መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
***
የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓት በመከበር ላይ ነው።በበዓሉ ሊይ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒዩወርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ክቡር ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የጠቅላይ ቤተክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የጠቅላይ ቤተክህነት መምሪያ ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣የከተማችን አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣አምባሳደሮች ፣ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ካህናት፣ምዕመናንና ምዕመናት ተገኝተዋል።

በበዓሉ ላይ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖትን የእንኳን አደረሳችሁን መልዕክት በንባብ ያሰሙት ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው። የቅዱስነታቸው የ፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል።

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ መልእክት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን።

“ንሕነሰ ንሰብክ ክርስቶስሃ ዘተሰቅለ፤
እኛስ የተሰቀለውን ክርስቶስ እንሰብካለን”
(፩ኛ ቆሮ. ፩፥፳፪)

የክርስትና ሃይማኖት በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በምድር ላይ እያቈጠቈጠ በነበረበት ጊዜ የዓለም ማኅበረ ሰብ እምነት በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፈለ ነበረ፤ ይኸውም፡-

አንደኛው፦ በአምልኮተ እግዚአብሔር ወይም እውነተኛውን አምላክ በማምለክ ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ፦ በአምልኮ ጣዖት ወይም በምስል በቅርጽ በፍጡር በማምለክ ነው፡፡

በአምልኮተ እግዚአብሔር የሚታቀፉት የእስራኤል ሕዝብ ሲሆኑ ሌሎቹ በጣዖት የሚያመልኩ አረማውያን ወይም አሕዛብ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት መደቦች የየራሳቸው የሆነ የአስተሳሰብ ወይም የአመለካከት ዝንባሌ ነበራቸው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው በአንደኛው መልእክቱ፦ የግሪክ ሰዎች ጥበብን ወይም ፍልስፍናን ይሻሉ፤ አይሁድም ምልክትን ወይም አስገራሚ ተአምርን ይፈልጋሉ በማለት ይገልጻቸዋል፤ በዚህ አገላለጹ ግሪካውያንን በአምልኮ ጣዖት፥ አይሁዳውያንን በአምልኮተ እግዚአብሔር መደብ መቀመጣቸውን እናስተውላለን።

ቅዱስ ጳውሎስ አዲሱ ሃይማኖተ ክርስቲያን ከነኝህ ሁለቱ የተለየ መሆኑን ሲገልፅ እኛ ግን ክርስቲያኖች ማለቱ ነው “የተሰቀለውን ክርስቶስ እንሰብካለን” ይላል፤ ምክንያቱም “የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሞኝነት ነው፤ ለኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር የማዳን ኃይል ነውና በማለት ያብራራል”፤ በመቀጠልም መስቀሉ ከጥበብ ሁሉ የበለጠ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው፥ ይልና ግሪኮች የሚመኩበት ጥበብ ወይም ፍልስፍና በእግዚአብሔር ዘንድ ሞኝነት ነው ይላል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ትምህርቱ የተመራማሪዎች ጥበብና የተአምራት ጋጋታ በሃይማኖተ ክርስትና ብዙ ቦታ የማይሰጣቸው መሆኑን በሚገባ አስምሮበታል፡፡ ምክንያቱም የሰውን ሁለንተና ሕይወት በማዳን ረገድ እዚህ ግባ የሚባል ሚና የላቸውምና ነው፤ ፍልስፍና በቊሳዊ ነገር ለዚያውም በጥቂቱ ለማወቅ ይሞክራል፤ ስለ መንፈሳዊው ነገር ግን ጭራሽ ባዶ ነውና የሰውን ሁለንተናዊ ሕይወት ሊያድን አይችልም፤ ተአምራት ማየት ወይም ማሳየትም ከገሃነም ፍርድ እንደማያድን ጌታችን በቅዱስ ወንጌል በማያሻማ መንገድ አስተምሮአል፤ ስለዚህ ፍልስፍናም ሆነ ተአምር ሰውን በማዳን ረገድ የሚጫወቱት ሚና እንደሌለ በዚህ እናስተውላለን።

በአንጻሩ ግን የክርስቶስ መስቀል ለሚጠፉትም ሆነ ለሚድኑት ወሳኝ ሚና ያለው የእግዚአብሔር የማዳን ኃይል እንደሆነ እናስተውላለን፤ ምክንያቱም በሰማይና በምድር ያሉትን ሁሉ አስታርቆ ሰላምንና አንድነትን የመሠረተ እሱ ነውና ነው፤ እዚህ ላይ በደምብ ማስተዋል ያለብን መስቀል ስንል ነገረ ወንጌል ማለታችን መሆኑን፥ ነገረ ወንጌል ስንል ነገረ ክርስቶስ ማለታችን መሆኑን፥ ነገረ ክርስቶስ ስንል ድኅነተ ሰማይ ወምድር ማለታችን መሆኑን ነው።

ከዚህ አንጻር ነገረ መስቀሉ በሰማይና በምድር ያሉትን ወይም መንፈሳውያኑንና ሥጋውያኑን በደሙ ቤዛነት ዋጅቶ የፍጡራንን ሁለንተና ሕይወት ያዳነ በመሆኑ ከጥበብ ከፍልስፍና እና ከተአምር ሁሉ በላይ ነውና ሊታመን፥ ሊሰበክና ሊከበር ይገባዋል፤ ክርስቲያኖች በአጠቃላይ በተለይም እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን በየዓመቱ የምናከብረው በተአምር ተቆፍሮ የተገኘውን ዕፀ መስቀል ብቻ ሳይሆን በዋናነት ከዕፀ መስቀሉ በስተጀርባ ያለውን ምስጢረ ድኅነት ነው፤

የበዓሉ ዓቢይ መልእክትም “ክርስቶስ በመስቀሉ ወይም በስቅላቱ በሰማይና በምድር ያሉትን አስታርቆ አድኖአል” የሚል ነው፤ ትናንትም ዛሬም እየተሰበከልን ያለው ወንጌል ይህ ነው ቅዱስ ወንጌል “እግዚአብሔር በዓለም እንዲፈርድ ልጁን አልላከውም፤ ዓለም በእሱ እንዲድን እንጂ፤ በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ የማያምን ግን በእግዚአብሔር ልጅ ስላላመነ አሁኑኑ ተፈርዶበታል” ብሎ እውነቱን ነግሮናል፤ መስቀልም ለኛ ያቀረበው ጥሪ ይህ ነው።

ከዚህ አንጻር የመስቀልን ነገረ ድኅነት የተቀበለ ሰው ሁለንተናዊ ሕይወቱ ይድናል፤ ያልተቀበለ ግን “የእግዚአብሔር መቅሠፍት በላዩ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያያትም” ተብሎ በማያሻማ መልኩ ተቀምጦአል፤ ለዚህም ነው “የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሞኝነት ነው፤ ለምንድን ለኛ ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው” ተብሎ ሓቁ የተነገረው።

የክርስቶስን መስቀል መስበክ ለኛ ለክርስቲያኖች ተቀዳሚ ተግባራችን ነው፤ የነገረ መስቀል ተልእኮ የሁሉም ክርስቲያኖች ተልእኮ ነው፤ መስቀሉን የምንሰብከው በቃል ብቻ አይደለም፤ በተግባራዊ ሕይወትም እንጂ፤ ነገረ መስቀል ማለት ለእምነት ለሰላም ለአንድነት ለእኩልነት ለነጻነት በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ደኅንነት ሲባል የሚከፈል የሰላም መሥዋዕት እንጂ ሌላውን ወገን የሚያሳድድ አይደለም።

መስቀል ሌላውን ማክበር ራስን ግን ዝቅ ማድረግን የሚያስተምር እንጂ ራስ ወዳድነትን አያስተናግድም፤ መስቀል ሁሉንም አቀራርቦ አስማምቶና አፋቅሮ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ እንጂ የሚያለያይ አይደለም፤ ታድያ የክርስቶስ ነገረ መስቀል ምሥጢር ይህ ሆኖ ሳለ እኛ መስቀላውያን የመስቀሉ ቃል በሕይወታችን እንዴት እየተተረጐመ ነው? የሚለውን ማንሣት ተገቢ ነው፤

ራሳችንን በራሳችን ለማታለል ካልከጀልን በቀር አእምሮአችን እውነቱን በሚገባ ያውቃል፤ ይመሰክርብናልም፤ ነገ ሳይሆን ዛሬ እውነቱን ተናግረን ንስሐ እንግባ ከተባለ ከመስቀሉ ቃል በብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀናል፥ አንድ ሁኑ ስንባል መለያየትን እየመረጥን እንታያለን፥ ሰላም ሁኑ ስንባል መጣላትን እንፈልጋለን፥ ታረቁ ስንባል እምቢ አንቀበልም እንላለን፥ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ስንባል በክንዳችን መመካትን እንመርጣለን፥ ታድያ የመስቀሉ ቃል በየትኛው አእምሮአችን ነው ያለው፤ በሀገራችን ያለው ሓቅስ ይህ አይደለምን? ይህ ጠቅሞን ከሆነ እናንተው ራሳችሁ ፍረዱ፤

የመስቀሉን ቃል ከልብ ብናደምጠውና ብንቀበለው በእጅጉ ይበጀናል፤ ይህንን የማንቀበል ከሆነም እኛ ይቀርብናል እንጂ መስቀሉ ምን ጊዜም አሸናፊ ነው፤ ለዘላለምም ሲያሸንፍ ይኖራል፤ ስለሆነም ጉዞአችን አላማረምና እባካችሁ ንስሐ ገብተን በመስቀሉ ቃል ተቀራርበንና ተስማምተን ይቅር ይቅር ተባብለን በአንድነት በእኩልነት በሰላምና በፍቅር እንኑር፤ በምድራችን ፍትሕ ርትዕ ይንገሥ፥ ሰብአዊ መብት ይከበር፥ የተበደለ ይካስ፥ እግዚአብሔር ይደመጥ መስቀል ማክበር ማለት ይህ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ሀገርእባካችሁ ንስሐ ገብተን በመስቀሉ ቃል ተቀራርበንና ተስማምተን ይቅር ይቅር ተባብለን በአንድነት በእኩልነት በሰላምና በፍቅር እንኑር፤ በምድራችን ፍትሕ ርትዕ ይንገሥ፥ ሰብአዊ መብት ይከበር፥ የተበደለ ይካስ፥ እግዚአብሔር ይደመጥ መስቀል ማክበር ማለት ይህ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ሀገርእባካችሁ ንስሐ ገብተን በመስቀሉ ቃል ተቀራርበንና ተስማምተን ይቅር ይቅር ተባብለን በአንድነት በእኩልነት በሰላምና በፍቅር እንኑር፤ በምድራችን ፍትሕ ርትዕ ይንገሥ፥ ሰብአዊ መብት ይከበር፥ የተበደለ ይካስ፥ እግዚአብሔር ይደመጥ መስቀል ማክበር ማለት ይህ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ሀገር በመንፈሳዊና በቊሳዊ በረከት ትባረካለች፤ ትለማለችም፤ ታድግማለች፤ እግዚአብሔርም በተግባሩ ወይም በፍጥረቱ ይደሰታል፡፡

መልካም የመስቀል በዓል ያድርግልን፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤
አሜን።

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም.