የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡ አስታወቀ።
ነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ምየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት አቅርቧል።
ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ ያገኘው ጠቅላላ ገቢ ካለፈው 2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ18,562,565.21 ብር ብልጫ ማሳየቱም ተገልጿል።
ከጠቅላላ ገቢ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ከድርጅቱ፣ ከመኖሪያ ቤት ኪራይና ከልዩ ልዩ ገቢዎች የተሰበሰበው 226.6 ሚሊዮን ብር ገደማ ሲሆን፣ ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ ለፈረሱ ቤቶች ከተከፈለ የካሳ ክፍያ ደግሞ 53.2 ሚሊዮን ብር በላይ፣ ከባንክ ወለድ 6.4 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ድሬዳዋ ከሚገኙ ቤቶች ከ3.5 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል ተብሏል።
ከዚህ ባሻገር፣ በኮሪደር ልማት ምክንያት የፈረሱ ቤቶችን ካሳ በተመለከተ በ1ኛው እና 2ኛው ዙር በ2017 በጀት ዓመት የተከፈለ 22.1 ሚሊዮን ብር ገደማ የነበረ ሲሆን፣ በ2018 በጀት ዓመት ግን ይህ ክፍያ ወደ 53.2 ሚሊዮን ብር ማደጉ ተጠቅሷል ፣ ከዚህ ውስጥ 7.8 ሚሊዮን ብር ገደማ ገቢ የተደረገ ሲሆን፣ ቀሪውን ገንዘብ ገቢ ለማድረግ ክትትል እየተደረገ ይገኛል ተብሏል።
በተመሳሳይ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት ጀርባ የነበሩ መኖሪያ ቤቶች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተሰጠ ሙያዊ አስተያየት መሠረት ለተነሱት 22 ግለሰቦችም ድርጅቱ 1.7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ምትክ መኖሪያ ቤቶችን ሰርቶ ማስረከቡ በሪፖርቱ ቀርቧል።
በተጨማሪም፣ ድርጅቱ በሕግ አገልግሎት በኩል ይከታተላቸው ከነበሩ 10 መዝገቦች ውስጥ 6ቱ ውሳኔ ያገኙ ሲሆን፣ ውል አፍርሰው ለ3ኛ ወገን አሳልፈው የሰጡ ተከራዮች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ከመወሰዱ ባሻገር፣ ወርሃዊ ኪራይ ባልከፈሉ አካላት ላይ በተመሠረተ ክስ ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፍሉ በወጡ ውሳኔዎች መሠረት ክትትል እየተደረገ ይገኛል ተብሏል።
ድርጅቱ አሰራሩን ዘመናዊና ግልጽ ለማድረግም የራሱን ድህረ ገጽ (WWW.eotcha.org) እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮችን ስራ ላይ ያዋለ ሲሆን፣ በተመሳሳይ መልኩ ከዓባይ ባንክ ጋር በመተባበር ተከራዮች ባሉበት ሆነው ክፍያቸውን በቀላሉ እንዲፈጽሙ የሚያስችል የሞባይል ባንክንግና የደወል (Alarm) ሥርዓት ተግባራዊ ማድረጉ ተነግሯል።
በሌላ በኩል ቀደም ሲል የውሃና የኤሌክትሪክ ፍጆታን በተመለከተ በወር ከ15,000 እስከ 20,000 ብር ያወጣ የነበረውን የድርጅቱን ወጪ፣ አሰራሩን በመቀየር ተከራዮች የተጠቀሙበትን ብቻ እንዲከፍሉ በማድረግ ወርሃዊ ወጪውን ወደ 2,000 – 2,500 ብር ዝቅ ማድረግ መቻሉም በሪፖርቱ ቀርቧል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሪፖርቱን ተከትሎ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በተገበራቸው አሰራሮች ከነበሩበት ችግሮች እየተላቀቀ መፍትሔም እያገኘ ስለመሆኑን ጠቁመዋል።
ብፁዕነታቸው “ችግሩ ምንድን ነው ፣ ከቤተክርስቲያን ራሳችንን እያስቀደምን ነው ፣ ለመሰባሰባችን ምክንያት የሆነችንን ቤተክርስቲያንን ማስቀደም ይኖርብናል ፣ አካሄዳችን አሠራራችን ሁሉ በጣም የተሻለ መሆን አለበት” ሲሉም አክለዋል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ ያስመዘገበው ውጤት አበረታች መሆኑንም ገልፀው “አሁንም ከዚህ የተሻለ አሰራራችን ግልፅ እንዲሆን መጠናከር ፣ መበርታት ያስፈልጋል” ብለዋል።
©የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/