በሥልጠናው መዝጊያ ላይ የተገኙት ብጹዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በህዝብ ግንኘነት አስፈላጊነትና ለቤተክርስቲያን ያለውን ፋይዳ በዝርዝር ገልጸው ቤተክርስቲያን በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ዘመኑን የዋጀና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

አያይዘውም ቤተክርስቲያን በዚህ ዘመን የመረጃ እጦት ሊገጥማት እንደማይገባ ገልጸው በህዝብ ግንኙነት በኩል ቤተክርስቲያን ከህዝበ ክርክቲያኑ፣ከሌሎች የእምነት ተቋማት፣ከመንግስት ና ከውጭ ሀገር ዲፕሎማት ጋር የሚኖርን ግንኙነት የሚያጠናክር በመሆኑ ከፍተኛ ኃላፊነት መሆኑን ተገንዝባችሁ ሥራችሁን ከተሰጣችሁ ስልጠናና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ህግጋት ጋር በማስተሳሰር ጠንክራችሁ መስራት ይኖርባችኋል ብለዋል።

ከብፁዕነታቸው የመዝጊያ ንግግር ቀደም ብሎ የጠቅላይ ቤተክህነት የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ዋና ኃላፊ ሊቀ ትጉሃን እስክንድር ገብረክርስቶስ ባደረጉት ንግግር ቤተክርስቲያናችን የጣለችብን ኃላፊነት እጅግ ከባድ መሆኑን በመገንዘብ ለጊዜያዊ ችግሮችና ፈተናዎች ሳንንበረከክ የህዝብ ግንኙነት ሥራችንን በአግባቡ መስራት ይኖርብናል። ካሉ በኋላ ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ በመጠቀምና በተቻለ አቅም ሁሉ በመንቀሳቀስ ፣የግንኙነት አድማሳችንን በማስፋፋት እና ሁሉንም የቤተክርስቲያኒቱን መዋቅር በመጠቀም ሥራዎቻችንን በኃላፊነት መንፈስ ለመወጣት ዝግጁ መሆን ይኖርብና ብለዋል።

አያይዘውም በስልጠናው ያገኘናቸውን እውቀቶች ከቤተክርስቲያኒቱ ህግጋት ጋር በማጣጣም ውጤታማ ሥራ እንደምንሰራም እምነቴ የጸና ነው ብለዋል።

በመጨረሻም ብጹዕነታቸው ቃለ በረከትና ቡራኬ በመስጠት የሥልጠና መርሐ ግብሩ ተጠናቋል ።