ጷጉሜን ፫ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት በርዕሰ አድባራት ወገዳማት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል የቅዱስ ሩፋኤል በዓል ሢመት በድምቀት ተከብሮ ውሏል። በብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መልካም ፈቃድና አሳሳቢነት የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እና ሊቀ ሊቃውንት ሐይለ ሥላሴ ዘማርያም በበዓሉ ተገኝተዋል።

የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ኃይል አባ ተስፋዬ እማምሰው (ቆሞስ) የሀገረ ስብከቱ የመምሪያ ኃላፊዎች የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እንዲሁም በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል።

በዕለቱም በብፁዕ አቡነ ገብርኤል “መልአኬን በፊትህ ይሄዳልና” ዘጸ ፳፫÷፳፫ በሚል በዓሉን በተመለከተ በሰፊው ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል ። በማስከተልም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስያን ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ከ፩ኛ እስከ ፫ኛ ለወጡ ተማሪዎች እንዲሁም የባሕረ ሀሳብ ትምህርትን ከመጋቤ ምሥጢር ያሬድ የተከታተሉ ደቀመዛሙርት የሽልማት መርሐ ግብርና ከሌላ ቤተ እምነት መጥተው ለተጠመቁ አዲስ ክርስቲያኖች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል። በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ገብርኤል የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተሰጥቶ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።

መረጃውን ያደረሰን የሀገረ ስብከቱ ሚዲያና ዘጋቢ ክፍል ነው።