ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ፣ የቤተ መጻሕፍት ወመዘክርና የማኅበራት ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ አላማጣ ከተማ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።

ጥር ፬ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
****
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
——————-

ከሦስት ዓመታት በፊት የቋሚ ሲኖዶስ ተረኛ መሆናቸውን ተከትሎ ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት የመጡት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በአዲስ አበባ ለመቆየት በመገደዳቸው ወደ ሀገረ ስብከታቸው ሳይሔዱ መቆየታቸው ይታወሳል።

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላም በአካባቢው ያለው ችግር ከመሰረቱ ባለመፈታቱ ምክንያት በራያና አካባቢው የሚገኙ ኦርቶዶክሳዊያን ምዕመናን የሚባርካቸው፣ የሚያስተምራቸውና የሚያጽናናቸው አባት ማጣታቸውን ተከትሎ ለቅዱስ ሲኖዶስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በአባትነት ተመድበው እንዲመጡላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በጊዜያዊነት የራያና አካባቢው  ስድስቱ ወረዳዎች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ እንዲመሩት የሰጠውን ውሳኔ ተከትሎ ጽሕፈት ቤቱ ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩና በ42ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሪፖርት ማቅረቡም ይታወቃል።

ይህን ተከትሎ ጽሕፈት ቤቱን በማቋቋም፣ በማደራጀትና ሰራተኞችን በመመደብ በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውኑ የቆዩት ብፁዕነታቸው ጥር 3 ቀን 2016 ዓ/ም. የጥምቀት በዓልን ለማክበር፤ በጦርነትና በድርቅ የተጎዳውን ሕዝበ ክርስቲያንም ለማጽናናት  አላማጣ ከተማ ገብተዋል።

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ  አላማጣ ከተማ ከመግባታቸው በፊት በቅርበት በምትገኘው ቆቦ ከተማ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ምዕመናንና ምዕመናት በአይሱዙ መኪናዎች፣ በቤት መከናዎች፣ በባጃጃጅና በእግር በማጀብ ደማቅ፣ ናፍቆት የተሞላበት፣ ጥልቅ የአባት ፍቅር የታየበትና በዓይነቱ ልዩና ደማቅ አቀባበል። አድርገውላቸዋል።

በአላማጣ ከተማ በሚገኘው ጥንታዊውና ታሪካዊው አላማጣ ደብረ መድኃኒት መድኀኔዓለም ካቴድራል በተደረገላቸው ደማቅ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ በአላማጣና አካባቢው የስድስቱ ወረዳ ቤተክህነት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ሥዩማን ሀብቱ አየነው የእንኳን ደህና መጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተገኙ በብዙ መቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ምዕመናንና ምዕመናት “እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋም።” በሚል ርዕስ  ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ልዑል እግዚአብሔር እንኳን በሰላምና በጤና አገናኘን ካሉ በኋላ ከሦስት ዓመታት በፊት ለቋሚ ሲኖዶስ አገልግሎት ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት በተጓዝኩበት ወቅት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት መንገድ በመዘጋቱ አገልግሎቴን አጠናቅቄ ወደ አገሬ መመለስ ባለመቻሌ በዚያው ለመቆየት ተገድጃለሁ ብለዋል። ልጆቼ ስትራቡ፣ ስትጠሙ፣ ስትታረዙ፣ ስትሰቃዩና ስትሰደዱ አብሬአችሁ ባለመሆኔ እጅጉን ሳዝን፣ ሳለቅስና ወደ ፈጣሪዬ ሳለቅስ ከርሜአለሁ። ያለፉትን ሦስት ዓመታትም በጾም፣ በጸሎትና በናፍቆት በመቆየት ዳግም የምንገናኝበትን ጊዜ ስናፍቅ ከርሜአለሁ ብለዋል።

በአላማጣና አካባቢው በአጠቃላይም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በሞተ ሥጋ የተለዩንን አባቶችካህናት፣ ዲያቆናት፣ ወንድሞችና እህቶችን ልዑል እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ከደጋጎቹ አባቶቻችን ጎን ያኑርልን ካሉ በኋላ ላደረጋችሁልኝ ታሪካዊና ደማቅ አቀባበል ልባዊ ምስጋናዬን እያቀረብኩ ለወደፊቱ በእምነታችሁ ጸንታችሁ፣ አንድነታችሁን አጽንታችሁ እንድትኖሩ አባታዊ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፤ በማለት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተው የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።

በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የአቀባበል ሥነሥርዓት ዙሪያ ዝርዝር መረጃዎችን ለማድረስ በአካባቢው ኢንተርኔት ባለመኖሩ ምክንያት በፎቶግራፍ የተደገፈ መረጃ ለማድረስ ባንችልም ለወደፊቱ የተጠናከረ መረጃ ስናገኝ መረጃውን የምናደርስ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን።