የካቲት 17 ቀን 2016ዓ.ም
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨

ቅዱስነታቸው በዛሬው ዕለት በህንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ድምቀት የተከበረውን የሐዋርያው የቅዱስ ቶማስ የሰማዕትነት መታሰቢያ በዓል በማስመለከት በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ከብፁዕ ወቅዱስ ባስልዮስ ማር ቶማ ማቴዎስ ሦስተኛ የህንድ ማላንካራ ሲሪያን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የክብር ጥሪ ተደርጎላቸው የነበረ ቢሆንም ቅዱስነታቸው በአካል ለመገኘት አስቀድሞ በተያዘ መርሐ ግብር ምክንያት ስላልቻሉ በቋሚ ሲኖዶስ በተወከሉ ልዑካን አማካኝነት አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል።

ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና የህንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት አስታውሰው በበዓሉ ላይ በአካል መገኘት ባይችሉም በጸሎት አብረው መሆናቸውን ገልጸውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው ለህንዱ አቻቸው የጻፉት መልእክት የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ እና ሊቃነ ጳጳሳት፣የህንድ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ምእመናን በታደሙበት በዓል ላይ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የምሥራቅ እና ምዕራብ ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በንባብ አሰምተው ለቅዱስ ፓትርያርኩ አስረክበዋል።
©የቅ/ፓ/ልዩ ጽ/ቤት