መስከረም 16/2017 ዓ/ም
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
በበዓሉ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ ሀገረ ስብከትና የታቦር ፍኖተ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣መጋቤ ሃይማኖት አባ አብርሃም የቅዱስ ሲኖዶስ ምክትል ጸሐፊ፣ ክቡር መኩሪያዬ መርሻዬ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ፣መጋቤ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ መርጊያ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣መጋቤ ሥርዓት ዳንኤል ጌታቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሕዝብ ግንኙነት መመሪያ ዋና ጸሐፊ፣ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት፣የሀገረ ስብከቱ የየመምሪያ ኃላፊዎች፣ላዕከ ወንጌል ደግፌ ባንቡራ የሀዋሳ ከተማና ዙሪያ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን፣ ምእመናንና ምእመናት የተገኙ ሲሆን ጸሎተ ወንጌል ከተደረሰ በኋላ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያሬዳዊ ወረብ ቀርቦ በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ያሬዳዊ ወረብና መንፈሳዊ ትርኢትቀርቧል።

በመቀጠል የሀዋሳ ወረዳ ዋና ሥራ አስኪያጅ ላዕከ ወንጌል ደግፌ ባንቡራ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈው የሀገረ ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት ሞላልኝ መርጊያን ጋብዘዋል። የሲዳማ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ መርጊያ በዓሉን የምናከብርትን መሠረታዊ ምክንያት አንስተዋል በዚህም ውስጥ በክርስቶስ መስቀል ሰላም መደረጉን ደመራው ዕሌኒ መስቀሉን ለመፈለግ ያደረገችውን የሚያሳይ ነው የሚል መልእክት አስተላልፈው ብፁዕነታቸውን የዕለቱን ትምህርት እንዲያስተምሩና አባታዊ ቡራኬ እንዲሰጡ ጋብዘዋል።

ብፁዕ አባታችን አቡነ ዮሴፍ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈው መስቀሉ ተገኘ በሚል ተነስተው መስቀል ክርስቶስ ለሰው ልጆች የባሕርይ ፍቅሩን የገለጠበት ለሰው ልጆች ደሙን ያፈሰሰበት ጠላት ዲያብሎስን ድል የነሳበት ስለሆነ በካህናት እጅ ይያዛል በቤተ ክርስቲያን ምልክት ሆኖ ይቀመጣል በልብሳችን ከዚያም አልፎ በሰውነታችን ምልክት እናደርገዋለን። በሕይወት እያለን ብቻ አይደለም በመቃብራችንም ሳይቀር ምልክት ይደረጋል።ምክንያቱም እኛ ሕይወት ያገኘንበት ጠላት ዲያብሎስ የተሸነፈበት ስለሆነ።

ስለዚህ መስቀል ሰላም ያገኘንበት ስለሆነ መስቀል ላይ የዋለውን ክርስቶስን ስናይ የሰላም ሰዎች እንሆናለን።
ታዲያ ለምንድንነው የማንግባባው ካልን ከመስቀሉ ላይ ዓይናችንን ስናነሳና መስቀል ላይ የዋለውን ክርስቶስን ስንረሳ ነው።በጥቅሉ በክርስቶስ የፈረሰውን የጠብ ግድግዳ መልሰን መገንባት የለብንም የሚል ሰፊ ትምህርት አስተምረዋል። በመቀጠል የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈው በብፁዕነታቸው ጸሎት መርሐ ግብሩ ተጠናቋል።

መረጃው የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ነው።