የአቋም መግለጫ
“ዘአዘዞሙ ለአበዊነ፡፡ ከመ ይንግሩ ለደቂቆሙ፡፡ ወከመ ያእምር ካልእ ትውልድ፡፡ ደቂቅ እለ ይትወለዱ ወይትነሥኡ፡፡ ወይዜንው ለደቂቆሙ፡፡” ለልጆቻቸው ያስታወቁ ዘንድ ለአባቶቻችን ያዘዘውን….የሚመጣ ትውልድ የሚወለዱም ልጆች ያውቁ ዘንድ ተነሥተው ለልጆቻቸው ይነግራሉ” መዝ 77 ቁ 5-6
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት ታሪካዊትና ሐዋርያዊት እንደመሆንዋ የዕለት ከዕለት ሥራዋንና አስተዳደርዋን የምታራምደው ቅዱሳን አበው ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በወሰኑት ፍትሕ መንፈሳዊ ነው፡፡
እምነትዋን የምታስፋፋበት፣የምታስተምርበትና የምታጸናበትን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ ተሰብስቦ በመምከር የጠመመውን በማቅናት የቀናውን በማጽናት በሚሰጠው ውሳኔና በሚያወጣው የሥራ መመሪያ መሠረት ነው፡፡
ይህን ውሳኔና መመሪያ አስፈጻሚው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በሥሩ በሚመራቸው መምሪያዎችና የሥራ ክፍሎች አማካኝነት፡-
የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዕልና በሁሉም ዘንድ እንዲታወቅና እንዲከበር ያደርጋል፣
ቤተ ክርስቲያን ባላት መብት መሠረት ሕልውናዋን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ይሠራል፣
ሕጓና ሥርዓትዋ እንዲከበር፣በአንድነትዋና በአላማዋ ጸንታ እምነቷ እንዲስፋፋ የሥራ ዕድገቷ ተፋጥኖ ግቡን ይመታ ዘንድ ዕለት በዕለት ይሠራል፣
ሕዝበ ክርስቲያኑ ማግኘት የሚገባውን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለማሟላት በሚቻልበት ጉዳይ በማተኮር ጉዳዮችን እየመረመረ በሥራ የሚተረጎሙበትን የሥራ አፈጻጸም መመሪያ ከሚሰጥባቸው መምሪያዎች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያና የትምህርት ማሰልጠኛ መምሪያ በጋራ “ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት” በሚል ርዕስ መምሪያዎቹ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሥራ መዋቅር የተጣለባቸውን ከባድ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ የጉባኤውን ተሳታፊዎች በሙሉ ደስ ያሰኘ ትልቅ ሥራ ከሰኔ 24 ቀን እስከ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ባሉት ዕለታት ሠርተዋል፡፡
የመርሐ ግብሩም አፈጻጸም በሚገባ ከዋናው መ/ቤት ከየአህረ ሰብከቱ ተመርጠው ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ በማድረግ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዩኒቨርሲቲዎች፣ኮሌጆች፣ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፤ከአዲስ አበባ ክፍላተ ከተሞች ከገዳማትና አድባራት የተመደቡ ሊቃውንት የአብነት ትምህርት መምህራን፣ሰባክያነ ወንጌል (ላዕካነ ወንጌል) በአጠቃላይ በምክክር ጉባኤው የተሳተፉ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት የሚያስገነዝብ ትምህርታዊ ጥናትና መወያያ ርእሶች ተቀርጸው የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ተልዕኮ ከሥልጠና እስከ ተልዕኮ ማስፈጸም ድረስ ያለውን ሐዋርያዊ ግልጋሎት ውስጣዊውን ገጽታ በዳሰሰ መልኩ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ መስክ በቂ ግንዛቤ ዕውቀትና ችሎታ ባላቸው ሊቃውተ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት የቆየውን ልምዳቸውና ዕውቀታቸውን አሁን ላይ ካለው አካሄዳችንና አገልግሎታችን አንጻር የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ለሆነው ሁሉ እኔ ማነኝ ብሎ መጠየቅ እስኪያስችል ድረስ በጥናታዊ ጽሑፍ የተደገፈ ትምህርት ተሰጥቷል፤በችግሩም ዙሪያ ያተኮሩ መጠይቆች ተነስተዋል፤ በመምህራኑም በቂ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶናል፡፡
ውይይቱም ሰፊና ጠቃሚ ሐሳብ ማሰባሰብ ያስቻለ ስለሆነና የምክክር ጉባኤው ተካፋዮችም በቅዱስነታቸው የተሰጠንን መመሪያና ቃለ ምእዳን ከብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ የተላለፈውን የሥራ አፈጻጸማዊ መመሪያ የጉባኤውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ሲመሩት ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሊቀ ጳጳስ የጉባኤ አመራርና ማብራሪያዎች ጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢዎች ከሆኑት ምሁራነ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠንን መመሪያና ከምክክር ጉባኤው ባገኘነው ጠቃሚ ትምህርት መሠረት የሚከተለውን ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡
ጉባኤያችን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተ/ሃይማኖት የተላለፈውን የመክፈቻ ቃለ ምዕዳን፣ከብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ የተሰጠውን የሥራ መመሪያና ጥናት አቅራቢዎች ያቀረቡትን ጥናታዊ ጽሑፎች በሥራ ለማዋል ቃል እንገባለን፣
ከቅዱስ ሲኖዶስ ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከዋናው መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሚወጡት ሕጎችና መመሪያዎች፣እንዲሁም ስለ ስብከተ ወንጌልና ትምህርትና ሥልጠና የሚተላለፉትን ትዕዛዞች በየአህጉረ ስብከቱና በቤተ ክርስቲያኗ ተቅዋማት ሁሉ በተግባር እንዲውሉ ቃል እንገባለን፣
እነዚህ መምሪያዎች የቤተ ክርስቲያኗን ሁለንተናዊ ተልዕኮ ለማሟላት የወሰዱትን የሥራ ተነሳሽነትና ኃላፊነትን በጋራ የመወጣት ልምዳቸው የሚበረታታ ስለሆነ በዚሁ መልኩ ተቀራራቢ የሆኑ የቤተ ክርስቲያኗ የሥራ መዋቅር ክፍሎች በጥምር የሚያስፈጽሙበት አሠራር መዘርጋት የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ተልዕኮ ስለሚያማክልና የጉባኤው ተሳታፊዎችም የምንደግፈው ስለሆነ በአፈጻጸም ረገድ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁነታችንን እንገልጻለን፡፡
የአብነት ት/ቤቶች እየተስፋፉ መሆናቸው ግልጽ ነው፤እነሱን ያግዙ ዘንድ የተቋቋሙት ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆችም በንባብ፣በቅዳሴ፣በዜማና በመጻሕፍት የትምህርት ዘርፍ እያደጉ የሚገኝበት ወቅት ስለሆነ ተመርቀው የወጡት ደቀ መዛሙርትም ከዋናው ማእከል ጀምሮ በየአህጉረ ስብከቱና ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቅዋማት በአገልግሎትና በኃላፊነት የሚገኙበት ወቅት ላይ መድረሳችን የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ዕድገቷን የሚያሳይ በመሆኑ አሁንም በየጊዜው በጥናት የተደገፈ ሥልጠና በመስጠት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላችን አስተዋጽኦ ለመወጣት ዝግጁነታችንን እንገልጻለን፡፡
ቋሚ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ትምህርት ለማጠናከር፤የመምህራንና የደቀ መዛሙርትን ኑሮ ለመደገፍ በየአካባቢው በየአህጉረ ስብከቱ በቂ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ዘገባዎች ቢያመለክቱም በውስጣዊ የአመራርና ውጫዊ ሁኔታዎች አንዳንድ ችግሮች የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መምህራንን ለፍልሰት እያደረጉ ስላሉ ለወደፊቱ መምህራኑ በየአካቢያቸው ወንበራቸውን አጽንተው ደቀ መዛሙርቶቻቸውን በሁለንተናዊ ስብእና ክብር አስታጥቀው እንዲያወጡ በመሥራት የበኩላችንን አደራና ኃላፊነት እንወጣለን፡፡
የቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ ትምህርት ዜማ፣ቅዳሴና ቅኔና ትርጓሜ መጻሕፍት የሚማሩ ደቀ መዛሙርት ለትምህርተ ወንጌልበአርያነት ለሚጠቀስ ለመንፈሳዊ አስተዳደር ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች ጊዜውን የዋጀ መምህራን ለማግኘት የሥርዓተ ትምህርት ዳሰሳዊ ጥናት የቤተ ክርስቲያኗን ባለሙያዎችና ሌሎች አጋዥ ኃይሎች በማሳተፍ እንዲቀርብ በተደጋጋሚ በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነ ስለሆነ እነዚህ ሁለቱም መምሪያዎች ሆኑ ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች ተባብረውበት ማኅደረ ጉዳዮች ታይተው የቀሩትን ተግባራት ወደ ሥራ ለማስገባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝና ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ምንጊዜም ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ያላቋረጠች መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷም በውጭው ዓለም በሚገኙ ክፍላተ ዓለማት ጭምር መስፋፋቷ በእግዚአብሔር ረድኤት እየቀጠለ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያኗ ወገኖች የሆን ውሉደ ክህነትና ውሉደ ክርስቲያን ለሐዋርያዊ ተልዕኮዋ መፋጠን የእምነት ተከታዮቿንም ምእመናን ለመጠበቅ የጋራ አሠራር በያዘ መልኩ በውስጣዊና ውጫዊ አሠራራችንና ግንኙነታችን ሁሉ ከመምሪያዎቹም የሚተላለፉ የሥራ መርሐ ግብሮችን ለማስፈጸም ቃል እንገባለን፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት የሰጠውን ታላቁን ሐዋርያዊ ተልእኮ ተቀብላ በሐዋርያት አሠረ ፍኖት ተገብታ በባለቤትነት ታስፈጽማለች። ነገር ግን ከእኛ ከአገልጋዮች የእውቀት እና የቁርጠኝነት ማነስ እንዲሁም ከአንዳንዶቻችን ጥቅም ተኮር እንቅስቃሴ የተነሳ ይህንን ታላቅ ተልእኮ ለመፈጸም የተቸገርን ቢሆንም ከዚህ በኋላ በተቻለን መጠን ለመማር፣የተማርነውን ለማስተማር ፣ለማሳመን፣ ከመንጋው ለመቀላቀልና ለመንከባከብ በሚደረገው ማንኛውም ጥረት ከቤተክርስቲያን ጎን ለመቆም ቃል እንገባለን።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለሀገራችን ለዘመናት ሃይማኖትንና ታሪክን ስታስተምርና ስትዘግብ ብራና ዳምጣ፣ቀለም በጥብጣ፣የራሷን ፊደል ቀርጻ፣ የራሷን ቀመር ቀምራ ለቁጥር የሚያዳግቱ መጻሕፍትን ጽፋለች፤ እየጻፈችም ነው። ነገር ግን አባቶቻችን የጻፏቸው መጻሕፍት በየገዳማቱ ግምጃ ቤት ሆነው ለጉብኝት አገልግሎት ከመዋል ባሻገር ለጥናትና ምርምር ክፍት ተደርገው ለማኅበረሰቡ መድረስ ባለመቻላቻው በዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ወገኖች ቤተክርስቲያንን መጻሕፍት አልባ ከማስመሰሉም በላይ የትምህርት ተቋማቶቻችን የአባቶቻችን ወዝ ባልካቸው መጻሕፍትና ታሪክ አልባ ተሞልተዋል የሚል ስሞታ እንዳለ ተገልጿል፤በመሆኑም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ቤተ ክርስቲያን ለምታደርገው ጥረት ጥናትና ምርምር በመሥራት በሁሉም ዘርፍ ከቤተክርስቲያን ጎን ለመቆም ቃል እንገባለን።
ቅድስት ቤተክርስቲያን የሁሉ እናት እንደመሆኗ መጠን ዘር ቀለም ጎሳ ሳትለይ እናቴ ብሎ የመጣውን ሁሉ አቅፋ የያዘች፣ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ከመሆኗ ባሻገር የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የምታቀብል መሆኗ የሚታወቅ ነው፤ነገር ግን ከላይ እስከታች የምንገኝ የቤተክርስቲያን ኃላፊዎች በጠረፋማ ሥፍራ የሚኖሩ ሰዎችን ወንጌል ለማስተማር የምናደርገው ጥረት ጅምሩ የሚበረታታ ቢሆንም ፍጹም ሥራ መሥራትን፣ ለሌሎች ዓለማትም መትረፍን የሚጠይቅ ተግባር መሆኑን በጉባኤው ከተሰጠው ዐውደ ጥናት ተረድተናል፤ በመሆኑም እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሁሉ እናትነት መላልሶ ለማስተማርና ለመላላክ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ቃል እንገባለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ