ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቅጣጫ ሰጪነት እየታደሰ የሚገኘውን ዕድሜ ጠገቡን የወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ጎበኙ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካሏት፣ ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳም አንዱ በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሚገኘው ወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ነው። ገዳሙ በ14ኛው ክፍለ ዘመን የተመሠረተ በወንጪ ሐይቅ ደሴት ላይ የሚገኝ ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳም ነው። ገዳሙ ከ800 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን፥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አቅጣጫ ሰጪነት እየታደሰ የሚገኝ በመሆኑ ገዳሙ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎችን በመሳብ ታዋቂ የሥነ ሕይወት (ኢኮ-ቱሪዝም) መዳረሻ ሆኗል።
ግንቦት ፯ ቀን ፳፻፲፰ ዓም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በገዳሙ እየተሠራ ያለውን ልማት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፣ ልማቱንም አድንቀዋል። ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክት ይህ ቦታ በዚህ መልኩ ለምቶ በማየታችን በጣም ነው ደስ ያለን። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ይህን ቦታ በማየታቸው የቀደመውን ታሪክ ትውልዱ እንዲያውቀው በማድረግ እንዲሁም የአብነት ት/ቤት በመክፈት ተተኪ ለመፍጠር መሥራት ትልቅ ሥራ ነው። መሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረትም በአስተባባሪነት ይህን በመሥራታቸው ዕድለኛ ናቸው። በዚህ ዘመን የሚሠሩ ሥራዎች የሚያስደንቁ በመሆናቸው በጣም እናመሰግናለን ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ስለ ወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም አመሠራረት የታሪክ መዛግብት ጠቅሰው ያስረዱት ሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት ገዳሙ በ13ኛው ክፍለ ዘመን በታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተመሠረተ ሲሆን በ15ኛው ክፍለ ዘመን በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን በኋላም በዐፄ ፋሲል እና በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የመልሶ ግንባታ ሥራ እንደተካሄደ ገልጸዋል።
ገዳሙ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡ በርካታ ቅርሶች የያዘ ታሪካዊ ገዳም ነው። ከእነዚህም መካከል ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ያበረከቱት “ገድለ ቂርቆስ” ፣ ዐፄ ፋሲለደስ ያበረከቱት “ዜና ፋሲል” እና ለገዳሙ ያበረከቱት “የጎንደር ደወል” በመባል የሚታወቀው ግዙፍ የቤተ ክርስቲያን ደወል የሚጠቀሱ ናቸው።
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳምና አካባቢው ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሲሆን ፣ የወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርስነቱን ጠብቆ በዘመናዊ ልማት እየተደገፈ ያለ ማራኪ የኢኮ-ቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑ ይታወቃል። ይህም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነትንም ፈጥሯል።
በመጨረሻም የገዳሙን ልማት የጎበኙ ብፁዓን አባቶች ገዳሙን ለማገዝና በአካባቢው የሚኖሩ ልጆችን በማስተማር ተተኪ ለማፍራት በማሰብ በየአህጉረ ስብከታቸው አብነት ት/ቤትና በመንፈሳዊ ኮሌጆች ልጆችን ለማስተማር ቃል ገብተዋል።
©Eotc tv.