የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ 11ኛ ዓመት የዕረፍት መታሰቢያ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በጸሎተ ፍትሐት ታሰበ።
ነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ምየብፁዕ አቡነ ፊልጶስ 11ኛ ዓመት የዕረፍት መታሰቢያ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በጸሎተ ፍትሐት ታስቦ ዋለ ። በዕለቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ቀሳውስት ዲያቆናት እና ሊቃውንት እንዲሁም የብፁዕነታቸው ቤተሰብ እና ምእመናን ተገኝተዋል።
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በዕለቱ ባደረጉት መንፈሳዊ ንግግር፤ “በእግዚአብሔር ቤት ለዘላለም የሚኖሩ ብፁዓን ናቸው፤ ከሕፃንነታቸው ጀምረው እግዚአብሔርን ሲያመልኩ የኖሩ አባቶቻችንን እንድናስባቸው በቅዱሳት መጻሕፍት ታዘናል” ብለዋል። አክለውም ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የሕዝብ አባትና የሁሉም እንባ አባሽ እንደነበሩ አስታውሰው፣ እግዚአብሔር እስከወሰነላቸው የአገልግሎት ዘመን ድረስ በታማኝነት አገልግለው ወደ ፈጣሪያቸው ማለፋቸውን ገልጸዋል።
ሊቀ ጳጳስት አባቶች እራሳቸውን ለአገልግሎት አሳልፈው በመስጠት ሌላው እንዲያምንና እንዲማር ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ “ለእኔ” ሳይሉ የሠሩት መልካም ሥራ ዋጋው ከምድር እስከ ሰማይ የከበረ መሆኑን አስገንዝበዋል። “በእነሱ ላይ ሁለተኛው ሞት ሥልጣንም ሆነ ኃይል የለውም፤ ሰው ሞተ የሚባለው እምነትና በጎ ሥራ የሌለው ሲሆን ነው፤ በእግዚአብሔር ያመነ ግን የነፍስ ድኅነትን ያገኛል” በማለትም አስተምረዋል።
በመጨረሻም፣ ከአባቶቻችን ፈለግ በመማር ለሰውና ለእግዚአብሔር በበጎ ተግባር ልንገለጥ እንደሚገባ አሳስበዋል። “ዋኖቻችሁን አስቡ” ሲባል በሕይወት ዘመናቸው የመሠሩትን ሥርዓትና መሠረት መከተል እንደሚገባ ገልጸው፣ ለአገልግሎት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
© Eotc tv
