“ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በደረሰባት የውስጥ ፈተና ሀዘኗ ከባድ ነው።” ብፁዕ አቡነ አብርሃም
“ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በደረሰባት የውስጥ ፈተና ሀዘኗ ከባድ ነው።” ብፁዕ አቡነ አብርሃም
ብፁዕ አቡነ አብርሃም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ይህን የገለጹት በዛሬው ዕለት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ የተፈጸመውን “የጳጳስ ሹመት” አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ነው።
ብፁዕነታቸው እንደገለጹት በፈተና የሚያጸናው ሁል ጊዜ ፈተናዎችን እያሳለፈ ለዘመናት ሲጠብቃት የነበረ እግዚአብሔር ዛሬም ጥበቃውና መግቦቱ እንደማይለያት ሙሉ እምነት አለን። በደረሰው ክስተትም እጅግ አዝነናል ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ታዝናለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ3ሺ ዘመን በላይ የራሷን አንድነት ከማስጠበቅ አልፋ የሀገርን አንድነት ስታስጠብቅ ለሰው ልጆች አንድነት ትልቁን ድርሻ በመውሰድ ስትሠራ የኖረች አሁንም ያለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነች በማለት ገልጸዋል።
ይህንን አንድነቷን የሚንድ ሕጋዊ ሰውነቷን የሚጥስ አላስፈላጊ ክስተት ተፈፅሟል። በዚህም ቅዱስ ፓትርያርኩ በአስተላለፉት ጥሪ መሠረት ከሀገር ውስጥ ከሀገር ውጭ የምትገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከነገው ዕለት ጀምሮ የቅዱስነታቸውን ጥሪ በመቀበል እንድትገኙ በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም የተፈጠረውን ችግር በዝርዝርና በጥናት ቅዱስ ሲኖዶስ አይቶ የመጨረሻውን ውሳኔ እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ ምእመናንና አገልጋዮች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሁላችሁም በየአላችሁበት ቤተ ክርስቲያንን እንድትጠብቁ ሲሉ አሳስበዋል። ተመሳስለውና የሌለ ሀሳብ እያቀረቡ ሕዝብን ከሚለያዩ ሠዎች እንድትጠበቁና እንድትጠብቁ በጽናት፣ በትእግስትና በፍቅር ሕጋዊ በሆነ ነገር ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን እንድትጠብቋት በአንድነቷ የተረከብናትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአንድነቷ ለነገው ትውልድ ለማስረከብ የእያንዳንዳችንን ድርሻ እንድንወጣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ብለዋል።
በመጨረሻም ሕጋዊ ሰውነቷ የተረጋገጠ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በሕጋዊ ሰውነቷ የመጠበቅ የማስጠበቅ ኃላፊነቱ የመንግሥት ስለሆነ ይህን የተፈጸመውን ግፍ መንግሥት ተመልክቶ የቤተ ክርስቲያኗን ሉዓላዊነት በመጠበቅና በማስጠበቅ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም ጥሪ አቅርበዋል ።