ሐምሌ ፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም አዲስ አበባ
“”””””””””””””””””””””””””””””””””””””
በነገው ዕለት ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም ሢመተ ኤጲስቆጶስነት ለሚፈጸምላቸው ፱ ቆሞሳት የጸሎተ አስኬማ ሥርዓት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መሪነት ብፁፅ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒዩወርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ክቡር ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶችና በርካታ ቁጥር ያላቸው ምእመናን በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተከናወነ።

በሥርዓተ ቤተክርስቲያን በተቀመጠው መሠረት አዲስ ለሚሾሙ ኤጲስቆጶሳት በሲመቱ ዋዜማ የሚፈጸመው ጸሎተ አስኬማ የደረሰላቸው ዘጠኝ ቆሞሳት ሰኔ ፳፱ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተመረጡና በነገው ዕለት ሥርዓትተ ሢመተ ኤጲስ ቆጶስና ተፈጽሞላቸው በዘጠኝ አህጉረ ስብከት የሚመደቡ ናቸው።

በዛሬው ዕለት በተፈጸመው ጸሎተ አስኬማ ለሥርዓቱ የተሠራው ጸሎት በቅዱስነታቸው መሪነት ከደረሰ በኋላ ቡራኬ የተሰጠበትን ቅናተ ዮሐንስ ቅዱስነታቸው ለተሿሚ ቆሞሳት አስታጥቀዋል። ሥርዓቱ ከደረሰ በኋላ በቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳንና ጸሎት ተጠናቋል።