በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ተጀምሮ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ትጋት ለፍጻሜ የበቃው ባለ 480 ካሬ ሜትር ሁለገብ ሕንጻ ተመረቀ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ምዕመናን በተገኙበት፣ በአዲስ አበባ አሮጌ ቄራ አካባቢ የተገነባው ዘመናዊ ሁለገብ ሕንጻ በዛሬው ዕለት በደመቀ ሁኔታ ተመርቋል። ይህ በ480 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈውና ባለ 11 ወለል (B+G+10) የሆነው ሕንጻ፣ ግንባታው የተጀመረው በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅነት ዘመነ ሢመት ነበር። ሆኖም ግንባታው በአራት የተለያዩ ኮንትራክተሮች እጅ በማለፉ ምክንያት ከፍተኛ መጓተት አጋጥሞት ቆይቷል።
​ይህንን መጓተት ለመቅረፍ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላላ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ከተሾሙ በኋላ፣ የአሠራር ሥርዓቱን በማስተካከልና ለሮሃ ኮንስትራክሽን ሙሉ ኃላፊነት በመስጠት፣ ግንባታው በአጭር ጊዜ ውስጥ ማለትም በ40 ቀናት አካባቢ ተጠናቆ ዛሬ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም ለምረቃ እንዲበቃ ሆኗል።
​በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላላ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
​የሕንጻውን ዝርዝር ሁኔታ በሚመለከት የግንባታ አማካሪው ኢንጂነር ቀሲስ ደመቀ አሸናፊ እንዳብራሩት፣ ሕንጻው ለእያንዳንዱ ቤተሰብ ምቹ የሆኑ ባለ ሦስት መኝታ ቤቶችን የያዘ ሲሆን፣ በውስጡም ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶችና ባልኮኒዎች ተካተውለታል። በተጨማሪም ሕንጻው የሚከተሉትን ዘመናዊ የደኅንነት ሥርዓቶች ያካተተ ነው፦
​ሙሉ ሕንጻውን የሚቆጣጠር የሴርቨላንስ ካሜራ ተገጥሞለታል።
​ሙቀትና ጭስን ለይቶ የሚያውቅና አደጋ ሲከሰት አላርም የሚያደርግ የፋየር ሲስተም ኮንትሮል አለው።
​በእያንዳንዱ ወለል ላይ የእሳት አደጋ መከላከያ (ፋየር ሃይድራንት) እና የአደጋ ጊዜ መውጫ (ኢመርጀንሲ ኢግዚት) ተዘጋጅቶለታል።
​ይህ ታላቅ የምረቃ ሥነ ሥርዓት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጸሎትና ቡራኬ ተጠናቋል።

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነችው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶሳዊ በመሆኗ አበው ቅዱሳን በፍትሕ መንፈሳዊና በጉባኤ አድያም ዘአንጾኪያ “ወይኩን ሲኖዶስ ዘጳጳሳት ፪ተ ጊዜያተ በበዓመት – የጳጳሳት ጉባኤም በዓመት ሁለት ጊዜ ይሁን” ብለው በደነገጉት ቀኖና መሠረት፤ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሚመራው፣ የሐዋርያት መንበር ወራሽ የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤውን በኅብረተ መንፈስ ቅዱስ ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ/ም ድረስ አካሄዷል፡፡
ምልዓተ ጉባኤው ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት፤ ስለ ሰው ልጅ ሁሉ ደኅንነትና ክብር፣ በአጠቃላይ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሰፊ ውይይቶችን በማድረግ ዘመኑን የዋጁ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ከውሳኔዎቹም መካከል፡-
የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት መጠበቅና ማስጠበቅ የቅዱስ ሲኖዶስ ተግባር በመሆኑ ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን በአንድነቷና በሉዓላዊነቷ እንደተረከብናት ለወደፊቱም ሉዓላዊ ክብሯ ተጠብቆ እንድትቀጥል በምልዓተ ጉባኤው የተሠየመው በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራው “የሀገራዊ ሰላምና የቤተ ክርስቲያን አንድነት” ኮሚቴ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ በተረጋጋ መንገድ እንዲካሄድ፣ ለሀገር ሰላምና ለሕዝብ አንድነት በሚጠቅም ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትጸልይ ሲሆን ምርጫው በሁሉም ወገን ለኢትዮጵውያን ዘላቂ ሰላምንና መረጋጋትን የሚያስገኝ ሆኖ እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ያሳስባል፡፡
ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የአርሲ ሀገረ ስብከትን በሊቀ ጵጵስና በቋሚነት እንዲመሩ፣ ሕዝቡን እንዲያጽናኑ እየደረሰ ያለውን ችግር ከቋሚ ሲኖዶስና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከሚመራው የሰላም ኮሚቴ ጋር በመሆን የሚመለከተውን የመንግሥት አካል በማነጋገር ዘላቂ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወስኗል፡፡
ከጥንት ጀምሮ “ቅዱስ ሲኖዶስ” በሚል ርእስ እየተዘጋጀ ይታተም የነበረው ታሪካዊ መጽሔት የቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖናዊ ውሳኔዎችን በማካተት በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አስፈጻሚነት ሕትመቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
የቤተ ክርስቲያናችንን ደንቦች መመሪያዎች መርምሮ ማጽደቅ የቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ ሥልጣን በመሆኑ፡-
የስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ተልእኮ ማስፈጸሚያ ደንብ በብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሰብሳቢነት
የአንድነት ገዳማት ኅብረት መተዳደሪያ ደንብ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስና ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ባሉበት በድጋሚ እንዲታይና ሌሎቹም ለውሳኔ የቀረቡ ደንቦች በሊቃውንትና በሕግ ባለሙያዎች ታርመው ለጥቅምት 2019 ዓ/ም ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል::
የቀድሞው የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ”ና “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በሚሉ አርእስት አዘጋጅተው ያሳተሟቸው መጻሕፍትን የማሳተምና የማሰራጨት የባለቤትነት መብት ከሚያዝያ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
ከተለያዩ አህጉረ ስብከት በቀረቡ ጥናቶችና የማጣራት ውጤቶች መሠረት፡-
የደቡብ ሱዳን ሀገረ ስብከት ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ጋር ተደርቦ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ፤
ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ሊቀ ጳጳስ የጋምቤላንና የቤንሻንጉል ጉምዝ አህጉረ ስብከትን ብቻ እንዲመሩ፤
ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከትን እንደያዙ እንዲቀጥሉ፤
ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከትን ደርበው በአባትነት እንዲመሩ፣
የኮንታ ዞን ሀገረ ስብከት እንዲሆን የቀረበው ጥያቄ የጸደቀ በመሆኑ ሀገረ ስብከቱ ራሱን ችሎ እንዲደራጅና በብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የልማት ተግባራትን ምልዓተ ጉባኤው በከፍተኛ ደረጃ በማድነቅ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ/ ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ሲቲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ በአባታዊ አመራር የፈጸሙት አስደናቂ የሥራ አፈጻጸም በጉልህ የሚታይ ለውጥ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅም፣ ሉዓላዊ ክብሯን የሚያስጠበቅ፣ ለሁሉም አበው ምሳሌነት ያለው በመሆኑ ምልዓተ ጉባኤው እጅግ ከፍ ባለ ክብር አመስግኗል፡፡
በዚህም መሠረት በብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጁ አባታዊ መሪነት እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት ማለትም፡-
የቤተ ክርስቲያንን ቀደምት ሠነዶች በዲጂታል ቴክኖሎጅ እንዲደራጁ የተደረገበት ሥልት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤
ከ1970 ዓ/ም ጀምሮ በመጋዝን ተከማችተው የቆዩ በርካታ ልዩ ልዩ መጻሕፍትን የማሠራጨት ሂደት በተጀመረው መንገድ እንዲጠናቀቅ፤
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የኢንፎርሜሽንና ኮምኒኬሽን ተጠቃሚ እንድትሆን የተጀመረው ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር በየደረጃው ተጠናክሮ ተግባራዊ እንዲሆን፤
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር የተጀመሩ የሕንፃ ግንባታዎችና አጠቃላይ የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ሁሉም አህጉረ ስብከትና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦና ትብብር እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ያሳስባል፡፡
በሰሜን አሜሪካ የሰሜን ካሊፎርኒያ፣ ኔቫዳና አሪዞና ሀገረ ስብከት ኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስና ቅድስት አርሴማ ገዳም የመንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የአብነት ት/ቤት ሥርዓተ ትምህርት የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ታሪክና ትውፊት በጠበቀ መልኩ ተጠናክሮ መዋቅራዊ ተጠሪነቱም በአግባቡ ተጠብቆ ሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያቀረበውን የ2019 ዓ/ም በጀት በማጽደቅ በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ እንዲውል ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፡፡
በመጨረሻም ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተነጋገረባቸው ጉዳዮች በትኩረት የተወያየው የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ዕድገትና ተቋማዊ ሕልውና ስለማስጠበቅ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ሀገራችንን ጨምሮ በመላው ዓለም እየታየ ያለው ግጭትና የሰላም መታጣት በእጅጉ አሳስቦታል፡፡
በመሆኑም ስለ ዓለምና ስለ ሀገራችን ሰላም፣ ስለ ሰው ልጆች ደኅንነት፣ በየቦታው በሃማኖታቸው ምክንያት መከራ የሚደርስባቸውን በየቦታው የሚገኙና ግጭት ባለባቸው ቦታዎች ያሉ ኦርቶዶክሳውያንን በማሰብ በመጪው የ2018 ዓ/ም ጾመ ሐዋርያት በመላው ዓለም ባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት፣ አድባራትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጸሎተ ምሕላ እንዲደርስ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
በመላው ዓለም፣ በደቡብ አፍሪካና በሳውዲ ዐረቢያ የሚኖሩ ዜጎቻችን ሰብዓዊ መብት እንዲከበር፣ የርኅራኄ ምሕረትና ፍትሕ እንዲያገኙ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ክትትል እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ጥሪውን በማቅረብ ለሰባት ቀናት ሲያካሂድ የሰነበተውን ቀኖናዊ ጉባኤ ዛሬ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም. በጸሎት አጠናቋል፡፡
“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ”
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ
ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ/ም

ቅዱስ ሲኖዶስ በልማትና ዘመናዊ አሠራር ላይ ያተኮሩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ለ6 ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን የ2018 ዓ.ም የርክበ ካህናት ጉባኤውን አጠናቀቀ

ግንቦት 5 ቀን 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለስድስት ተከታታይ ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን መደበኛ የምልኣተ ጉባኤ ስብሰባውን በ22 አጀንዳዎች ላይ በመወያየትና ለቤተክርስቲያናችን ቀጣይ ጉዞ ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ማጠናቀቁን የቅዱስ ሲኖዶስ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ቀሲስ ዳንኤል ሰይፈ-ሚካኤል ለEOTCTV በሰጡት ዕለታዊ መግለጫ አስታውዋል።
ኃላፊው በሰጡት ማብራርያ፣ ጉባኤው በተለይም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እየተከናወኑ ያሉትን የልማት፣ የዘመናዊ አሠራር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች በዝርዝር ከገመገመ በኋላ ከፍተኛ አድናቆቱን መግለጹን ተናግረዋል።
በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሆኑት በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ አመራር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በምስል እና ድምፅ የተደገፈ ሰፊ ሪፖርት ለምልአተ ጉባኤው መቅረቡን የጠቀሱት ረዳት ፕሮፌሰር ቀሲስ ዳንኤል፣ ሪፖርቱ “ቤተክርስቲያናችን ለዘመናት ያላትን ታሪካዊ አስተዋጽኦ እያስጠበቀች፣ ከዘመኑ ጋር የሚራመድ አሠራርን ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ርብርብ በጉልህ አሳይቷል” ሲሉ ገልጸዋል።
በሪፖርቱ ከቀረቡት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል በመንበረ ፓትርያርክ ግቢ እና “በኮሪደር ልማት” በተገኙ መሬቶች ላይ የተጀመሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ግቢውን የማስዋብና ምቹ የማድረግ ሥራዎች እንደሚገኙበት የገለጹ ሲሆን ረዳት ፕሮፌሰር ቀሲስ ዳንኤል እንዳብራሩት፣ “ምልአተ ጉባኤው በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገኙትን እነዚህን ተጨባጭ ውጤቶች በማየት ሥራዎቹን በከፍተኛ አድናቆት ምልዓተ ጉባኤው ተቀብሏቸዋል።” ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ለዘመናት ተቀምጠው የነበሩ ታሪካዊ የሰነድ መዛግብትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የማስቀመጥ ሥራ መጀመሩና
አስተዳደራዊ መዋቅሩን በማዘመን የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተብራርቷል።
ለረጅም ጊዜ በመጋዘን የቆዩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማሳተም ለምዕመናን ተደራሽ የማድረግ ሥራም በስፋት መከናወኑን ኃላፊው አክለው ገልጸዋል።
ብፁዓን አባቶች በቀረበው ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ “የተጀመሩት ስራዎች የቤተክርስቲያኒቱን ክብርና ልዕልና
የሚያስጠብቁ፣ ተቋማዊ ህልውናዋን የሚያጠናክሩና ለምዕመናን የሚሰጠውን አገልግሎት የሚያዘምኑ ናቸው” በማለት ሙሉ ድጋፋቸውን መግለጻቸውን ረዳት ፕሮፌሰር ቀሲስ ዳንኤል አስረድተዋል።
በዚህም መሠረት ምልኣተ ጉባኤው የተጀመሩት የልማትና የማዘመን ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከመወሰኑም በላይ፣ ሌሎች አባቶችም በየአህጉረ ስብከታቸው ተመሳሳይ ማሻሻያዎችን እንዲተገብሩ ጥሪ ማቅረቡን ገልጸዋል።
ጉባኤው ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጥም አረጋግጧል ተብለዋል ።
ጉባኤው በሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ከመከረ በኋላም፣ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት በቋሚ ሲኖዶስ ውስጥ የሚያገለግሉ ብፁዓን አባቶችን ምርጫ ማካሄዱን የኮሙኒኬሽን ኃላፊው ተናግረዋል።
በመጨረሻም፣ “ለቀናት በተለያዩ አገራዊና ሃይማኖታዊ አጀንዳዎች ላይ ሲመክር የቆየው የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልኣተ ጉባኤ፣ በነገው
ዕለት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሚሰጡት ቃለ ምዕዳንና አባታዊ ቡራኬ በይፋ ይጠናቀቃል” ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰር ቀሲስ ዳንኤል ሰይፈ-ሚካኤል ማብራርያቸውን አጠቃለዋል።©EOTc tv

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የኢትዮጵያ ፈደራል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ “ጠንካራ ትብብር ለሀገር ሰላም! ሰላም የወል ሀብታችን ነው!” በሚል መሪቃል ስለሰላም በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የጋራ ስምምነት ተፈራረመ

ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም
ከየቤተ እምነቱ የተወከሉ አባቶች በተገኙበት “ጠንካራ ትብብር ለሀገር ሰላም በሚል የተከናወነው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የጋራ ስምምነት ፊርማ ፤ በሀገራችን በሚከናወኑ ምክክሮች ሰላምን ለማረጋገጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑ ተገልጿል ።
የስምነት ስነዱን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ተፈራርመዋል ።
በዚሁ ስምምነት ውስጥ ወንጀለኞችን መከላከል ፣ በጋራ በመሆን ወንጀል ሳይፈጠር አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል አቅም መፍጠር ፣ በሕግ ገደብና ነጻነት አንዱ በሌላው ጣልቃ ሳይገባ፣ የእምነት ተቋማት እና የሕግ አስከባሪው አካል በየራሳቸው የሕግ ማዕቀፍ እንዲሠሩ ድንበር የለየ መሆኑ ተገልጿል ።
ሚስጥራዊነት በጋራ ስራዎች ወቅት የሚገኙ መረጃዎችና በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉ ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ የመንበረ ፓትርያርከሰ ጠቅላይ ቤተክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ “እግዚአብሔር የሚናገረውን እሰማለሁ፥ ሰላምን ለሕዝቡና ለቅዱሳኑ ይናገራልና” የሚለውን ቃል በመጥቀስ፣ ቤተክርስቲያን ሁልጊዜ ስለ ፍጻሜውም ሰላም እንደምትጸልይ ገልጸዋል ።
ሼህ ኢብራሂም ቱፋ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ” ሰላም እንዲመጣ የሃይማኖት ሕግጋትን በማክበር እያንዳንዱ አማኝ የእምነቱን አስተምህሮ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተክርስቲያናት ካውንስልን በመወከል ንግግር ያደረጉት ቄስ ደረጀ ጅምበሩ የክርስትና እምነት ዓላማ ሰላምን ማጽናት ፣ እንደሆነ ገልጸው መጽሐፍ ቅዱስ ለሰላም ወሳኝ እንደሆነ አስገንዝበዋል ።
ይህ የጋራ ስምምነት ሀገራችንን ሰላምና ደኅንነት በመጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ላይ ለማቆም ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተወስቷል።© EOTC t.v

ከግንቦት እስከ ግንቦት

ክፍል አንድ
አምና በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የግንቦቱን ርክበ ካህናት ጉባኤውን በሚያካሒድበት ወቅት አንዱ አጀንዳ አድርጎ የያዘው የጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ምርጫን ነበር።
በምርጫውም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በማድረግ በከፍተኛ ድምጽ መርጦ ሾማቸው።
ወዲያውኑም ሁለቱ ብፁዓን አባቶች ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አባታዊ ቡራኬና መመሪያን በመቀበል፣አስፈላጊና ውሳኔ የሚሹ ሥራዎችን በቋሚ ሲኖዶስ በማስወሰንና ውሳኔዎችን በጽኑ በማስፈጸም ሥራዎቻቸውን በውጤታማነት ለማከናወን ጥረት ማድረግ ሲጀምሩ አንድነታቸውንና ወንድማማችነታቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ ማጽናት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን በማመን ተናበውና ተመካክረው ዘመነ ሢመታቸውን በስኬት ለመፈጸም ቆርጠው ተነሱ።
ይህንንም ለማድረግ በዕቅድ ላይ የተመሠረተ የትኩረት አቅጣጫን ነድፈው ዕቅዳቸውን ለማሳካት የሚያስችል የሥራ ኃላፋዎች ዝውውርና ምደባን በማድረግ የሚከተሉትን ጉዳዮች ለማሳካት በሙሉ ኃላፊነት ወደ ሥራ ሲገቡ መንፈሳዊ፣አስተዳደራዊና ልማታዊ የሥራ ዘርፎችን በውጤታማነት ለማከናወን የረጅም ጊዜ ልምዳቸው፣የመሪነት አቅማቸውና የማስፈጸም ብቃታቸውን በሚገባ ተጠቅመዋል።
በዚህም መሰረት ባሳለፍነው አንድ ዓመት ውስጥ በቤተክርስቲያናችን ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ውጤት ማስመዝገብ ቻሉ።
በመሆኑም በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አመራር ሰጪነትና ከፍተኛ ክትትል ከግንቦት እስከ ግንቦት ምን ውጤቶች ተመዘገቡ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ እንችል ዘንድ ጥቂቶቹን ለማሳያነት ያህል እንደሚከተለው እናቀርባለን ።
1.ኛ. ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋትና ለማጠናከር የሚያስችሉ በርካታ የውይይት መድረኮች ፣የሰባኪያነ ወንጌልን አቅም ሊገነቡ የሚችሉ ሥልጠናዎች፣የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ አገልግሎትን በማኅበራዊ ሚዲያ የማስፋፋት ሥራዎች ፣ለበርካታ ዓመታት ሳይሰበሰብ የቀረውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት አንድ ፐረሰንት ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብም የመምሪያውን ገቢ የማሳደግና በበጀት እጥረት ምክንያት አገልግሎቱ እንቅፋት እንዳይገጥመው የማድረግ ሥራ፣ የስብከተ ወንጌል ስምሪትና የመምሪያውን ሥራ የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ ልዩልዩ ጥናቶችም ተደርገዋል።በመደረግም ላይ ይገኛሉ።
በሸገር ከተማና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ አህጉገረ ስብከት ደረጃ በብፁዕነታቸው አመራር ሰጪነት የተቋቋመው ወጣትነት ለቤተክርስቲያን በተሰኘው ማኅበር አማካኝነትም ታላላቅ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብሮችም ተካሒደዋል።
በአጠቃላይ በስብከተ ወንጌል ዘርፍ የተከናወኑና በመከናወን ላይ የሚገኙ ስኬታማ ሥራዎች በዘርፉ ቤተክርስቲያን የበለጠ ውጤታማ ሥራን ማከናወን እንድትችል የሚያደርጋት ነው።
2.ኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅትን አሠራር ማዘመን ይቻል ዘንድ ብፁዕነታቸው የሰጡትን አመራር ተከትሎ ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል። በዚህም የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ ዘመናዊና ዲጃታል እንዲደረግ፣ድርጅቱ የራሱ የሆነ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲኖረውና በድርጅቱ የሚሠሩ ሥራዎች ሁሉ በየጊዜውም ውጤታቸው ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ ተደርጓል፣የድርጅቱን ገቢ የሚጎዱና ግለሰቦችን የሚጠቅሙ የኪራይ አሰባሰብ ሥርዓቶችን በማስወገድ የቤተ ክርርቲያን ገቢ በአግባቡ የሚሰበሰብበት ሥርዓት ተፈጥሯል፣ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር የድርጅቱ ቢሮ በዘመናዊና የቤተክረስቲያናችንን ክብር በሚመጥን መልኩ እንዲታደስ ተደርጓል።በአጠቃላይ በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ መነቃቃትና የሥራ ተነሳሽነት እንዲጎለብት፣አሠራሩ እንዲዘምንና ውጤታማ ተቋም እንዲሆን የማድረግ ሥራ በማከናወን ድርጅቱን ግንባር ቀደም የቤተክርስቲያናችን የልማት ተቋም ማድረግ ተችሏል።
3.ኛ እጅግ በጣም ለበርካታ ዓመታት ከዕቅድ፣ከፍላጎትና ከሥርጭት ጋር ሳይጣጣሙ በከፍተኛ ወጪ ታትመው የተከማቹ መጻሕፍቶችን የመለየት፣የማደራጀት፣የማሰባሰብና የማሰራጨት ሥራ መላውን የቤተክህነት ሠራተኛን በማሳተፍ እንዲከናወን በማድረግ መጻሕፍቶቹ በጨረታ ተሸጠው የቤተክርስቲያን ገቢ በአግባቡ እንዲሰበሰብ፣መጻሕፍቱም አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የማድረግ ታሪካዊ ሥራ ተሰርቷል።
4.ኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ታሪኮቿ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎችን፣ልዩልዩ ሃብቶቿን፣የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊና ተቋማዊ ሕልውናን የሚመሰክሩ ማኅደሮች በተበታተነና ለአያያዝ ምቹ ባልሆኑ ሥፍራዎች ተከማችተው ለአደጋ ተጋልጠውና ለመጥፋት ተቃርበው የነበሩ ሲሆን እነዚህን ፋይሎች በሚገባ ተለይተው፣ተደራጅተውና በዘመናዊ መልኩ ወደ ዲጂታል ፋይል ተቀይረው ለታሪክና ለትውልድ እንዲተላለፉ እንዲደረግ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የተሰጠውን መመሪያ ተከትሎ ፋይሎቹን ወደ ዲጂታል የመቀየሩ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። ቀደም ሲል የቤተክርስቲያናችንን አሠራር ወደ ዘመናዊና በICT የተደራጀ እንዲሆን ለማድረግ የተጀመረውን ሥራ ማስቀጠል እንዲቻልም ከፍተኛ ባለሙያዎችን የያዘ ኮሚቴ በማደራጀትም ትርጉም ያለው ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
5.ኛ ለበርካታ ዓመታት ሳይጸዳ የኖረው ለእይታ የማይመቸውና የቤተክርስቲያንን ክብርና ልዕልናን የማይመጥነውን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ቅጽር ጊቢ በሚገባ ጸድቶ፣
አምሮና ተውቦ፣ለዕይታ የሚማርክ፣የቤተክርስቲያንን ክብር የሚመጥን፣የሥራ ተነሳሽነትን የሚፈጥር፣ቅጽረ ጊቢ እንዲሆን ተደርጓል። የቅጽረ ጊቢው ማማር እጅግ በጣም ከፍተኛ በሆነ ወጪ በመገንባት ላይ ለሚገኘው ዘመናዊው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተጨማሪ ውበትን ያጎናጸፈ ሲሆን የዘመናዊ አዳራሽ ግንባታው አፈጻጸምም እስከዛሬ ከነበረው እጅግ በተሻለ ሁኔታና ፍጥነት መከናወን በመቻሉ እነሆ የማጠቃለያ ሥራ ላይ ይገኛል። የግንባታ ሥራው ሙሉበሙሉ ተጠናቆ ሥራ በሚጀምርበት ወቅትም ታላላቅ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብሮችን በማከናወን የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴዎችን ከማስፋፋት ጎን ለጎን ሀገራችን
የምታከናውናቸውን ዓለም ዓቀፋዊ ስብሰባዎችን ጭምር በማስተናገድ የቤተክርስቲያን እና የሀገር ኩራት የሚሆን ተቋም በመሆን እንደሚያገለግል ይታመናል።
6.ኛ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ በነበሩ ጊዜ በተለምዶ አሮጌው ቄራ በመባል በሚታወቀው ቦታ ላይ በመሠራት ላይ የነበሩት ሁለት ግዙፋን ሁለገብ ሕንጻዎችም ትኩረት ሰጥቶ ለውጤት የሚያበቃቸው አጥተው ለበርካታ ዓመታት የቤተክርስቲያን ሀብት ሲባክንባቸው ከርመው በአሁኑ ወቅት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ በመሆን ዳግም ወደ አመራርነት ሲመጡ በልዩ ትኩረትና በፍጥነት እንዲሠሩ በመደረጋቸው እነሆ በአራት መቶ ሰማኒያ ካሬ ላይ ያረፈው ሕንጻ ግንባታ ተጠናቆ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት በደማቅ ሥነሥርዓት ለምርቃት ሲበቃ በአንድ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ሕንጻ ግንባታ ደግሞ የግንባታ ሥራው በመፋጠን ላይ ይገኛል። ይ ቀ ጥ ላ ል …
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
ግንቦት ፳፻ ፲ወ፰ ዓ.ም
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ።

ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት እንደሚከተለው ነው፦

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

‹‹ተዘከሩ መቁሓነ ዘከመ ተሞቃሕክሙ ምስሌሆሙ ወእለ ተሣቀዩ ከመ ዘሀለውክሙ በሥጋክሙ፡-
ከእነርሱ ጋር አብራችኋቸው እንደታሰራችሁ ሆናችሁ እስረኞችን ዐስቡ፤ መከራ የጸናባቸውንም በሥጋችሁ ከእነርሱ ጋር እንዳላችሁ ሆናችሁ ዐስቡ››
(ዕብ. 13፡3)

እውነተኛ እምነትም ሆነ ጤናማ አመለካከት የሚመዘነው መከራ ስለሚቀበሉ ሰዎች ሰምቶና አይቶ በዝምታ ባለማለፍ፤ ይልቁንም በእነርሱ ሕመም ውስጥ ራስን በማስገባት በሚሰማው ጥልቅ ኀዘን እና በሚደረገው ድጋፍ ነው፡፡ ይልቁንም በዚች ዓለም የምንኖር ለችግርና ለመከራ ቅርብ እንደመሆናችን የታሰሩትን መጎብኘት፣ የተገፉትን ማጽናናት፣ በስደት ምድር ላይ ሆነው በሞት ፍርድ የሚጨነቁትን ወገኖች ስቃይም እንደራሳችን ስቃይ በመቁጠር ስለእነርሱ ድምፅ መሆንና ማዘን ስንችል በሰማያዊው መንግሥት የማይጠፋ የጽድቅ ዋጋን እናከማቻለን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!

እረኛ በበረት ውስጥ ያለችው አንዲት በግ ስትጠፋ ወይም ለአደጋ ስትጋለጥ ዝም ብሎ እንደማያይ ሁሉ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ ምድር በሞት ጥላ ሥር ሆነው ‹‹የፍትሕ ያለህ›› እያሉ የሚጮኹ፤ በጭንቀት ቀናትን የሚቆጥሩና ድምፅ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን የተሻለ ኑሮ እናገኛለን ብለው በተሰደዱበት ሀገር ሕይወታቸው በጅምላ ሊቀጠፍ እንደሆነ መረጃውን ከልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን የተገነዘብን በመሆኑ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጠቀሜታው የሰው ልጆችን ሕይወት ለመጠበቅ ነውና የኢትዮጵያ መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ ከሚገኙ ከሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር በግፍ የተፈረደባቸው ልጆቻችን የሞት ፍርድ እንዲነሳላቸውና ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበት መንገድ ይመቻች ዘንድ የተጀመሩ ሥራዎች ልዩ ትኩረት እንዲሰጥባቸው፤ ወገኖቻችንም በቋንቋ እጥረትና በሕግ አማካሪ እጦት ለሞት እንዳይዳረጉ ከአደራ ጭምር እናሳስባለን ፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጅ የሰጠው ታላቅ ስጦታ ሕይወት ነው፤ “አትግደል” የሚለው ሕግም በማንኛውም ምድርና ቋንቋ የሚሠራ ሲሆን ፍርድ ያለ ምሕረት ከሆነ አምላካዊ ቁጣን ይጋብዛልና የሳዑዲ ባለሥልጣናት የሁለቱን ሀገራት የቆየ ታሪክና ወዳጅነት አስበው፣ በሞት ፍርድ ጥላ ሥር ላሉት ወገኖቻችን ምሕረትን እንዲያደርጉ፣ ቅጣቱንም ወደ እስራት እንዲቀይሩ በአባታዊ ርኅራኄ እንጠይቃለን ፡፡

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችም በማያውቁት ቋንቋ እንዲሁም ባልተረዱት የሕግ ሂደት ሞት የተፈረደባቸውን ወገኖች ስቃይ ተመልክተው የፍትሕ መዛባትን እንዲቃወሙና የንጹሐንን ነፍስ እንዲታደጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

በመጨረሻም፣ ማንኛውም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሰው ሕይወቱ ሊጠፋ አይገባምና ኦርቶዶክሳውያን ልጆቻችን የክርስትናችን አንዱ መገለጫ የአንደኛው ወገን ሕመምን በጋራ መካፈል እንደሆነ ተረድታችሁ ወደ ፈጣሪያችን በጸሎት እንድትማጸኑ፤ መላው ኢትዮጵያውያንም ለመፍትሔው የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ስንል አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን።

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን።

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የአዳማ ሰቀቀሎ ደብረ ገነት ቅዱስ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤቱ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከበረ

ግንቦት ፪ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም አዳማ — በአዳማ ከተማ በውብ የኪነ-ሕንጻ ጥበብ የታነጸው የአዳማ ሰቀቀሎ ደብረ ገነት ቅዱስ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን አዲሱ ሕንጻ ቤተ መቅደስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን በተገኙበት በዛሬው ዕለት ቅዳሴ ቤቱ በታላቅ መንፈሳዊ ድምቀት ተከብሯል።
ትላንት ግንቦት ፩ ቀን በብፁዕ አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ (የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና ሥራ አመራር መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ቋሚ አባልና የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ተቋማት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ) እንዲሁም በብፁዕ አቡነ ጢሞቲዎስ (የዳውሮ፣ ኮንታ እና የከንባታ ሀላባ ጠንባሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ቋሚ አባል) ቡራኬ ተባርኮ የተመረቀው ይህ ቤተ መቅደስ በዛሬው ዕለት ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል።
በክብረ በዓሉ ላይ በመገኘት ቡራኬና ትምህርት የሰጡት ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ምእመናን የእግዚአብሔርን ቤት በመሥራታቸው ያለቸውን ደስታ ገልጸው የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል፦
“ዛሬ አሳንጻችሁ የወልደ እግዚአብሔርን ሥጋውን የምንበላበት፣ ደሙን የምንጠጣበት የእግዚአብሔርን ቤት ሠርታችኋል። በዚህ ቤተ መቅደስ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያም ፣ ቅዱሳን መላእክትን፣ ጻድቃንና ሰማዕታትን እናገኝባቸዋለን። ይህ ሥፍራ ያዘነ የሚጽናናበት፣ የደከመ የሚበረታበት፣ ያጣ የሚያገኝበትና የተቸገረ ከችግሩ የሚላቀቅበት ዘላለማዊ ቤት ነው” ብለዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም፣ እግዚአብሔር ከምእመናን የሚፈልገው በዋናነት ራሳቸውን እንደሆነ ገልጸው፤ ምእመናን በንስሓ ሕይወት በመመላለስ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ በበኩላቸው፣ በሀገረ ስብከታቸው እየተከናወኑ ያሉ የቤተ ክርስቲያን የልማት ሥራዎችን በማድነቅ ጥልቅ የሆነ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክትና ቃለ ምዕዳን አስተላልፈዋል።
“ለሁሉም ነገር መሠረቱ ሕዝብ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን በሰላም፣ በአንድነትና በመቻቻል ተሳስሮ የኖረ ድንቅ ሕዝብ ነው። ይህ ሕዝብ ቤተ ክርስቲያኑን ሠርቶ በማስፈጸም ረገድ ያለውን ጥንካሬ የምናደንቀው ቢሆንም፤ ከምንም በላይ ግን ይህንን ለዘመናት የቆየ ሰላሙን፣ አንድነቱንና መቻቻሉን ጠብቆ ማስቀጠል አለበት” ብለዋል።
አክለውም አዳማ ከተማ የፍቅርና የአንድነት ከተማ መሆኗን ጠቅሰው፣ ከልጅ እስከ አዋቂ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ለደከሙ ሁሉ “እንኳን ደስ አላችሁ” በማለት በአባታዊ ቡራኬና ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል።
በዕለቱ የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ኃላፊ መጋቤ ሐዲስ ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ተስፋ፣ በብፁዕነታቸው መልካም ፈቃድ “የማትፈርስ መቅደስ” በሚል ርዕስ ጥልቅ የሆነ የወንጌል ትምህርት አስተምረዋል። መርሐ ግብሩን ደግሞ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሣሕል ቀሲስ ነጋሽ ሀብተ ወልድ በብቃት መርተውታል።
በመጨረሻም ሕንጻ ቤተ መቅደሱ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው እንዲደርስ በእውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና በገንዘባቸው ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉ ምእመናንና ባለሙያዎች ዕውቅናና ምስጋና ተሰጥቷል።
የሐመረ ተዋሕዶ ሚዲያ ማጠቃለያ ዕይታ ፤ ይህ ውብ ሕንጻ ቤተ መቅደስ ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት ለፍጻሜ መብቃቱ፣ ከመንፈሳዊ ጥንካሬ ባለፈ የታላቅ አመራርና የተናበበ ሥራ ውጤት መሆኑን ነው።
​በተለይም የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ቀሲስ ታፈሰ ተስፋዬ፣ ግንባታው ከመሠረት ድንጋይ ጀምሮ እዚህ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ የነበራቸው ሚና የሚደነቅ ነው። አስተዳዳሪው ከዲቁና የክህነት ማዕረግ ጀምሮ በዚህ ደብር ውስጥ በማገልገልና አሁን ላይም በኃላፊነት በመምራት፣ የአዳማ ከተማን ምእመናን በአንድነት በማስተባበር ያሳዩት ቁርጠኝነት ለቤተ መቅደሱ ግንባታ መሳካት ዋነኛ ምሰሶ ሆኖ ተገኝቷል።
​ይህ ክስተት የሚያሳየው፣ አንጋፋ አባቶች ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር በፍቅርና በትሕትና ሲሰለፉ፣ እንደዚህ ያሉ ታላላቅ የልማት ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማከናወን እንደሚቻል ነው። ሚዲያችን እንደተመለከተው፤ የአስተዳዳሪው የረጅም ዘመን አገልግሎትና ከምእመናን ጋር የገነቡት ጥንካሬ፣ ዛሬ ለታየው ታላቅ መንፈሳዊ ድልና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ክብር መጎናጸፊያ ሆኗል። ይህም ለሌሎች አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችም ትልቅ ትምህርትና አርአያ የሚሆን ተግባር መሆኑን ሐመረ ተዋሕዶ ሚዲያ ባደረገው ዳሰሳ አረጋግጧል።©ሐመረ ተዋሕዶ ሚዲያ

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በቃሊቲ አካባቢ ለበጎ አድራጎት ሥራ ከ23 ዓመት በፊት ያስገነቡትን Gተ1 የመኖሪያ ሕንጻ ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማኅበር በስጦታ አበረከቱ

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የዋሽንግተን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት የስጦታ መርሐ ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል።
ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ለበጎ አድራጎተት እንዲውል የሕንጻ ቁጥሩ 982 የሆነውንና በግል ገንዘባቸው በ544 ካሬ ሜትር ቦታ ያረፈ ሕንጻ በመገንባት ለዚሁ ዓላማ እንዲውል አድርገዋል።
ሕንጻው ያረፈበት ቦታ 240 ካሬ ሜትር ሲሆን በግንባታ ወቅት የወጣበት ወጪ ከ3ሚሊዮን በላይ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ባለው የገበያ ዋጋ ከ120 ሚሊዮን በላይ ይገመታል።ሕንጻው ከተገነባ 23 ዓመታትን ማስቆጠሩ ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ አቶ አምሓ ይልማ ባቀረቡት መልእክት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ሕንጻውን በገነቡበት ወቅት ያስተላለፉትን በሕግ ፊት የሚጸና ተብሎ የተመዘገበውን የኑዛዜ ሰነድ በጽሑፍ አቅርበውታል።
ቤቱን ለመቄዶንያ አረጋውያንና አእምሮ መርጃ ማዕከል ለማስተላለፍ ከቤተ ሰብ ጭምር ኮሚቴ (ቦርድ) ተቋቁሟል ተብሏል።
በመቀጠልም በስጦታ አድራጊ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልና በስጦታ ተቀባይ መቄዶንያ የውል ስምምነት ሰነድ እና ካርታ ርክክብ ተፈጽሟል።
ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በስጦታ መርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት እግዚአብሔር የሰጠኝን ቤት ለእግዚአብሔር አስረክቤያለሁ ብለዋል። ብፁዕነታቸው ጨምረው እንደገለጹት 19 ዓመት የቤቱ ኪራይ ለበጎ አገልግሎት ውሏል ብለዋል።
መስጠት የማይፈልጉ ኃይሎች የእኔን ስጦታ ሲተቹ ሰምቻለሁ።
ይህ ግን አግባብነት የለውም ብለዋል። ብፁዕነታቸው እኔ የሚቆጠር ንብረት የለኝም ያሉ ሲሆን በመጨረሻም ካርታውንና የቤቱን ቁልፍ የመቄዶንያ መሥራች ብኒያም በለጠ ተረክበው የምስጋና መልእክት አስተላልፈዋል።
ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል 18 ዓመታቸው ስለመነኮሱ እግዚአብሔር የመቄዶንያ መሥራች ብንያም በለጠ የጠራቸው አባት መሆናቸውን እናምናለን። ስጦታቸውን የሚያጣጥሉ ኃይሎች መፈጠራቸው አሳዝኖናል ብለዋል።
ቀድሞም የቤት ኪራዩን ሜቄዶንያ ሲጠቀምበት የቆየ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ቤቱ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል 58ኛ መቄዶንያ ቅርንጫፍ እንዲባል ጠይቀዋል።
በመቄዶንያ ታሪክ ትልቁ ስጦታ ይህ ነው በማለት የመቄዶንያ መሥራቹ ብኒያም በለጠ ተናግረዋል።
በመቀጠልም የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ስለስጦታው አርአያነት ያለው ነው በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የመቄዶንያ አረጋውያንና አእምሮ ሕሙማን ማዕከል ተረጅዎችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ አባታዊ ትምህርት የሰጡ ሲሆን ብፁዕነታቸው በሰጡት ትምህርት የትንሣኤው በኩር የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኔ ተማሩ በማለት ያስተማረውን ትምህርት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በተግባር አውለውታል ብለዋል።
ብፁዕነታቸው ራሳቸውን በመስጠት ትልቁን መሰናከል አልፈዋል ብለዋል። ዛሬ ያጣነው የሚሠራ እንጂ የሚያወራ አይደለም ሲሉ መልዕታቸውን አጠቃለዋል።
በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ኤልያስ የኖርዲክ ሀገራት እና የግሪክ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ የመጨረሻ ትምህርትና ጸሎት መርሐ ግብሩ ተጠናቋል።©Eotc tv.

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሓዱ ኣምላክ ኣሜን!
ብፁዕ ኣቡነ ሳዊሮስ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ ኣስኪያጅ፤
ብፁዕ ኣቡነ ዲዮስቆሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፤
ብፁዕ ኣቡነ ሕርያቆስ
የኣዲስ ኣበባ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዓን ኣበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት፣
በኣጠቃላይ በዚህ ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልኣተ ጉባኤ የተገኛችሁ በሙሉ፦
ማሕየዊት በምትሆን ሞቱ ሰማያውያንና ምድራውያንን ያስታረቀ፣ በቅድስት ትንሣኤውም የሙታንን ሕይወት በተስፋ ያለመለመ ጌታችን፣ ኣምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እንኳን ለዓመታዊው የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልኣተ ጉባኤ ኣደረሰን ኣደረሳችሁ!
“እስመ ተዋለጠ እግዚአብሔር ዓለመ በክርስቶስ ኣናኅስዮ ኃጢኣቶሙ ወኢነጺሮ ጌጋዮሙ፤ ወረሰየ ላዕሌነ ቃለ ሥምረቱ፤ ወወሃበነ መልእክተ ሣህሉ፡- እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና በደላቸውን ኣይቈጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል ኣኖረ” (2ቆሮ. 5፥19)።
የእግዚአብሔርም ልጅ፣ የሰውም ልጅ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሰብእነት ሲገለጽ ግልጽ የሆነ ዓላማና ግብ እንደነበረው ቅዱስ መጽሓፍ ይነግረናል፤ እሱም በሰማይም፣ በምድርም ያሉትን በሙሉ ማስታረቅ፣ ማገናኘትና ኣንድ ማድረግ ነበረ፤
ጌታችን ይህንን ሲያደርግ ሰማያውያኑንና ምድራውያኑን የለያየው ምክንያት በማስወገድ ነው፤ የመለያየቱ ምክንያት ክፉ ኅሊና ኣምጦ የወለደው በደልና እሱን ተከትሎ የተከሠተው ኃጢኣት ነበረ፤ በኃጢኣት ምክንያት የገባው ሞት ደግሞ የቅጣቱ ማሳያ ፍርድ ነበረ።
የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በፈጸሙት ስሕተት መነሻነት ምድርንና ምድራውያንን ለከባድ ቅጣትና መርገም የዳረገው ይህ መለያየት ለሰማያውያኑም ተርፎኣል፤
ምክንያቱም መለያየቱ በእግዚአብሔርና በሰው፣ በመላእክትና በሰው፣ በሰውና በሰው፣ በነፍስና በሥጋ ጭምር የጥል ግድግዳን ገንብቶ እስከ ክርስቶስ ዕለተ ስቅለት መዝለቁን በቅዱስ መጽሓፍ የምናውቀው ስለሆነ ማለት ነው።
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት!
ቀዳማዊና ዘላለማዊ የሆነው ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ሰብእናችንን ተዋሕዶ በዚህ ዓለም የተገለጸው ሰማያውያንንና ምድራውያንን የለያየው የጥል ግድግዳን ለማፈራረስ ነው፤
ለመለያየት ምክንያት የሆነችውን ኃጢኣት በሰውነቱ በመቅጣት የሕግን ትእዛዝ ከፈጸመ በኋላ የዕርቁን ተግባር በወሳኝ መልኩ ኣከናውኖታል፤
በክርስቶስ ቤዛነት የሆነው ይህ ዕርቅ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተወደደ ነበረና እሱ ራሱ በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ኣስታረቀ፤
ለዚህም ነው ተበዳይ እሱ፣ ቤዛዊ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው እሱ፣ ኣስታራቂ እሱ፣ ታራቂ እሱ ሆኖ የምናገኘው፤ ለሱ የሚሳነው ነገር የለምና ለኛ ግር የሚል ቢመስልም ለሱ ቀላል ነበረ።
በዚህ የዕርቅ ተግባር ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሰውና ሰው፣ ነፍስና ሥጋ ታርቀው በይፋ ተገናኙ፤ በኅብረትና በኣንድነትም መኖር ቻሉ፤ በቀኙ ለተሰቀለው ሽፍታ “ዛሬውኑ ከኔ ጋር በገነት ትኖራለህ” የሚለው ቃለ ምሕረትና “ኣባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ ኣደራ እሰጣለሁ” የሚለው ቃለ ኣማሕፅኖ የዕርቁ፣ የግንኙነቱና የኣንድነቱ ማሳያ ኣስረጅ ናቸው።
ስቅለተ ክርስቶስ ነፍሶቻችን ወደ ግዞት ቤት ሳይሆን ወደ ገነት እንዲገቡ፣ የሚቀበላቸውም ራሱ እግዚአብሔር እንዲሆን ያስቻለ ታላቅ መለኮታዊ ፍጻሜ ነው፤
እኛ “ክርስቶስ መድኃኒታችን ነው፤ ኣድኖናል” ብለን በልበ ሙሉነት የምንመሰክረው፣ እሱም “ሰላሜን ሰጠኋችሁ” ብሎ የሚያረጋጋን በመሰቀሉ ይህንን ውጤት ስላስገኘልን ነው።
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት!
የድኅነታችንና የሰላማችን መሠረት የሆኑትን የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ለዓለም ማኅበረ ሰብ የማብሰርና የማሥረጽ ተግባር የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቍጥር ኣንድ ተልእኮ ነው፤
ነገረ ሞቱና ነገረ ትንሣኤው በኣስተውሎት፣ በጥልቀትና በተመሥጦ ስናስተምር በውስጡ የምናገኘው የዕርቅ፣ የሰላምና የኣንድነት ምስጢር ነው፤
እንደ እውነቱ ከሆነ እኛ የክርስቶስ መልእክተኞች እንደ ቃሉ ራሳችንን ክደን በሚጠበቀው መጠን ተልእኮኣችንን መወጣት ብንችል ኖሮ፣ ኣሁን በዓለማችን የተፈጠረው መለያየትና ግጭት ኣይኖርም ነበር፤
ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባንችልም በእጅጉ መቀነስና ዓቅሙን ማዳከም እንችል ነበር፤ ነገር ግን ተልእኮኣችንን በኣግባቡ ኣለመወጣት ኣንድ ነገር ሆኖ የዓለሙ መሳሪያ ሆነን መገኘታችን “በዕንቅርት ላይ…” ሆኖ ይስተዋላል።
ይሁንና ኣሁንም ሕዝቡን ወደ ኣንድነት፣ ወደ ፍቅር፣ ወደ ሰላም፣ ወደ ዘላቂ የጋራ ጥቅምና ወደ ፈሪሐ እግዚአብሔር ማምጣት የጉባኤያችን ዓቢይ ተግባር ሊሆን ይገባል፤ እነዚህ ካሉ የምናጣውም ሆነ የሚያመልጠን የለምና ነው፤
ሃገርን በኃላፊነት ተረክባችሁ በላዕላዊ፣ በማእከላዊና በታሕታዊ መዋቅር የምትገኙ፣ እንደዚሁም ኣማራጭ ሓሳብ ኣለን ብላችሁ የምትንቀሳቀሱ ልኂቃነ ሃገር ፣ ሁላችሁም እግዚአብሔርን ከሚያውቅ፣ ከሚያመልክና ከሚፈራ ሕዝብ የተገኛችሁ ናችሁና በልባችሁ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ድምፁንም ስሙ፤ የሱ ገንዘብ በሆኑ ፍጡራንም ኣትጨክኑ፤ ሰውን መያዝ የሚቻለው ኅሊናን በመርታት እንጂ በሌላ ኣይደለምና፣
የሕዝቡን ፍላጎትና የልብ ትርታ በሚገባ ኣዳምጡ፤ ሕዝቡ የሚፈልገው በኣንድነትና በእኩልነት መኖር፣ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ፍትሕን ማስፈን፣ ለኑሮው የሚበቃ ምጣኔ ሃብትን ማግኘት፣ የእምነት ነጻነትና እኩልነት መረጋገጥ የመሳሰሉት ናቸው።
ሕዝቡ እነዚህ ከተሟሉለት ተደመጠ ማለት ነው፤ ከተደመጠ ደግሞ እሱም በበኩሉ ያደምጣል፤ ይከተላልም፤
ስለሆነም ለሁሉም ልጆቻችንና ወገኖቻችን የምናስተላልፈው ወቅታዊ ጥሪ ሁሉንም ችግሮቻችን በሰላምና በሰላም ብቻ ለመፍታት ተባበሩ የሚል ነው፤ ከዚህ ውጭ የሚደረገው ኣማራጭ ሁሉ ለዘላቂ ሰላማችን ኣይበጅም እንላለን።
በመጨረሻም፦
በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ከበዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ ኣምስተኛው ቀን የሚካሄደው ዓመታዊው የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልኣተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተጀመረ መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑና ለመላው ኢትዮጵያውያን እናበስራለን!!!
እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሓት ለእግዚአብሔር፤
አሜን!!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘኣኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ
ተክለ ሃይማኖት፤
ሚያዝያ 28 ቀን 2018 ዓ.ም
ኣዲስ ኣበባ – ኢትዮጵያ

የ፳፻ ፲ወ፰ ዓ/ም የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የጸሎት መርሐ ግብር በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተከናወነ

ሚያዚያ ፳፯ ቀን ፳፻፲ወ፰ ዓ/ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ፳፻ ፲ወ፰ ዓ/ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመክፈቻ ጸሎት መርሐ ግብር በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተከናወነ።
በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በተከናወነው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆርስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያውና የድርጅቶቹ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የግንቦት ፳፻ ፲ወ፰ ዓ/ም የቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ በቋሚ ሲኖዶስ ተዘጋጅተው በአጀንዳ አሪቃቂ ኮሚቴ ታይተውና በምልዓተ ጉባኤ ተመርምረው በሚጸድቁ አጀንዳዎች ዙሪያ በጥልቀት በመወያየት ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል።