ታሕሳስ 13 ቀን 2017ዓ.ም.
የጋምቤላ ክልልና የደቡብ ሱዳን፣ የቤኒሻንጉል ክልል ፣የምዕራብ ወለጋ፣ የምስራቅ ወለጋ ፣ የሖሮ ጉድሩ እና የቄለም ወለጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ከጥቅምቱ የ43ኛው አጠቃላይ የሰበካ ጉባኤ ስብሰባና ከጥቅምቱ ሲኖዶስ በኋላ የተዘጉ አቢያተ ክርስቲያናትን ለማስከፈት እና የአገልግሎት ነዋየ ቅድሳት የሌላቸውን 200 አቢያተ ክርስቲያናትን ለመደገፍ፣ አሳዳጊ ወላጅ የሌላቸውን ህጻናት እና ጧሪ አልባ አረጋውያንን ለመርዳት በአዲስ አበባ እና በውጪ ሀገር ከሚገኙ የነፍስ ልጆቻቸው ሲያስተባብሩ ቆይተው በዛሬው እለት ወደ ሀገረ ስብከታቸው አቅንተዋል።
የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት በሰጡን መረጃ እስከ ታሕሳስ 30 ቀን 2017ዓ.ም. ድረስ ባሉ ተከታታይ ቀናት በአራቱ ወለጋዎች ሕገ ቤተክርስቲያንን እና የመዋቅር አንድነትን አስመልከቶ ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቀሰዋል። በመቀጠልም በቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከት በደምቢደሎ ከተማ የሚሠራው የቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያንን የማሳለጥ ሥራ ይሠራል ብለዋል።
የታሕሳስ ገብርኤልን፣ የታሕሳስ ተክለሃይማኖትንና ልደትን በአራቱ ወለጋዎች ላይ ተዘዋውረው እንደሚያከብሩ በመግለጽ አሁን በዚህ ሰዓት የሰባቱ አሁጉረ ስብከት የሥራ ኀላፊዎች ከብፁዕነታቸው መመሪያ ለመቀበል እና ብፁዕነታቸውን እንኳን ደህና መጡ ለማለት በቄለም ወለጋ መንበረ ጵጵስና እንደሚገኙ ገልጸዋል። ብፁዕነታቸውም በእኩለ ሌሊት በመኪና የጀመሩትን ጉዞ በሰላም በማጠናቀቅ በቄለም ወለጋ መንበረ ከጵጵስናቸው ተገኝተው ሐዋርያዊ ጉዟቸውን አንድ ብለው የጀመሩ ሲሆን በጉዟቸው በሀገረ ስብከታቸው ሥር እና በመንገዳቸው ላይ ያሉ አቢያተ ክርስቲያናትን እየጎበኙ ከነፍስ ልጆቻቸው ያስተባበሩትን ለአገልግሎት የሚሆን ልብሰ ተክህኖ፣ ጧፍ ፣ እጣን እና ዘቢብ እየሰጡ አመሻሹ ላይ ወደ መንበረ ጵጵስናቸው በሰላም ገብተዋል ። በቀጣይም በየወረዳው ይህ ጉብኝትና ልገሳ እንደሚቀጥል የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ገልጸዋል።