ግንቦት ፬ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ/ም
“””””””””””””””””””””””””””
ደቡብ አፍሪካ- ጁሐንስበርግ
==================

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፣ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት፣ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የዳውሮ-ኮንታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ በደቡብ አፍሪካ ጁሐንስበርግ ጽርሐ ጽዮን መድኀኔዓለም ካቴድራል የተመሰረተበትን ፳፭ኛ ዓመት በዓል ለማክበር በደቡብ አፍሪካ የተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ አብያተክር
ስቲያናትና ምዕመናንን ለመጎብኘትና ለመባረክ ደቡብ አፍሪካ ጁሐንስበርግ መግባታቸው ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው በዛሬው እለት በደቡብ አፍሪካ የጆሐንስበርግ መንበረ ጵጵስና ጽርሐ ጽዮን መድኃኔዓለም ካቴድራል በመገኘትም ካቴድራሉ የተመሰረተበትን ፳፭ኛ ዓመት በዐልን አክብረዋል።

በዓሉ በማኅሌት፣ቅዳሴ፣ በዝማሬና በልዩልዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብሮች የተከበረ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ የግሪክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስና የደቡብ አፍሪካ ዜግነት ያላቸው ኦርቶዶክሳዊያን ካህናትም የበዓሉ ታዳሚዎች ሲሆኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ምዕመናንና ምዕመናትም ተገኝተዋል።

በዚሁ ጊዜ በሀገረ ስብከቱ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት በሪፖርት ቀርበዋል።በሪፖርቱም በሀገረ ስብከቱ ሀገሩንና ቦታውን የሚመጥን የአስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋቱን፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ መንፈሳዊ ዕወቀቱ እንዲጎለብት፣ በሃይማኖቱ እንዲጸና፣ተተኪ ወጣቶች መንፈሳዊ ዕውቀትን እንዲገበዩ፣ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸውን፣ አዳዲስ አብያተክርስቲያናት በአገሪቱ በአራቱም ማዕዘን እንዲተከሉና ስብከተወንጌል እንዲስፋፋ መደረጉን የሚገልጽ ሪፖርት ቀርቧል። በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ደቡብ አፍሪካዊያን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካህናትም የእንኳን ደህና መጣችሁና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው ቅዱስ አባታችን በደቡብ አፍሪካ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ለቅዱስነታቸው የክብር ስጦታ አበርክተዋል።

በብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የዳውሮ-ኮንታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ትንሣኤ ሙታንን በተመለከተ ሰፊ ትምህርተ ወንጌል የተሰጠ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በደቡብ ና ደቡብ ምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት የተሰሩ ዋናዋና ሥራዎች፣ ባለፉት አራት ዓመታት የተተከሉ አዳዲስ አብያተክርስቲያናትና ወደፊት የሚተከቱ አዳዲስ አብያተክርስቲያናትን የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ አጭር ሪፖርት አቅርበው ቅዱስነታቸው ለበዓሉ ታዳሚዎች ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ እንዲሰጡ ጋብዘዋል።

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፒትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱምጨወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ፦ እግዚአብሔርን እንድናመልክ ቅድስት እርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ስላሰባሰበችን ክብር ምስጋና ለእግዚአብሔር ይግባው፤ካሉ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ የዚህን የጁሐንስበርግ ጽርሐ ጽዮን መድኀኔዓለም ካቴድራልን ሃያ አምስተኛ ዓመት በዓል በጋራ እንድናከብር ከያለንበት ስለሰበሰበንና በጋራ እንድናከብር ስላደረገን አሁንም ክብር ምስጋና ይግባው።ብለዋል።

ይህን ካቴድራል በዚህ መልኩ አሳምራችሁና አስውባችሁ በመሥራት ለአገልግሎት ምቹ ያደረጋችሁና በዚህ የተቀደሰ ሥራ በልዩልዩ መልኩ በመሰማራት አስተዋጽኦ ያደረጋችሁ ልጆቻችን ሁሉ ምስጋና ይገባችኋል።ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ የቤተክርስቲያኑ ቅጽረ ጊቢ ጠባብ ስለሆነ ወደፊት ፓርኪንግ ያለው ሕዝበ ክርስቲያኑ አየር እየተቀበለ ፣ኡደት እየተደረገ በዓል የሚከበርበት ቤተክርስቲያን በአጭር ጊዜ ሰርታችሁ ለአገልግሎት እንድታበቁት አደራ እንላለን በማለት ቃለ ቡራኬና ቃለ ምዕዳን በመስጠት የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።

ከቅዱስነታቸው ቃለምዕዳንና ቃለ ቡራኬ ቀደም ብሎም ለቅዱስነታቸው፣ለብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ፣ ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ለቤፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ የግሪክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ፣ በጁሐንስበርግ ጽርሐ ጽዮን መድኀኔዓለም ካቴድራል የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን በገንዘባቸው፣ በእውቀታቸውና በጉልበታቸው በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ወገኖች ሀገረ ስብከቱ ያዘጋጀላቸው ሽልማት ተበርክቷል።