መስከረም ፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””””
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
******

የቅድስት ልደታ ጤና ኮሌጅ በተከታታይ ዓመታት ያስተማራቸውን ተማሪዎች ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በተገኙበት አስመረቀ።

የቅድስት ልደታ ጤና ኮሌጅ በፋርማሲ ፣ በነርሲንግ እና ቢዝነስ ማኔጅመንት ያስተማራቸውን ተማሪዎች በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ አዳራሽ በክብር አስመርቋል ፤ ኮሌጁ በ1997 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ 5ኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ተባርኮ የዛሬ18 ዓመት የተመሠረተ ኮሌጅ መሆኑም ተገልጿል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል (ዶ/ር) የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ፣ የማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያምና የደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም አስተዳዳዳሪ መልአከ ብርሃናት ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ አማረ ፣ የደብሩ የሰበካ ጉባኤ አባለት ፣ የደብሩ ካህናት እና የተክለ ሳዊሮስ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ፣ የኮሌጁ የቦርድ አባላት መምህራን እና የኮሌጁ የአስተዳደር ሠራተኞች ተመራቂ ተማሪዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ተከናውኗል።

በዕለቱ በብፁዕነታቸው ጸሎተ ቡራኬ የዕለቱ መርሐ ግብር በጸሎት የተከፈተ ሲሆን በኮሌጁ የሥራ ኃላፊዎች የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልዕክትና የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ተላልፎ በመርሐ ግብሩ ላይ የተመራቂ ተማሪዎች የምረቃ እና የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

በመጨረሻም ከየትምህርት ክፍሉ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የዋንጫ እና የሽልማት መርሐ ግብር ተካሂዶ በብፁዕነታቸው አባታዊ መልዕክት እና ጸሎተ ቡራኬ ተሰጥቶ የዕለቱ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ተጠናቋል።