በዘርፈ ብዙ የቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲያደርግ የቆየው 14ኛው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ በቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ እና ባለ 12 አንቀጽ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል ።
+ + +
ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም.
ከሉላዊነት (Globalization) ጋር አንገት ለአንገት እየተናነቀ ወጣቱን ዓርነት ለማውጣት አየሠራ የሚገኘው ሀገር አቀፍ የሰንበት ትምርህት ቤቶች አንድነት ጉባኤ ለ14ኛ ጊዜ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ አያደረገ ነው። 14ኛው ሀገር አቀፍ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ ከመላ ሀገሪቱ የተሰበሰቡ የሰንበት ትምርህት ቤቶች ማደራጃ ክፍል ኀላፊዎች ፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ ተቀዳሚ ምክትሎችና ምክትሎች የሚሳተፉበት ሲሆን ትናንት ግንቦት 30 ቀን 2017ዓ.ም በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሀገር አቀፍ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ ዓመታዊ ሪፖርት በማድመጥ ተጀምሯል ። በመቀጠልም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ የብፁዕ አቡነ ሳዊሮስን አባታዊ መልእክት አድምጧል ። ጉባኤው የአህጉረ ስብከት ጠቅለል ያለ ዓመታዊ ሪፖርት ካደመጠ በኋላ ከላይ በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ውይይት አድርጓል።
ከውይይቱ በመቀጠል የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ ሦስተኛውን ስልታዊ እቅድ ትግበራ ላይ የውይይት መነሻ ሐሳብ ቀርቦ ጉባኤው ተወያይቶበታል። ጉባኤው ዛሬ ሰኔ 1 ቀን 2017ዓ.ም. የቀጠለ ሲሆን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ሱታፌ ለቤተክርስቲያን፣ የአንድነቱ የትኩረት አቅጣጫዎች ማለትም በየወረዳው የአደንድነት ጉባኤዎችን ማጠናከር ፣ያልታተሙ መጻሕፍቶችን ለኅትመት ማብቃት ፣ስርዓተ ትምህርቱን ሁሉም ቦታ ተደራሽ ማድረግ ፣ስልጠናዎችን ማዘጋጀት የውስጥ መመሪያዎችን መደንገግ ሚዲያና ቴክኖሎጂ በማበልፀግ ማናበብ መቻል እና በአቋም መግለጫ የቀረበውን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ መሆኑ ተገልፆ በሀገረ ስብከት ተወካዮች የቀጣይ ዓመት ትግበራዎች ላይ ውይይት አድርጓል። ከውይይቱ በተጨማሪም ብፁዓን አባቶች ትምሀርተ ወንጌል ሰጥተዋል።
ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምሕሮ መሠረት ታትሞ ለኅትም የበቃው ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል የመማሪያ መጽሐፍ በዘንድሮው ዓመት በአፋን ኦሮሞ እና ከ5ኛ እስከ 7ኛ ክፍል የሚያገለግል የመማሪያ መጽሐፍም በአማርኛ ታትሞ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑ ተብራርቶ ለምርቃቱ ግን ልዩ ዝግጅት ለማዘጋጀት እንደታሰበ ተገልጿል።
በመጨረሻም ጉባኤው በአቋም መግለጫው በልዩ ልዩ ሥፍራ የተፈጠሩ ልዩነቶች በእረቀ ሰላም እንዲፈቱ እና የመሪ እቅድ ትግበራው ተፈጻሚ እንዲሆን በአጽንዖት ጠይቋል።
የጉባኤን በሰላም መጠናቀቅ ተከትሎ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሰጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በዓለ ጰራቅሊጦስ ቤተክርስቲያን የተሠራችበት እና ሐዋርያት ኃላፊነት የተቀበሉበት ልዩ ቀን መሆኑን ገልጸው በዚህ ቀን ወጣቶች ከቤተክርስቲያን ኃላፊነት ለመውሰድ በየዓመቱ መሰብሰባቸው መልካም ነው ብለዋል። በቤተክርስቲያን አላስፈላጊ ነፋስ እንዳይገባ ተግቶ የሚጠብቀው የሰንበት ትምርህት ቤት ወጣቶች መሆናቸውንም አክለው ገልጸዋል።
ቅዱስነታቸው በአቋም መግለጫው ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ሰላምን ማስፈን የዘወትር ጸሎቴ ነው። ነገር ግን ብቻየን የማደርገው አይደለም። በሁሉም በኩል ለሰላም የሚከፈለውን ዋጋ መክፈል ይጠይቃል። ነገር ግን በእኔ በኩል የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ያሉ ሲሆን እንደ ዓይን ብሌን የምንመለከተውን መሪ እቅድም ተፈጻሚነት እንዲኖረው የበኩሌን ጥረት አደርጋለሁ ብለዋል።