ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፲ወ፯ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””””””””””
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
+++++++++++++
በመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽርሐ ተዋህዶ አዳራሽ “ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት”በሚል መሪ ቃል በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ከትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያዎች ጋር በመቀናጀት የምክክር ጉባኤ አዘጋጀ።

ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም በተዘጋጀው በዚህ ጉባኤ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል።

መርሐ ግብሩም በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎተ ቡራኬ የተከፈተ ሲሆን ቅዱስነታቸውም የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ቤተ ክርስቲያን የምትጠበቀው በካህናትና በምዕመናን ነው ያሉ ሲሆን ለዚህም ቤተ ክርስቲያንን እና ሃይማኖታችንን ለመጠበቅ እየተሰበሰቡ መመካከር አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ወቅታዊውን የበሀገራችንን ሁኔታንም በማስታወስ አሳሳቢነቱን የጠቀሱት ቅዱስነታቸው ለዚህም ቤተክርስቲያንን ጠንክረን መጠበቅ አለብንም ሲሉ መክረዋል።

ይህችን ቤተ ክርክቲያን የሚቃረኗት ብዙ መሆናቸውንም ጠቅሰው ለዚህም ሁላችሁም ኃላፊነታችሁን ለመወጣት መሰል ጉባኤያት አስፈላጊም ኃላፊነትም ነው ሲሉ ቤተ ክርስቲያንን ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ነቅቶ መጠበቅ እንደሚያሻ አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዕለቱ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስም የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ሐዋርያትን በዓለም ዞረው ወንጌልን መስበካቸውን ጠቅሰው የሐዋርያትን ፈለግ የተከተለችው ቤተ ክርስቲያን በየዘመኑ ከመናፍቃን ጋር ያደረገችውን ተጋድሎም አንስተዋል።ለዚህም በዋቢነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ጉባኤያትን አንስተው አርዮስን፣መቅዶንዮስ እና ንስጥሮስን አውግዛ መለየትዋን ገልጸዋል።

ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋ ወንጌልን ተደራሽ ማድረግ እና ተልዕኮዋን እንዳትወጣ የሚያደርጓትን ችግሮችን መቅረፍ እና አውግዞ መለየት ነውም ሲሉ አክለዋል።

“ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት”በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ይህ ጉባኤ የስብከተ ወንጌልን እና የአብነት ትምህርትን ለማስፋፋት ያለመ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያ ዋና ኃላፊ መጋቤ ሐዲስ ኃይለ እግዚ አሰፋ ሲሆኑ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ መርሐ ግብሩ በጥምረት መዘጋጀቱ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንስተዋል።

ሁለቱም መምሪያዎች ቀደምት መሆናቸውንም ጠቅሰው ምንም እንኳ የተለያየ የሥራ ዘርፍ ቢኖራቸውም በስብከተ ወንጌል ረገድ ያላቸውን አንድነትም አብራርተዋል።

በመሆኑም ከወርሐ መጋቢት ጀምረው በጥምረት መስራት መጀመራቸውን ገልፀው ሊሰሩ ያሰቧቸውንም ዘርፈ ብዙ የሥራ መስኮችም በዝርዝርና በቁጥር አቅርበዋል።

መላከ ሰላም ቆሞስ አባ ቃለ ፅድቅ ሙሉጌታ (ዶ/ር) የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያም በበኩላቸው ጉባኤው ውጪያዊውን ችግሮች ለመፍታት የተዘጋጀ ሳይሆን ውስጣዊ ችግሮችን ለማየት እና ለመፈተሽ የተዘጋጀ ጉባኤ መሆኑን ገልጸዋል።

መላከ ሰላም “መንፈሳዊነት ለሁለንተናዊ አገልግሎት” በሚል ርዕስም ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን በጥናታዊ ጽሑፋቸውም የመንፈሳዊነትን ምንነት ዳሰዋል።

ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠው ትምህርት ትውፊታዊ መሆኑንም የጠቀሱ ሲሆን ያ ወንጌል ቀለም ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊነትንም የያዘ እና እኛም የወረስነው ነው ሲሉ መንፈሳዊነትን በተለያየ መልክ አብራርተዋል።

በመጨረሻም በቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፍ ዙሪያ ሰፊ ሀሳብ እና አስተያየት የተሰጠ ሲሆን በዋናነት በመምህራን ረገድ ያለው የእውቀት ክፍተት እና የመንፈሳዊነት ዝለት ተነስቷል።

መርሐ ግብሩ በቀጣይም በየዓመቱ የሚዘጋጅ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በከሰዓቱም ውሎም የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡበት ሲሆን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ቤተ መጽሐፍትና ወመዘክር ጉብኝት የሚቋጭ መሆኑ ታውቋል።
በዕለቱም ብፁዓን አበው ላቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፤የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

መርሐ ግብሩ ለሁለት ቀናት የተዘጋጀ ሲሆን በነገው ዕለትም ቀጥሎ ይውላል።