ክፍል ሁለት …..” ከግንቦት እስከ ግንቦት ” እንደሚከተለው ይቀርባል
ባለፈው “ከግንቦት እስከ ግንቦት” ዝግጅታችን በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ዘመነ ሢመት የተከናወኑ ዋናዋና ሥራዎችን በመጠኑ የዳሰስንበትን ዘገባ ለንባብ ማቅረባችን ይታወሳል።ቀጣዩን ክፍል እንደሚከተለው እናቀርባለን፦
7.ኛ ቤተክርስቲያን በመጪው ዘመን መንፈሳዊ አገልግሎቷን ለማሳለጥ፣ ቀደምት አባቶቻችን ጥለውልን በሄዱት ይዞታዎች ላይ ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ ሠርታ ለማስተላለፍ እንዲሁም በከተማችን የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍና በከተማችን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማበርከት በሚያስችላት መልኩ በፒያሳና በአራት ኪሉ በብዙ ቢሊየን ብር ወጪ ግዙፋን ሁለገብ ሕንጻዎችን ለመገንባት የሚያስችላትን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በሚገባ ካጠናቀቀች በኋላ ወደ ግንባታ ሥራ በመግባት በፍጥነት የግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች።ይህ የግንባታ ሥራ ጊዜያዊ የሥራ ዕድልን ከመፍጠር ባለፈ ተጨማሪ ቋሚ የሥራ ዕድልን በመፍጠር ዜጎችን የሚጠቅም እንደሚሆንም ይታመናል።ይህንን ውጤታማ ሥራ በሚገባ በመምራት ፣በማደራጀትና በመቆጣጠር ረገድም ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ስኬታማ ሥራ እየሠሩ ነው።
8ኛ ባለፈው ዐንድ ዓመት ውስጥ በቤተክርስቲያናችን ዋናዋና መምሪያዎች የተከናወኑት የለውጥና የሕዳሴ ሥራዎች ለተቋሙ ሁለንተናዊ ዕድገትና መስፋፋት ጉልህ አስተዋጽኦን የሚያበረክቱ ከመሆን ባለፈ የቤተክርስቲያናችን ቁልፍ ሥራ የሆነውን የስብከተ ወንጌል መስፋፋትና መጠናከርን ዕውን ከማድረግ ባሻገር የመምሪያውን ሥራ በሚደግፉ ክፍሎች ላይ ተጨባጭ ለውጥ የተመዘገበበትም ነበር።
ከእነዚህ ክፍሎች መካከልም ኢ/ኦ/ቲ/ሲ ቴሌቪዥን አንዱና ዋነኛው ነው።ድርጅቱ በተለይም በሁለቱ ብፁዓን አባቶች ዘመነ ሢመት ከፍተኛ መነቃቃት ከታየባቸው የቤተክርስቲያናችን ተቋማት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ሲሆን የፕሮግራም ይዘቶች መሻሻል፣የዜናና የፕሮግራም አቀራረቦች ዘመኑን የሚመጥኑ እንዲሆኑ መደረጉ፣ዜናዎች በመልክና በይዘታቸው ተለይተው እንዲሰራጩ መደረጉ፣ወቅታዊ ፕሮግራሞች ወቅታቸውን ጠብቀው እንዲለቀቁ መደረጉ፣የቀጥታ ሥርጭቶችና አስፈላጊ መረጃዎች በፍጥነት እንዲሰራጩ መደረጉ ወዘተ…ድርጅቱ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በስኬት ካከናወናቸው በርካታ ውጤቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
እነዚህ ስኬቶች ሊመዘገቡ የቻሉትም የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ፣የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ፣የድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች፣የመርሐ ግብር አዘጋጆችና ጋዜጠኞች ተናበውና ዕቅድ አውጥተው በመሥራታቸው እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አመራር፣ክትትልና ድጋፍ ቀዳሚውን ድርሻ የሚወስድ በመሆኑ ለለውጡ መመዝገብ ትልቁን ድርሻ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የሚወስዱት ይሆናል።ይህም የብፁዕነታቸውን የመሪነት ጥበብና የለውጥ ሰውነት የሚገልጽ በመሆኑ ለለውጡ መመዝገብ ብፁዕነታቸው የከፈሉ መስዋዕትነት ፍሬ እንዲያፈራ በማድረግ ረገድ በትጋት በመሥራት ላይ የሚገኙትን የድርጅቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ቁርጠኝነትና የመሪነት ጥበብ ዕውቅና መስጠትም የሚገባ ይሆናል።
9.ኛ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በዘመነ ሢመታቸው ትልቅ ውጤት ካስመዘገቡባቸው ተቋማት መካከል የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያና የገዳማት አስተዳደር መምሪያዎች ተጠቃሾች ሲሆኑ በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በኩል የሰበካ ጉባኤ ስምሪት መደረጉ፣የተሳካ ዓለምዓቀፍ የሰበካ ጉባኤ መካሔዱ፣ልዩልዩ ሥልጠናዎች መሰጠታቸው፣ወዘተ ተጠቃሽ የብፁዕነታቸው ዘመነ ሢመት ውጤቶች በመሆን በታሪክ ተመዝግበዋል።በሌላ በኩል የገዳማት አስተዳደር መምሪያም ተደጋጋሚ ሥልጠናዎችን ለገዳማት አበ ምኔቶች፣ለገዳማውያንና ለሚመለከታቸው ሁሉ በመስጠት፣በገዳማት አስተዳደር በኩል ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ ያደረገ ሲሆን በገዳማት አስተዳደር መምሪያ በኩል ከፍተኛ መነቃቃትና ተጨባጭ የሥራ ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል።ለዚህ ስኬትም የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ቆራጥ አመራር የመምሪያ ኃላፊው ለሥራው ትኩረት መስጠትና በብቃት የመምራት ክህሎት ታክሎበት በመምሪያው ተጨባጭ ለውጥ ማምጣትና በመምሪያውና በገዳማት መካከል ተገቢ የሆነ የሥራ ትስስር ፣መነቃቃትና ውጤት መመዝገብ አስችሏል።
10.ኛ ቅድስት ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የምታከብራቸው የአደባባይ በዓላት በደመቀና ባማረ መልኩ እንዲከበሩ በማድረግ ሂደት ውስጥ በየ ዘመናቱ በርካታ ሥራዎች የሚሠሩ እንደሆነና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ በዓላት እንደሆኑም ይታወቃል።እነዚህ በዓላት በዓለም አቀፉ ተቋም በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገቡና የቤተክርስቲያናችን ዐበይት በዓላት በመሆናቸው በልዩ ትኩረትና በድምቀት መከበር እንዳለባቸው በጽኑ የሚገነዘቡት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በዓላቶቹን በተቻለ አቅም በከፍተኛ ድምቀት፣ወጪ ቀናሽ በሆነ ስልትና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማክበር ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ሁለቱ የአደባባይ በዓላቶቻችን ማለትም የመስቀልና የጥምቀት በዓላት እጅግ ባማረና በደመቀ መልኩ ተከብረው መዋል እንዲችሉ አድርገዋል።
በተለይም የአደባባይ በዓላቶቹ ወጪዎች በከተማ አስተዳደሩ በኩል እንዲሸፈኑ፣ተገቢው የጸጥታ ሥራ እንዲሠራ፣የበዓል ዝግጁቱ የቤተክርስቲያንን ሃይማኖታዊ ትውፊት በጠበቀ መልኩ እንዲከናወንና የአከባበር መርሐ ግብሩም የተዋጣለት እንዲሆን በማድረግ ረገድ ብፁዕነታቸው የሰጡት አመራር በዓላቱ የአገራችንን የሃይማኖት መሰረትነትና የቤተክርስቲያንንና የመንግሥትን አስፈላጊ ግንኙነቶችን በማጠንከር ረገድ ውጤታማ በመሆናቸው የ2018 ዓ.ም የመስቀልና የጥምቀት በዓላት በተዋቡ፣በተረጋጉና በደመቁ ሁኔታ ተከብረው መዋል ይችሉ ዘንድ ብፁዕነታቸው የሚጠበቅባቸውን የመሪነት ሚና በሚገባ ተወጥተዋል።
11.ኛ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በዘመነ ሢመታቸው ከሠሯቸው በርካታና ውጤታማ ሥራዎች መካከል እጅግ አስገራሚና ልዩ ሥራ ተደርጎ በታሪክ መዝገብ ከሚሰፍሩ ሥራዎቻቸው መካከል ተጠቃሽ የሚሆነው የሸገር ሀገረ ስብከት ውጤታማ ሥራቸውና ከአስተዳደራዊ ሥራዎች በተጓዳኝ የሚያከናውኗቸው የመንፈሳዊ አገልግሎቶች ናቸው።
ብፁዕነታቸው በሚገርም ትጋትና ብቃት የአስተዳደራዊና የልማት ሥራዎችን ከመምራት ጎን ለጎን በዓበይት በዓላት፣በአብያተ ክርስቲያናት ምረቃ፣በስብከተ ወንጌል አገልግሎቶች፣ወዘተ
በሀገረ ስብከታቸው በየጊዜው በመገኘት በአስገራሚ ሁኔታ መንፈሳዊውን ዘርፍ በመምራት ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ውጤት አስመዝግበዋል።በተለይም ወጣቱ ትውልድ በስብከተ ወንጌል አማካኝነት፣በቃለ እግዚአብሔር ታንጾ እንዲያድግና የቤተክርስቲያን ተረካቢ እንዲሆን በማድረግ ረገድ እያደረጉት ያለው ጥረትና እያስመዘገቡት ያለው ውጤት የሚያስገርምና የመሪነት ብቃታቸውን የሚያሳይ ነው።
ከዚህ ትጋት ጎን ለጎንም በጎ አድራጊ ምዕመናንን በማስተባበርና ወደ ሥራ በማሰማራት የጠቅላይ ቤተክህነቱንና የሸገር ሀገረ ስብከት ቢሮዎችን የቤተክርስቲያንን ክብርና ልዕልና በሚመጥን መልኩ በማስዋብና ግብዓቶችን በማሟላት የተቋማቱን ክብር ከፍ በደርግ፣በተቋማችን እንድንመካና እንድንደሰት የሚያደርግ ሥራን ሠርተዋል።
12.ኛ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በዘመነ ሢመታቸው ካስመዘገቧቸው በርካታና ስኬታማ ሥራዎች መካከል የቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የዕድሳት ሥራ አንዱ ሲሆን ገዳሙ ለበርካታ ዓመታት ተገቢው የዕድሳት ሥራ ሳይደረግለት መቅረቱን ተከትሎ ወደ መቅደሱ ሳይቀር ዝናብ እየገባ መንፈሳዊ አገልግሎቱን እያወከ ከመቆየቱም በላይ ቅጽር ጊቢውና ሌሎች አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሥፍራዎች ተጎሳቁለው አገልግሎት መስጠት የማይችሉበት ደረጃ ላይ እየደረሱ መሆኑን በመገንዘብ ከገዳሙ የሥራ ኃላፊዎችና ከሚመለከታቸው ጋር ባደረጉት ውይይት በመነሳት ሕንጻ ቤተኮርስቲያኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታድሶ አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ ሥራን በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
በዚህም ሕንጻ ቤተኮርስቲያኑን ለማደስና ወደ አገልግሎት ለመመለሰ የሚያስችል ሥራን በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚገባ በመሥራት በመጪው ሐምሌ ወር ቤተክርስቲያኑ እንዲመረቅና ታቦተ ሕጉ ወደ ቤተክርስቲያኑ እንዲመለስ የሰጡትን መመሪያ ተከትሎ የቤተክርስቲያኑ የዕድሳት ሥራ በፍጥነት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን በመጪው ወር መጀመሪያ ላይ ሥራው ተጠናቆ ርክክብ የሚፈጸም ይሆናል።ይህም የብፁዕነታቸው የአመራርና የሥራ ውጤት በመሆን በታሪክ መዝገብ በደማቅ ቀለም የሚመዘገብ ይሆናል።
ይ ቀ ጥ ላ ል በክፍል ሦስት ዝግጅታችን የቅዲስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤትን የሥራ እንቅስቃሴን፣የቋሚ ሲኖዶስ እና የምልዓተ ጉባኤውን ስብሰባዎች በመዳሰስ የብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊውን “ከግንቦት እስከ ግንቦት”የሥራ ስኬቶችን እና የሁለቱ አባቶችን ዘመነ ሢመት ተግዳሮቶች እንዲሁም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በመዳሰስ የምናቀርብ ይሆናል።ቸር እንሰንብት።