የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅና የዋና ክፍል ሐላፊዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ለብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የአዲስ ዓመት እንኳን አደረሰዎ በማለት ቡራኬ ተቀበሉ።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ መሪነት፣ ከሀገረ ስብከቱ ዋና ክፍል ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በመሆን እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ 2019 ዓ/ም በሰላምና በጤና አሸጋገረዎ በማለት ከብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ለቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና ለራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቡራኬ ተቀበሉ።የእንኳን አደረሰዎ መልእክት ለብፁዕነታቸው ያስተላለፉት የልኡካኑ ተወካዮች ሊቀ ሊቃውንት አባ ጥዑመ ልሳንኪዳነ ማርያምና ሊቀ ልሳናት በዳሳ ቶላ ሲሆኑ በመልእክታቸውም ቤተ ክርስቲያን የተጋረጡባትን ፈተናዎችና አደጋዎች ለማስተካከል በብፁዕነትዎና በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ እየተመራ የሚታየው ለውጥና ውጤት በእጅጉ የሚመሰግን መሆኑን በመጤቀስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው ከቅዱስ ሲኖዶስና ከፈጣሪ የተቀበሉትን ታላቅ አደራ በእውነትና በቆራጥነት በመወጣት፣ ለቤተ ክርስቲያን ለውጥ ብዙ መስዋዕትነት እየከፈሉና ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በተለይም ቤተ ክርስቲያን እየተወቀሰች ያለችበትን ችግር በምክርና በሐሳብ ለመፍታት ከብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ጋር በመሆን ብዙ ጊዜ መወያየታቸውንና መሥራታቸው የሚታወቅ ነው ያሉ ሲሆን በ2018 ዓ.ም. የታየውን የቤተ ክርስቲያን ክብር በጠበቀ መልኩ ታላቅነቷን የሚያሳይ ለውጥን በማመስገን፣ ይህ ለውጥ በአዲሱ ዓመትም በበለጠ እንዲጎለብትና በቤተ ክርስቲያን ላይ ያሉ ችግሮች እንዲቀረፉ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ ለብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ እንኳን በሰላም በጤና አደረሳችሁ በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ቤተ ክርስቲያን ከሙስናና ከዘረኝነት የጸዳ አስተዳደርና አገልግሎት በመፍጠር ለተሰጠን ኃላፊነትና አደራ በታማኝነት መወጣት እንድንችል ብፁዕነታቸው የበኩላቸውን በአባታዊ ድጋፍና ምክር በጎን መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ይህ የተሰጠን አደራ ቤተ ክርስቲያን የሚጠበቅባትን ተልዕኮ በተሻለ መልኩ እንድትወጣ የብፁዕነታቸው ጸሎት፣ በረከትና ረድኤት እንዳይለየን በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በበኩላቸው ከዘመነ ማርቆስ በሰላም አሳልፎ ወደ ዘመነ ሉቃስ እንድንሸጋገር የረዳንን አምላካችንን ክብርና ምስጋና ይድረሰው በማለት አመስግነዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ሐላፊዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ለአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሰዎ ሲሉ ይህ ለመጀመሪያ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቀጥለውም አዲስ ለተመደቡት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ ከዚህ ቀደም በሠሩባቸው አድባራት በምስጉን አገልጋይነታቸው የሚታወቁ በመሆናቸውና ባላቸው ልምድና ዕውቀት ለሀገረ ስብከቱ የተመደቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው በመልእክታቸው፣ ለሥራ አስኪያጁ የተሰጠውን ኃላፊነት በተገቢው ለመወጣት የሀገረ ስብከቱ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሥራ አስኪያጁን በመደገፍና በመተጋገዝ፣ እርስ በርሳቸውም እንደ ወንድማማች በመተሳሰብ፣ ሳይሳደዱና ሳይጠላሉ ጊዜና ዘመን ሳያንሸራትታቸው በአንድነት መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በተለይም የመዋቅር ለውጡ እንዲመጣ፣ ሥራዎችም እንዲስተካከሉና አንገት የሚያስደፉ ተግባራት እንዲበቁ፣ ሁሉም በቤተ ክርስቲያን የተሰጠውን ኃላፊነትና አደራ በታማኝነት እንዲወጣ፣ ከሙስናና ከዘረኝነት የጸዳ አሠራርን በመከተል ለቤተ ክርስቲያን ለውጥ በአንድነት እንዲሠሩ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ዘመነ ሉቃስ መልካም የሥራ ዘመን፣ የበረከትና የጤና ዘመን እንዲሆን፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ሰላም እንዲሆንላት ምኞታቸውን በመግለጽ መልእክታቸውን አጠናቀዋል።
ዘጋቢ ጽናት አስቻለው