቃታቸው በተረጋገጠ መምህራን ይመራ ዘንድ የገዳሙ አስተዳደር ቦርድ ግምገማ አድርጎ ተገቢውን አመራር በተገቢው ቦታ በመመደብ ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ መሰናዶ ትምህርት ድረስ ትውልድን እያስተማረ ለሀገር ተተኪ ምሁራንን በማፍራት ላይ ነው።
​ከዚህ በፊት በገዳሙ ተሠርተው አገልግሎት ላይ የዋሉ የልማት ተቋማት የሆኑትን ባለ ሰባት ፎቅ ሕንፃ፣ መካከለኛ ክሊኒክ እና የተከራዩ ክፍሎችን በማጠናከር ለምዕመናን አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ላይ ይገኛል።
​ከዚህ በተጨማሪ የገዳሙ አስተዳደር ቦርድ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ከተመሠረተበት ትውልድን የማፍራት ዓላማ አንጻር ያሉት የልማት ተቋማት በቂ ባለመሆናቸው ለገዳሙ እና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ርስት የሚሆን ከመሬት ሥር ባለ ሁለት ወለል፣ ከመሬት በላይ ባለ አሥራ አንድ (11) ወለል ግዙፍ ሕንፃ በማስገንባት ላይ ይገኛል።
​ይህን ግዙፍ ሕንፃ ለማስገንባት የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ከስምንት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
​በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት ምዕመናን ናቸውና ሕንፃው ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ምዕመናን በማስተባበር እና የገቢ ማሰባሰቢያ ጉባኤ በማዘጋጀት በተገኘው ገንዘብ ከመሬት ሥር ያለው ሁለት ወለል አርማታ ተሞልቶ ከመሬት በላይ አራተኛ ፎቅ በመገንባት ላይ ይገኛል።
​የተወደዳችሁ ምዕመናንና ምዕመናት ይህ ታሪካዊ ገዳም እያስገነባ ያለው ግዙፍ ሕንፃ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የሚችለው በሁላችሁም ድጋፍ ነው። ሕንፃው እስኪጠናቀቅ ድረስ ገንዘብ ያላችሁ በገንዘብ፣ ጉልበት ያላችሁ በጉልበት፣ ሐሳብ ያላችሁ በሐሳብ ድጋፋችሁን እንድታደርጉ በመድኃኔ ዓለም ስም እንጠይቃችኋለን።
• ​ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
• ​ክቡራንና ክቡራት የመድኃኔ ዓለም ወዳጆች
​በገዳሙና የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች እንዳሉ ሆነው ወደ ዛሬው ታሪካዊ በዓላችን ስንመለስ
​በመንፈስ ቅዱስ በመቃኘት ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት፦
​ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር
​ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች
​ብሎ በተናገረው መሠረት ግርማዊነታቸውና ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ሳይለያዩ በአንድነት የጸሎት እጆቻቸውን ወደ መድኃኔ ዓለም ዘርግተው በመጸለይ ወራሪው ፋሽስት ጣሊያንን ድል አድርገዋል።
​የጥንት አባቶቻችን ከባሕር ማዶ ተሻግሮ የመጣ የሚታይ ጠላትን በኃይለ እግዚአብሔር ድል አድርገው የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በማስከበር ባሕልና ቋንቋችን እንዲሁም ሃይማኖታችን ሳይበረዝ ለእኛ እንዲደርስ አድርገዋል። በመሆኑም በበዓሉ እግዚአብሔር በረድኤቱ ቤተ ክርስቲያናችንን እና ሀገራችንን የጠበቀበትን መንገድ እያሰብን በምስጋና የምናከብረው ነው።
​ስለዚህ የተወደዳችሁ ምዕመናን አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩልንን ባሕልና ታሪክ ጠብቀን ለሚመጣው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል።
​በዓሉን በዓለ ሰላም፣ በዓለ ፍሥሐ ያድርግልን።
​መድኃኔ ዓለም አምላካችን ሀገራችን ኢትዮጵያን ይጠብቅልን
ሕዝባችንን ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ይሰውርልን
​አሜን!!!
​ሚያዝያ 27/08/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
© EOTC tv

በምሁር ኢየሱስ ገዳም የአዲሱን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ቡራኬን ተከትሎ ሲከበር የነበረው በዓል ተጠናቀቀ

ሚያዚያ ፳፭ ቀን ፳፻፲ወ፰ ዓ.ም
በታላቁ አባት በአቡነ ዜና ማርቆስ የተገደመው የምሁር ኢየሱስ ገዳም ሚያዚያ ፳፬ ቀን በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፀሎተ ቡራኬ ታቦታቱ ከነበሩበት መቃኞ ቤተ ክርስቲያን ወጥተው ወደ አዲሱ ሕንጻ ቤተ ክርስታያን መግባታቸው ይታወሳል።በዓሉ በዛሬው ዕለትም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ታቦታቱ ታጅበው ወጥተው በልዩ ድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በዕለቱ የሕንጻ ሥራውን አስመልክቶ በገዳሙ አበመኔት በመምህር አባ ዘኢየሱስ ቀርቧል።
በሪፖርቱ መነሻም የምሁር ኢየሱስ ገዳም አንጋፋ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን ምስረታውም ከ840 ዓ.ም በፊት በ13 ክ.ዘመን እንደተገደመ እና የገዳሙ መስራች ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ 3 ጊዜ ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ወደ ገዳሙ ማድረጋቸው ተገልጧል።
በወቅቱ ሕዝቡ እግዚያብሔርን ከማምለክ ወደ ባዕድ አምልኮ ተሻግሮ የነበር ቢሆንም ጻድቁ ሕዝቡን አስተምረው ወደ እግዚአብሔር መመለሳቸው ተወስቷል።
ጻድቁ ለሁለተኛ ዙር ሲመጡም 156 አብያተ ክርስቲያናትን በአካባቢው ማሠራታቸውም ነው የተገለፀው።
ከገዳሙ ታሪክ ጋር ተያይዞም ጻድቁ በዘመናቸው የሠሩት ዘርፈ ብዙ ገድልና ታሪካቸው ታውሷል።
በዘመኑም ገዳሙ በኑቡረ ዕድ ይተዳደር እንደነበር እና እንደ አክሱምና ጎንደር የትምህርት ተቋም ሆኖ ለዘመናት የቆየ መሆኑም ተጠቅሷል።በዘመናት ሂደት በዋናነትም ከመሬት ላራሹ ጀምሮ ገዳሙ እንደተዳከመም ያነሱት የገዳሙ አበመኔት አባ ዘኢየሱስ ከ1988 ጀምሮም በድጋሚ ገዳሙ በብፁዕ አቡነ መልከ ጼድቅ ካልዐይ ጥረት ማንሰራራቱን ጠቅሰዋል።
ዛሬ ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንም 17 ዓመት መፍጀቱ በሪፖርቱ የተጠቀሰ ሲሆን ይህም ሥራ የተጀመረው በብፁዕነታቸው በ2000 ሲሆን በ2002 ብፁዕነታቸው ማረፋቸው ተገልጿል።
በወቅቱ በወልቂጤ በአዲስ አበባ በሰበታ የጀመሯቸው ትምህርት ቤት እና የሕንጻ ሥራ የነበር በመሆኑ ከጀመሯቸው የልማት ሥራዎች ጋር ይህም የሕንጻ ሥራ ለፍጻሜ መብቃቱ ተገልጿል።
የሕንጻ ሥራውን አስመልክቶ የፈጀው የገንዘብ መጠን በሪፖርት ያልቀረበ ሲሆን ይህንንም አስመልክቶ አባ ዘኢየሱስ በምክንያትነት ያቀረቡት ከሕሊና ጀምሮ ብዙ መዋዕለ ነዋይ የፈሰሰበት በመሆኑ ገንዘብ አይተምነውም ነው ያሉት።
በተጨማሪም ለሕንጻ ሥራው ከሳንቲም ጀምሮ ከፍተኛውን ብር የሰጡ በእግዚአብሔር ፊት እኩል በመሆናቸው ለይቶ ማመስገን እንደማይቻል ነው በምክንያትነት የተጠቀሰው።
ከዚህም የተነሳ በሌሎች አብያተ ክርስቲያን እንደተለመደው የምስጋናና የእውቅና ሰርተፊኬት ያልተከወነ ሲሆን ከዚያ ይልቅ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎተ ማርየም እንዲጸለይላቸው ተደርጓል።
በገዳሙ የበዓላትን ቀንን ጨምሮ የገንዘብ አሰባሰብ የማይደረግ መሆኑም ተገልጿል።
ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ በገዳሙ መነኮሳት እና መነኮሳይት የተሳለ ኢትዮጵያዊ መልክ ባላቸው ቅዱሳን ያጌጠ ሲሆን አንዳንዶቹም ማብራሪያ የሚሹ በመሆናቸው ወደፊቱ በመጽሔት ማብራሪያ እንደሚቀርብበት ተነግሯል።
በዕለቱም ብፁዓን አባቶች ትምህርተ ምዕዳን የሰጡ ሲሆን የብፁዕ አቡነ መልከ ጼድቅ ካልዓይ በሕይወት በነበሩበት ወቅት ከብፁዓን አባቶች ጋር የነበራቸውም ቆይታ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ በትዝታ የዳሰሱበት ነበር።
ትላንት ሚያዚያ ፳፬ በነበረው መርሐ ግብርም ለብፁዕነታቸው የተሠራው መታሰቢያ ሀውልትና ቤተ መዘክር መመረቁ ይታወሳል።
በዕለቱ በብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ቅኔ የቀረበ ሲሆን በደብሩ ካህናትም ወረብ ቀርቧል።
በበዓሉ ላይ ከአዲስ አበባና ከወረዳው የመጡ በርካታ ምዕመናን ፣ የሙር አክሊል ወረዳ አስተዳዳር አቶ ብስራት ገብሩ እና ሌሎችም የመንግሥት ኃላፊዎች፣የእንድብር ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ተገኝተዋል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ለካህናት የቅዳሴ አልባሳትም በስጦታ አበርክተዋል።
በመጨረሻም ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ለመምሪያ ኃላፊዎች እና ለገዳሙ አበመኔት ለመምህር አባ ዘኢየሱስ የሽልማት መርሐ ግብር ተከናውኖ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ መርሐ ግብሩ ተጠናቋል።©E.o.t.c.tv.

ታሪካዊው የምሁር ኢየሱስ ገዳም አዲሱ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ተከበረ

ሚያዚያ ፳፬ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
የምሁር ኢየሱስ ገዳም በጉራጌ ዞን፣ በምሁር አክሊል ወረዳ የሚገኝ ከአዲስ አበባ በ207 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳም ነው። ገዳሙ የተመሰረተው በ14ኛው ክፍለ ዘመን በታላቁ አባት በአቡነ ዜና ማርቆስ እንደሆነ የገዳሙ ታሪክ ይነግረናል።
ገዳሙ የከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ማዕከል በመሆን፣ጥንታዊና ብርቅዬ የብራና መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳትን ጠብቆ በማቆየት፣እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያላቸው ሊቃውንትን በማፍራት ይታወቃል።በተለይም በውስጡ የሚገኘውና እጅግ ተአምረኛ እንደሆነ የሚነገረው “የምሁር ኢየሱስ” ስዕለ አድኖ ለብዙዎች የፈውስና የበረከት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።
ገዳሙ በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ውስጥ ስመ ጥር የሆነ የጉባኤ ቤት መገኛም ነው። በተለይም በቅኔ፣ በዜማና በመጻሕፍት ትርጓሜ ጥልቅ እውቀት ያላቸውን ሊቃውንት በማፍራት፣በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ አድባራትና ገዳማት ባለ ውለታም ነው።
ገዳሙ ከመንፈሳዊ ሥራው ባሻገር ለኅበረተሰቡ አገልግሎቶች የሚውሉ በሐዋርያት ከተማ ውስጥ የመዋዕለ-ሕጻናት ትምህርት ቤት፣ የእንግዳ መቀበያና ማረፍያ ቤት፣ በገዳሙ ግቢ ውስጥ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ት/ቤት፣ በወልቂጤ ከተማ ደግሞ ከመዋዕለ-ሕጻናት እስከ 10ኛ ክፍል ባለሶስት ፎቅ ሕንጻ ት/ቤት አስገንብቶ በማስተማር የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡
በገዳሙ የተለያዩ ክብረ በዓላት የሚከበሩ ሲሆን በዋናነት ታህሳስ ሶስት የአቡነ ዜናማርቆስ የእረፍት ቀን መታሰቢያ፣አብይ ፆም አጋማሽ(ደብረዘይት) ልዩ የበገና ምሽት፣ በግንቦት ወር ውስጥ አብይ ፆም በተፈታ አርባኛው ቀን(የእርገት በዓል) ሲሆኑ በእነዚህ በዓላት ወቅት ቁጥሩ በዛ ያለ ከተለያዩ የአካባቢው፣ የሃገሪቱ ክፍሎች እና ከሃገር ውጪ በሚመጡ ቱሪስቶች በድምቀት ይከበራል።
በዛሬው ዕለት ደግሞ ይህንን ታሪካዊ ገዳም ከነበረበት የቆየ ህንጻ ቤተ ክርስቲያን ወደ ዘመናዊና ሰፊ ቤተ ክርስቲያን ለመቀየር በርካታ ምእመናን፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የገዳሙ ልጆችና በጎ አድራጊዎች በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸውና በዕውቀታቸው ደክመዋል። ዛሬ ሚያዚያ 24 ቀንም ይህ ድካም ፍሬ አፍርቶ የገዳሙ አዲሱ ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ቤት (ምረቃ) በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በዕለቱ በተለያየ አልባሳት ከደመቁ ካህናትና ሰንበት ተማሪዎች በተጨማሪ ከገዳሙ አቅራቢያ ከሚገኘው ከሃዋርያት ከተማ ጀምሮ በባንዲራ የተዋበ አካባቢ፣ የሚጥለውን ዝናብና ንፋስ ተቋቁመው ገዳሙ ድረስ በተለያዩ መኪኖች ያጀቡ የዞኑ ፖሊሶች፣ ሞተር ሳይክሎችና ባጃጆች እንዲሁም በየራሳቸው ባህልና ወግ የሚዘምሩ ነዋሪዎችን በዓሉን ልዩ ድምቀት ሰጥተውት ውለዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣የገዳሙ መነኮሳትና አባቶች፣ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን በስፍራው ተገኝተው ይህንን ታሪካዊ በዓል በዝማሬና በደስታ እያጀቡት ይገኛል።
በተጨማሪም የብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ካልኣይ የመታሰቢያ ሐውልት እና ቤተ መዘክር በገዳሙ ግቢ ተመርቋል።
መርሐ ግብሩ በነገው ዕለትም የሚቀጥል ሲሆን ስርዓተ ቅዳሴ ተከውኖ ታቦታቱ ወጥተው ሕዝቡን ይባርካሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት
©EOTC tv

በሸገር ሀገረ ስብከት የኮዬ ገላን ክፍለ ከተማ ደንጎራ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ሕንጻ የቤተክርስቲያን በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ቅዳሴ ቤቱ ከበረ

ሚያዚያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም
ሚያዝያ 24 ቀን 2018 ዓም በተካሄደው የሕንጻ ቤተክርስቲያን ምርቃት ሥነ ሥርዐት ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንደተናገሩት “እንኳን ደስ አላችሁ፣ ስትደክሙበት ለነበረው ሥራችሁ ለፍጻሜ በቅቷል።” ብለዋል። ብፁዕነታቸው አክለውም “የድካማችሁን ፍሬና የሥራችንን ውጤት ለማየት ያበቃን አምላካችን እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይድረሰው።” ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ብፁዕ አቡነ ሚካኤል የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሉቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት ቤተክርስቲያን የሚሠራ የተፈቀደለት ነው። እናንተ ተፈቅዶላችሁ ቤተክርስቲያን ስለ ሠራችሁ እንኳን ደስ አላችሁ። ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ በርናባስ የዋግህምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ መልአከ ኃይል አባ አፈወርቅ ዮሐንስ የመልካ ኖኖ፣ጉጂ ገፈርሳ ክፍለ ከተማ ኃላፊ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የለሚ ኩራ ሥራ አስኪያጅ፣ ሊቀ ልሣናት በዳሳ ቶላ የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የአጥቢያው ምእመናንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።©Eotc tv.

በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት በሰበታ ገላን ጉዳና ፉሪ የዓለም ገና ደብረ ቀርሜሎስ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ተባረከ

ሚያዝያ 22 ቀን 2018 ዓ.ም
በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት በሰበታ ገላን ጉዳና ፉሪ ክፍላተ ከተማ ቤተክህነት የዓለም ገና ደብረ ቀርሜሎስ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም የበላይ ኃላፊ ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የራያና አከባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳሰ፣ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የቅድስት ሀገር የኢየሩሳሌም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ መልአከ ሰላም ዓለማየሁ ሺፈራው የሸገር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ፣ መልአከ ኃይል አባ አፈወርቅ ዮሐንስ የ3ቱም ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ስራ አሥኪያጅ፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣የሰንበት ትምሕርት ቤት ዘማሪያን እና ዘማሪያት፣ በርካታ ምዕመናንና ምዕመናት በተገኙበት በብፁዓን አባቶች ቡራኬ ተባርከዋል።
ይህ ታላቅ ቤተ መቅደስ በኪነ ሕንጻ አሰራር በአይነቱ በውበቱ ዘመን ተሻጋሪ መሆኑን ቤተ መቅደስ ሲሆን ግንባታ በተጀነርፕ በ13ኛ ዓመት ተጠናቆ ላዛሬው ለምእቃት ቀ. በቅቷል ።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ይህ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ተሠርቶ ይጠነቀቃል ተብሎ ባይታሰብም በእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ እና በእናንተ ብርታት ለምርቃት በመብቃቱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ በበኩላቸው ይሄንን የደከማችሁበትን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ለምርቃት በቅቶ ስላያችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ በቤተክርስቲያን የምንሰበሰበብ ለዘለዓለማዊ ድኅነት ነው፤ ቤተክርስቲያን መማጸኛ እንዲሁም የሰውና የቅዱሳን መገናኛ ናትም ብለዋል ስለዚህ ወደ ቤተክርስቲያን የምንመጣው ምድራዊው በረከት፣ ሰማያዊ ክብር ለማግኘት ነውና ቤተክርስቲያን ልንጠብቃት፣ ልንከባከባት ያስፈልጋል በማለት አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በተጨማሪም በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አመራር ሰጪነት ብዙ ልማቶች እየተሠሩ እንደሆነም ጠቅሰዋል፤ ብፁዕነታቸው አክለውም እግዚአብሔር ህዝቡን የሚያገለግል፣ ቤተክርስቲያንን የሚያንጽ አባት ስለተሰጣችሁ እግዚአብሔርን ልታመሰግኑ ይገባልም በማለት ቃለ ቡራኬያቸውን አስተላልፈዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ለሕንጻ ቤተክርስቲያኑ መሠራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉት ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
በተጨማሪም ደብሩ ለሚያከናውናቸው መሠረታዊ የልማት ሁለገብ G-1 ሕንጻ የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል ።
በመጨራሻም በብፁዓን አባቶች ቃለምዕዳንና ቡራኬ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።©ም/ዙ/መ/ገ/ሚዲያ

“የአበው ሥርዓት ለቤተ ክርስቲያን አንድነት” በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የቆየውን የገዳማት አበምኔቶችና እመምኔቶች አገር አቀፍ ጉባኤ ተጠናቀቀ

ሚያዚያ ፳፫ ቀን ፳፻፲ወ፰ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ባዘጋጀው መርሐ ግብር፤ ከመላው ኢትዮጵያ የአንድነት ገዳማት ለተውጣጡ አበምኔቶች እና እመምኔቶች “የአበው ሥርዓት ለቤተ ክርስቲያን አንድነት” በሚል ርዕስ ሲሰጥ የነበረው የሥልጠና እና የምክክር ጉባኤ ፍጻሜውን አግኝቷል።
ከሚያዝያ ፳፪ እስከ ሚያዚያ ፳፫ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
ድረስ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው በዚህ ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ፤ የገዳማቱን አስተዳደራዊ እና መንፈሳዊ አቅም የሚያጎለብቱ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል። ከዚህም ባለፈ ተሳታፊዎቹ አባቶች እና እናቶች እርስ በርስ የልምድ ልውውጥና ጥልቅ ምክክር ያደረጉ ሲሆን፣ ከብፁዓን አባቶችም አባታዊ ቃለ ምዕዳን ተሰጥቷቸዋል።
በጉባኤው ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የደቡብ ምዕራብና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣
የመንበረ ፓትርያርክ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ቶማስ የምሥራቅ ጎጃም፣ የመተከል እና አዊ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተገኝተዋል። በተጨማሪም
የገዳማት መምሪያ ዋና ኃላፊ መጋቤ ካህናት አባ ሀብተ ጊዮርጊስ ዓሥራትን ጨምሮ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ የገዳማት
አበምኔቶች (አባቶች) እና እመምኔቶች (እናቶች) የጉባኤው ተካፋይ ነበሩ።
በመዝጊያው መርሐ ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ሰፋ ያለ አባታዊ መልእክትና መመሪያ አስተላልፈዋል። ብፁዕነታቸው በንግግራቸው “ገዳማት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጽናት መሠረቶች ናቸው” በማለት አጽንዖት ሰጥተው፣ አባቶችና እናቶች በአንድነት መሰባሰባቸውና መወያየታቸው ትልቅ ውጤት ያመጣ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም “ለገጠሙን ችግሮች በጋራ ባደረግነው ውይይት መፍትሔ አግኝተናል፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን ካለችበት ሁኔታ አኳያ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የጸኑ ጠንካራ
መነኮሳት በእጅጉ ያስፈልጓታል። ስለዚህም ወደ ቀደመው እና ወደ ጥንታዊው የአበው መንፈሳዊ ሕይወት መመለስ ግድ ይለናል”
ብለዋል።
ከተሳታፊዎች ለተነሳው የማረፊያ ቦታ ጥያቄ በተመለከተም፣ ጉዳዩን አጥንተው ለቅዱስ ሲኖዶስ እንደሚያቀርቡ ብፁዕነታቸው ቃል ገብተዋል።
በመጨረሻም ገዳማውያኑ የቅዱስ ሲኖዶስ የጸሎት መሠረት መሆናቸውን በማስታወስ፣ “ጾምና ጸሎት ትልልቅ
መንፈሳዊ የጦር መሣሪያዎች በመሆናቸው ለሀገር እና ለቤተ ክርስቲያን ሰላም በትጋት ጸልዩ” ሲሉ አደራ ብለዋል።
ለሁለት ቀናት በስኬት ሲካሄድ የቆየው ይህ የምክክር እና የሥልጠና ጉባኤም፣ በአረጋዊው አባት በብፁዕ አቡነ ዮሴፍ
አባታዊ ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ ተጠናቋል።©EOTC t.v.