መንፈሳዊ ፍርድ ቤት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሀገር አቀፍ ደረጃ በብሔራዊ ሃይማኖት በነበረችበት በቀድሞው ዘመነ መንግስት ቤተክርስቲያኒቴ ያሏትን መንፈሳዊ እሴቶች ፣ ባህሎችና አስተምህሮዎች በወቅቱ በነበረው ሥርዓተ መንግሥት መዋቅራዊ አደረጃጀት ውስጥ ማስረጽ ችላ ነበረ፡፡
ለአብነትም ያህል የቤተክርስቲያኒቱ ሕግ የሆነው ፍትሐ ነገሥት የሀገሪቱ የበላይ ህግ ሆኖ ከማገልገሉም በተጨማሪ በወቅቱ በመንግሥታዊ ,ፍርድቤቶች በዳኝነት ተመድበው ፍትሕ ና ርትዕ ይሰጡ የነበሩት የቤተክርስቲያኒቱ የፍትሐ ነገሥት መምሕራንና ሊቃውንት እንደነበሩ በልዩ ልዩ የታሪክ ድርሳናት ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡
ለአብነትም ያህል ለ900 ዓ.ም በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የመጀመሪያው የመንግስት ፍርድ ቤቶች መዋቅራዊ አደረጃጀት፣ የአፈር ዳኛ ፣የአከል ዳኛ፣ሻለቃ ፍርድ ቤት፣ አፈ ንጉስና ንጉሰ ነገሥት፣ዙፋን ችሎት በማለት አዲስ መዋቅራዊ አደረጃጀት በተሠራበት ወቅት መዋቅራዊ አደረጃጀትን በመሥራትና በእያንዳንዱ የዳኝነት መዋቅር ውስጥ የቤተክርስቲያኒቱ የፍትሐ ነገሥት መምህራን ተመድበው በመሥራት ዛሬ አደገ ተመነደገ ተብሎ የሚነገርለትን የፍትሕ ሥርዓት ከዚህ ደረጃ እንዲደርስ ከጽንሰቱ እስከ ውለደቱ ብሎመ እስከ እድገቱ በቤተክርስቲያኒቱ እንቁ ሊቃውንት ልጆች አማካኝነት እሰከ ዓለም ፍጻሜ ሲዘክረው የሚኖር አኩሪ ታሪክ የሠራች እናት ቤተክርስቲያን መሆኗን እንኳንስ እኛ ልጆቿ ይቅርና የማያምኑትን እንኳን ሳይቀሩ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ በማጽናት እራሷ ሀገር የሆነች እናት ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ዘወትር በየአደባባዩ በኩራት ሲመሰክሩላት ይገኛል፡፡
የመንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች ታሪካዊ ዳር
ፍርድ ቤቶች የሰውን ልጅ መብት ለማስከበሪያ ዜጎች መብቶቻቸውን በተጣሱባቸውና ባልተከበሩባቸው ወቅት ይህን የመብት ጥሰት ከሀገሪቱ ሕጎች ድንጋጌ አንጻር መርምረውና ተመልክተው ፍትሕና ርትዕ ለመስጠት መሆናቸው አጠያያቂ አይደለም ፡፡
ከላይ የተገለጸው የመንግሥታዊ የዳኝነት ሥርዓት መዋቅራዊ አደረጃጀት እንደተጠበቀ ሆኖ በመንግሥታዊ የዳኝነት ሥርዓት ሊሸፈኑ የማይችሉትን የዳኝነት ዓይነቶችን ደግሞ መንፈሳዊ ነክ የሆኑትን በመንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች ባህል ነክ የሆኑትን ጉዳዮች ደግሞ እንደየአካባቢው ወግና ሥርዓት በባህላዊ የዳኝነት ሥርኣት እንዲታዩ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት አሁን የምንያቸው በየደረጃው ያሉት መንፈሳዊ ፍርድቤቶች ሊቋቋሙና ሊመሰረቱ ችለዋል፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ አሁን ላለነው ትውልድ ተላልፈው ዛሬም ድረስ ፍትሕ ና ርትዕ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ይህንንም መሠረት አድርጎ በአሁኑ ሠዓት የሀገሪቱ የበላይ ሕግ በሕገ መንግስቱ እውቅና የተሠጣቸው መሆኑና የመቋቋሚያ አዋጅ ጥያቄ ሲቀርብም በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ የሕዝብ እንደራሴ ምክርቤቶች በመቋቋሚያ አዋጅ እንዲቋቋሙ የማድረግ ሐላፊነት ያለባቸውን ስለመሆኑ ለሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78/5/ ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
ይሁን እንጂ ምንም እንኳን መንፈሳዊ ፍርድ ቤቾች ሕገ መንግስታዊ ዕውቅና ያላቸው ቢሆንም የኤፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስከ አሁን ድረስ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች የማቋቋሚያ አዋጅ ባለመፍቀዱ ለዘመናት በርካታ ፍትሕና ርትዕ ሲሰጥባቸው የቆዩ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶቻችን ጥርስ የሌለው አንበሣ ሆነው እነኳንስ በመንግሥታዊ አስፈጻሚ አካላት ዘንድ ይቅርና በራሷ በቤተክርስቲያኒቱ በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚ አካላት ዘንድ በማስፈጸም አስቸጋሪ መንፈሳዊ ፍርድቤቶቻችን በመኖርና ያለመኖር ሥጋት ውስጥ ወድቀው ይገኛሉ፡፡
በመሆኑም ይህ ለመንፈሳዊ ፍርድቤት ተግዳሮት የሆነውን የማቋቋሚያ አዋጅ በኤ.ፌ.ድ.ሪ.የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለማጽደቅ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቶ በአሁኑ ሰዓት ረቂቅ አዋጁን አዘጋጅተን እንድናቀርብ በምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ በተሰጠው አመራር መሠረት የአዋጁን ረቂቅ በብቁ የሕግ በላሙያዎች ተዘጋጅቶ ለቅዴስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ በአጀንዳነት ተይዞ ይገኛል በመቀጠል በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራት ዝርዝር ሪፖርት በአጭሩ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡