መስከረም ፲፩ ቀን ፳፻ ፲ ፮ ዓም
“””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******
በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለንደን (UCL) መምህር የሆኑትና ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያና በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤክርስቲያን ጉዳይ ላይ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ጃኮፖ ግኒስኪ በመቅደላ ጦርነት ዘመን ከአገር እንደወጣ የሚገመትና በእርሳቸው እጅ የነበረ ጽላት ወደ ሀገሩና ወደ መንበረ ክብሩ እንዲመለስ ከፍተኛውን አስተዋጽዖ እንዳበረከቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን በመወከል ጽላቱን የተረከቡት የልዑካን ቡድኑ ተወካይ ቀሲስ ዶ/ር አባተ ጐበና ምስጋናቸውን በልዑካኑ ስም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በእንግሊዝ አገር በተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች እጅ የሚገኙ ንዋየ ቅድሳትን የማስመሡን ጉዳይ ትኩረት በመስጠት የማጣራቱንና የማስመለሱን ከተቋማቱና ከግለሰቦቹ ጋር በመነጋገር ሒደት እንዲከታተሉ ልዑካን ቡድን መመደቡ ታውቋል። የልዑካኑ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የስዊድን፣ ስካንዲናቭያና ግሪክ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ምከትል ሰብሳቢው ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የጣልያንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ እንዲሁም ዋና ጸሐፊው ቀሲስ ዶ/ር አባተ ጐብና ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እና ከውጭ ጉዳይ መምሪያ ጋር በመነጋገር ጉዳዩን በቅርብ በመከታተል ለዚህ ፍጻሜ እንዲበቃ ያላሠለሰ ጥረት አድርገዋል።

ዶ/ር ጃኮፖ ግኒስኪ ጽላት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ዘንድ ያለውን የተለየ ክብር በመገንዘብ በቅዱስ ሲኖዶስ ከተመደቡላቸው ልዑካን ጋር በመመካከርና ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በተከታታይ የተሰጠውን መመሪያ በመከተል ጽላቱ መንፈሳዊ ክብሩን በጠበቀ መንገድ ርክክቡ ተፈጽሞ ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ማድረጋቸው እጅግ የሚደነቅ አርአያነት ያለ ተግባር መሆኑን የልዑካን ቡድኑ ፀሐፊ ቀሲስ ዶ/ር አባተ ጐበና ጨምረው ገልጸዋል።

በለንደን ከተማ ጥንታዊ ቅርሶችንና ሃይማኖታዊ ጥቅም ያላቸው ንዋያትን ለተገቢው ባለቤቶቻቸው የሚመልሱ ተቋማትንና ግለሰቦችን የሚያበረታታው “ሸሃራዛድ ፋውንዴሽን” (The Schaharazade Foundation) የተባለ ምግባረ ሠናይ ድርጅት ዶ/ር ጃኮፖ ግኒስኪ ጽላቱ ወደ ትክክለኛዋ ባለንብረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እንዲመለስ ለፈጸሙት አርአያነት ያለው መልካም ተግባር እውቅና በመስጠት የድርጅቱን ልዩ ሜዳልያና የምሥከር ወረቀት ሸልሟቸዋል።

የሸልማቱ ሥነ ሥርዓት መስከረም ፲ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም. በለንደን አቴናዩም መሰብሰቢያ አዳራሽ (The Atanaeum) የተካሄደ ሲሆን፣ በሽልማቱም ወቅት የፋውንዴሽኑ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጣሂር ሻህ ዶ/ር ጃኮፖ ግኒስኪ ያደረጉትን ምሳሌነት ያለው ተግባር ሌሎችም ተቋማትና ግለሰቦች ሊከተሉት እንደሚገባ አሳስበው ይህንንም ለመደገፍ ድርጅታቸው ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ዓለም አቀፍ ኮሚቴን በመወከል በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተካፈሉት የታሪክ ምሁሩና የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑት የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ልጅ ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት በበኩላቸው ጽላቱ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መመለሱ አጅግ ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጸው፣ ከመቅደላ የተዘረፉ ሌሎችም ንዋየ ቅድሳት አንዲሁም ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ሁሉ እንዲመለሱ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በብሪታንያ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ከቡር አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በበኩላቸው ዶር ጃኮፖ ግኒስኪ ጽላቱን ክብሩን በጠበቀ መንገድ ለኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መመለሱ ፣ ሌሎችም የቤተመንግሥት የክብር መገልገያ የነበሩ የተለያዩ ቅርሶችም ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጸው አሁን የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት እየከበሮን ያለበት ሰሞን እንደመሆኑ እነዚህ ሁሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአዲስ ዓመት ሥጦታ ሆነው እንደተሰጡ እንቆጥረዋለን በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል።

ጽላቱ አስፈላጊው ቀኖናዊ ሥርዓት ከተፈጸመ ተፈጽሞ እሑድ
መስከረም ፲፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የስዊድን፣ስካንዲናቪያና ግሪክ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣ የልዑካ ሰብሳቢ, በተገኙበት በሚደረግ ሥርዓተ ማኅሌት፣ ጸሎተቅዳሴ እና ሥርዓተ ዑደት በካህናት፣ በምእመናንና በሰንበት ት/ቤት መዘምራን ልዩ የአቀባበልና የሽኝት ሥነ ሥርዓት ከተደረገለት በኋላ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ወደ መንበረ ክብሩእንደሚመለስ ቀሲስ ዶ/ ር አባተ ጐበና የልዑካኑ ጸሐፊ ጨምረው ገልጸዋል ሲል የውጪ ግንኙነት መምሪያ በላከልን ዘገባ ገልጿል።