ጥቅምት 2 ቀን 2017ዓ.ም.
+ + +
በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ በሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ተዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ የሰንበት ት/ቤቶች ወጥ ሥርዓተ ትምህርት ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተዘጋጅቶ በትግበራ ላይ ነው። በዚህም ሥርዓተ ትምህርት በሁሉም አህጉረ ስብከቶች የሚገኙ የሰንበት ት/ቤቶች በማስተማር መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን እንዲፈጽሙ በብጹእ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅና የባሕርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ አባታዊ መመሪያ ተላልፎ 4ኛ፣6ኛ እና 10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የሰንበት ት/ቤት አባላት በየሀገረ ስብከታቸው እየተመረቁና የምስክር ወረቀት የሚሰጣቸው ሲሆን በሥርዓተ ትምህርቱ መሠረት 12ኛ ክፍል ሲያጠናቅቁ በመንበረ ፓትርያርክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የማጠቃለያ ፈተና ተሰጥቷቸው የሚመረቁ ይሆናል።

በዚሁም መሠረት በስድስት ክፍለ ትምህርቶች የተዘጋጁ ትምህርቶችን በሦስት ሀገረ ስብከትና በ8 አጥቢያ ሰንበት ት/ቤቶች ሲከታተሉ የነበሩና 12ኛ ክፍል ያጠናቀቁ 183 ወጣቶች ለኹለተኛ ጊዜ ዛሬ ጥቅምት 02ቀን 2017 ዓ.ም ብጹእ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕርዳርና ምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣ ብጹዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ተመራቂ አባላት ቤተሰቦቻቸውና የሰንበት ት/ቤት አመራሮች የማደራጃ መምሪያው ኃላፊና ልዩ ልዩ ሰራተኞች የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮች በተገኙበት ተከናውኗል።

በመርሐ ግብሩ መልእክት ያስተላለፉት ብጹእ አቡነ በርናባስ የዋግኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የቤተክርስቲያን ተተኪዎች፣ ጌጦቿ ናቸውና በትኩረት ሊያዙ ይገባል ብለዋል። በመቀጠልም ብጹእ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕርዳርና ምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በመልእክታቸው በመጽሐፈ ምሳሌ ፱፥፱ “ለጠቢብ ሰው ትምህርትን ስጠው፥ጥበብንም ያበዛል ጽድቅንም አስተምረው፥ዕውቀትንም ያበዛል።” የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ አድርገው ቤተክርስቲያን ሃይማኖትን ዶግማን ቀኖናና ሥርዓትን አስተምራችኋለችና እድለኞች ናችሁ፤ ብዙዎች የሚመኙትን እድል እናንተ አግኝታችኋል፤ በዚህ ባገኛችሁት መንፈሳዊ ትምህርት ለቤተክርስቲያን የምትጠቅሙ እንድትሆኑ አደራ እላለሁ ያሉ ሲሆን ለተመራቂዎች ፣ለማደራጃ መምሪያውና ለሰንበት ት/ቤቶች አንድነቱ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል ። በመጨረሻም የተጀመረው የመጻሕፍት ዝግጅትና ሕትመት እንዲቀጥል አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል።

በመርሐ ግብሩ መዝሙር ፣መነባንብ፣ ቃለወንጌል ከተሰጠ በኋላ በብፁዓን አባቶች ለተመራቂዎቹ ና ለሀገረ ስብከቶቹ ሰርተፊኬት እንዲሁም በከፍተኛ ውጤት ላጠናቀቁ አባላት የማስታወሻ ሽልማትና ዋንጫ በመስጠት ብፁዕ አቡነ ሰላማ የምዕራብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተው ጉባኤው በጸሎት ተጠናቋል።