የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዛሬው ዕለት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ የመልዕክቱ ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡
የተከበራችሁ የሃገራችን ሕዝቦች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና ምዕመናን፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሀገርን ዳር ድንበር እና ሰላም ለማስከበር ቀን ከሌት የምትደክሙ የሠራዊት አባላት፣ በሕመም ምክንያት በቤታችሁ እና በሕክምና ማዕከላት የምትገኙ ሕሙማን፣ በማረሚያ ቤቶች የምትገኙ የሕግ ታራሚዎች በአጠቃላይ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የምትገኙ ውድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ለ2017 ዓመተ ምሕረት የዘመን መለወጫ ባዕል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ፣ አደረሰን፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎች ቢገጥሟትም በፈጣሪ እርዳታ እና በሕዝባችን አስተዋይነት እንዲሁም ትጋት ለማለፍ ችላለች፡፡ ሰላም በአንድ ቀን በሚሠራ በጎ ሥራ የሚገነባና የሚጠናቀቅ ባልለመሆኑ ሁላችንም በሃገራችን አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከግጭት ይልቅ እርቅን፣ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፣ ለእኔ ብቻ ከሚል ክፉ አስተሳሰብ ለእኛ ማለትን፣ ከንቀት ይልቅ መከባበርን፣ ከልባችን በመምረጥ በአስተማማኝ ሰላሟ ተምሳሌት የሆነች እና ያደገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁላችንም በቅን ልቦና እንድንሰራ በፈጣሪ ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
በተለይም በየደረጃው የምትገኙ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ፈጣሪ እና ሃገር የጣሉብንን ታላቅ ኃላፊነት እና አደራ ሰላምን በመስበክ እና በመጠበቅ፣ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ የተቸገሩትን በመርዳት እና ፍትህ ላጡ እና ለተበደሉ ወገኖቻችን ድምጽ በመሆን ከምን ጊዜውም በላይ እንድንሰራ አደራ ለማለት እንወዳለን፡፡
በመጨረሻም አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የምሕረት፣ የርህራሄና፣ የአንድነት እና የመረዳዳት ዓመት እንዲሆንልን በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ስም እየተመኘን በዓሉን ስናከብር በተለመደው ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህል የተቸገሩትን በመርዳት እና በአዲሱ ዓመት በሃገራችን የተሟላ ሰላም ይሰፍን ዘንድ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት ቃል በመግባት እንዲሆን በፈጣሪ ስም አደራ ለማለት እንወዳለን፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ/ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ