መስከረም 2/2017 ዓ/ም
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
በዕለቱ በዐውደ ምህረት በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በሰ/ት/ት ቤት መዘምራን ያሬዳዊ ወረብ ቀርቧል። የዕለቱን ትምህርት መጋቤ ምሥጢር ኢሳይያስ ገብረ መድኅን የሀዋሳ ደብረ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ”ምቹ ቀን”ማር 6፥21 በሚል ርእስ ተነስተው ዛሬ ታሪኩን የምንተርክለት ዮሐንስ አባቱን በቤተ መቅደስ ሲያጣ እናቱንም በበረሃ በሞት እንዳጣ ታሪኩ ይነግረናል።
በበረሃ ያደገው ዮሐንስ ወጥቶ ማስተማር ጀመረ። በዚያ ወቅት የዘመኑ ባለ ጊዜ ሄሮድስ የወንድሙን ሚስት ሊያገባ ፈልጎ ዮሐንስ የወንድምህን ሚስት ማግባት አይገባህም በሚል ስለከለከለው ሄሮድስ ይታወክ ነበር። ባሏ የሞተባት ሄሮድያዳም የባሏን ወንድም አግብታ የንጉሥ ሚስት መባልና ዝና ፈልጋ ስለነበር ዮሐንስ እንቅፋት ሆኖባታል። ሄሮድስ ልደቱን በሚያከብርበት ቀን ግን የሄሮድያዳ ልጅ በዘፈኗ አስደሰተችው። ሄሮድስም የምትፈልጊውን ሁሉ አደርግልሻለሁ ብሎ ማለላት።
የሄሮድያዳ ልጅም ወደ እናቷ ሄዳ ንጉሥ የምንግሥቱን እኩሌታ ሳይቀር ሊሰጠኝ ቃል ገብቶልኛል ምን ልጠይው? አለቻት ሄሮድያዳም የመንግሥት እኩሌታ ምን ያደርግልሻል ጠላታችን ዮሐንስ ነው እርሱ ቢሞት እኔ የንጉሥ ሚስት አንቺ የንጉሥ ልጅ ሆነን እንኖራለን። ስለዚህ የዮሐንስን ራስ ጠይቂው በማለት መከረቻት በዚህ ምክንያት የዮሐንስን ራስ ቆርጦ ሰጣት። ዮሐንስም በክብር አረፈ ሄሮድያዳን ግን መሬት ተከፍታ ዋጠቻት።
ዛሬም የእኛ ደስታ ለሌሎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል በማለት ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። በመጨረሻም የወረዳው ዋና ሥራ አስኪያጅ ላዕከ ወንጌል ቀሲስ ደግፌ ባንቡራ አባታዊ መልእክት አስተላልፈው በደብሩ አስተዳዳሪ በመልአከ መንክራት ቆሞስ አባ ወልደ ሰንበት አባቡ ጸሎትና ቡራኬ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።
መረጃውን ያደረሰን የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ነው።