የወልዳ ዱካ ቡኦታና ወልዳ ሥላሴ ጠቅላላ ማኅበራት ከኦሮሚያ ክልል በክረምት ወራት የሚያሠለጥኗቸውን መምህራን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የሚሠሩትን ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችንና ሙዚየሙን ጎበኙ፡፡
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ የወልዳ ዱካ ቡኦታና ወልዳ ሥላሴ ጠቅላላ ማኅበራት በፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ ማኅበር ድጋፍ ከኦሮሚያ ክልል በክረምት ወራት የሚያሠለጥኗቸውን መምህራን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የሚሠሩትን ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችንና ሙዚየሙን ጎበኙ፡፡ነሐሴ ፩ ቀን ፳፻፲፰ ዓም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት “እናንተን ከየክፍለ ሀገሩ ጠርቶ ማስተማር፣ ማሠልጠን በጣም ትልቅ ሥራ ነው፤ እዚህ መጥታችሁ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት እንድትጎበኙ የጥንቱንም አሁን የተሠራውን እንድትመለከቱ ስለመጣችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ” ብለዋል። ብፁዕነታቸው አያይዘውም “ስለ ቤተክርስቲያናችሁ እንድታውቁ፣ እንድትሠለጥኑ ያደረጉትን የፍኖተ ጽድቅ ባለቤት መጋቤ አእላፍ ጸጋዬን እናመሰግናለን፡፡” ሲሉ መልእክታቸውን እስተላልፈዋል፡፡
የወልዳ ሥላሴ ጠቅላላ ማኅበራት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ አገልግሎት የሚሰጥ በ2010 ዓ.ም የተመሠረተ ነው፡፡ የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲ/ን ጸጋው ታዬ እንደተናገሩት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ልማት እያየን ነው፡፡ ብዙ ለውጦች አይተናል እኛ ዛሬ የመጣነው የአባቶቻችንን ፈለግ ተከትለን ለቤተክርስቲያን ዘብ እንድንቆም፣ ከዚህ ባገኘነው ትምህርት ጥሩ ነገር እንድንሠራ ነው፤ ባየነው ለውጥ በጣም ደስ ብሎናል” ብለዋል፡፡
ወልዳ ዱካ ቡኦታ ጠቅላላ ማኅበራት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ማኅበር ነው፡፡ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሥርዐት ቀሲስ ኢንጅነር ፍቃዱ ከበደ እንደተናገሩት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት፣ ሙዚየምና የልማት ሥራዎች ተዋውረን ተመልክተናል፤ ልማቶቹ በጣም አስደናቂ ናቸው፤ እኛ ክረምት የምናሠለጥናቸው ልጆች ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው የጠቅላይ ቤተክህነቱን ልማት ተመልክተው ሲሄዱ በየአጥቢያቸው ከዚህ ባገኙት ልምድ እንዲሠሩ ለማድረግ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
መ/ር ኤልያስ ሙላቱ የፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ ማኅበራት ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደተናገሩት ማኅበሩ ከሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች አንዱ ሥልጠና ነው፡፡ ወልዳ ዱካ ቡኦታ ጠቅላላ ማኅበራት 200 የሚሆኑ፣ ወልዳ ሥላሴ ጠቅላላ ማኅበራት ደግሞ ከ30 ዩኒቨርስቲዎች 200 ተማሪዎች መጥተው በፍኖተ ጽድቅ ድጋፍ ለትምህርት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን፣ ምግብ፣ ማደሪያ መማሪያ ክፍል በማመቻቸት ለሥልጠናውም ከ15 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉን” ገልጸዋል፡፡ መ/ር ኤልያስ አያይዘውም በመንበረ ፓትርያርክ እየተሠራ ያለው ግቢውን ማስዋብ ልማትም ልዩ ነው፡፡ ይህም ለትውልዱ ልዩ ኩራት፣ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ትልቅ ሥራ አይተናል፡፡ በሙዚየሙም ያየነው የቤተክርስቲያን ታሪክን ነው፤ ይህም ታሪክ ተጠብቆ በመቆየቱ እኛም በማየታችን የቀደሙ አባቶቻችን እንዴት ባለ መልኩ ይህችን ቤተክርስቲያን ጠብቀው ለእኛ እንዳስረከቡን፣ ምን ዓይነት ቅርስ እንዳለን አይተናል፡፡ ይህን ታሪክ በማየቴ ኮርቻለሁ፣ ተደንቄአለሁ፡፡ እኛ ደግሞ ይህን ታሪክ ማስቀጠል ከእኛ ይጠበቃል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የራያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በጉብኝት ወቅት ባስተላለፉት መልእክት “በመንበረ ፓትርያርክ ለጉብኝት በመምጣታችሁ ልትመሰገኑ ይገባል፤ ሃይማኖታችሁን ጠብቃችሁ፣ ሥርዐታችሁን አስከብራችሁ ቤተክርስቲያናችሁን ማገልገል ከሁላችሁም ይጠበቃል” ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡©Eotc tv