ሚያዚያ ፳፮ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
****
አዲስ አበባ -ኢትዮጵያ
***
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ቅጽረ ጊቢ ውስጥ በመገንባት ላይ የሚገኘው ዓለም አቀፍ ሁለገብ አዳራሽ ባለፈው ሁለት ዓመት ከስድስት ወራት በግንባታ ላይ እንደሚገኝና በአሁኑ ጊዜ የግንባታ ሥራው ፹፯ ፐርሰንት የተጠናቀቀ መሆኑን የግባታ ሥራው አማካሪ ድርጅት ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አስተዳደር ጉባኤ ባቀረበው የግንባታ ሥራ አፈጻጸም ሪፖርተርት ገልጿል።
አዳራሹ ከሁለት ሺህ አምስት መቶ በላይ ታዳሚዎችን የሚይዝ ዘመናዊው ዓለም የደረሰበትን ግብዓቶችን ያሟላ ሁለገብ አንድ አዳራሽ፣መካከለኛ የኮንፈረንስ ክፍሎችን፣መለስተኛ አዳራሾችን፣ቤሮዎችን፣ካፊቴሪያና ዘመናዊ የመኪና መቆሚያ ሥፍራዎችን አሟልቶ የያዘና በሦስት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታላይ ያረፈ ደረጃውን የጠበቀ ግንባታ ነው።
ሪፖርቱን ያዳመጠው የመንበረ ፖትርያርክ አስተዳደር ጉባኤም በግንባታዎቹ ማጠቃለያ ሥራዎች ላይ ቤተክርስቲያንን የሚወክሉ፣መንበረ ፓትርያርኩን የሚገልጹ ምስሎችና ሥዕሎች እንዲካተቱበት ጠቁሟል።
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጠቅላይ ቤተክህነቱን ለመምራት ሥልጣኑን ከብፁዕ አቡነ ያሬድ በተረከቡበት ወቅት የግንባታ ሥራው ፴፩ ፐርሰንት አፈጻጸም ላይ የነበረ ሲሆን በዚህ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በብፁዕነታቸው በተደረገው የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ የግንባታ ሥራው ፷፯ ፐርሰንት መድረስ ችሏል። ይህ ማለትም በዚህ ዓመት ብቻ ፶፯ ፐርሰትት አፈጻጸም የተመዘገበ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን ውጤቱ ሊመዘገብ የቻለውም የብፁዕነታቸው የክትትልና የድጋፍ ሥራ በተገቢው መልኩ በመከናወኑ እንደሆነ ጉባኤው ተገንዝቧል።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ይህን ታሪካዊ የግንባታ ሥራን ለማስጀመር በርካታ ዓመታትን ማስቆጠሩን ገልጸው ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስና ብፁዕ አቡነ ያሬድ ጨከን ብለው ግንባታውን በማስጀመራቸው ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል ብለዋል።
ይህ ዘመናዊና ዓለም ዓቀፍ አዳራሽ ቤተክርስቲያናችን ዓለም ዓቀፍ ጉባኤዎችን ለማከናወን፣ሀገር አቀፍ ታላላቅ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብሮችን ለማካሔድ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር የገለፁት ብፁዕነታቸው የግንባታው የማጠቃለያ ሥራ መንበረ ፓትርያርኩንና ጥንታዊት ቤተክርስቲያናችንን የሚገልጹ ምልክቶች እንዲኖርበት ይደረጋል ካሉ በኋላ የግንባታው ማጠቃለያው ሥራ በተቻለ ፍጥነት በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ ይኖርበታል ብለዋል።
የግንባታ ሥራው የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን ዓለም አቀፍ ተጽዕኖና በየወቅቱ የሚቀያየረውን የግንባታ ቁሳቁስ ዋጋ ማሻቀብን ተቋቁሞ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ የሚደነቅ መሆኑንም ብፁዕነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።