ታኅሣሥ ፯ቀን ፳፻ ፲ወ፰ዓ.ም
==================
ኦሮሚያ-ወንጪ
****
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኘው የወንጪ ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ሕንጻ ቤተክርስቲያን የግንባታ ሥራ ክንውን የደረሰበትን ደረጃ ለመመልከት በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሚመራ የልዑካን ቡድን በዛሬው ዕለት በወንጪ ይፋዊ ጉብኝት አድርጓል።

በጉብኝት መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የደቡብ ኦሞ፣ አሪ ዞኖች ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፣
ብፁዕ አቡነ ሕርያቅስ የአዲስአበባና የሀድያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የከምባታ ሀላባና ጠምባሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙኀዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና የክፍላተ ከተሞች ሥራ አስኪያጆች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ተገኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንደገለጹት ገዳሙ ጥንታዊና ታሪካዊ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከያወኑ መሆኑን ገልጸው ከሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ግንባታ በተጨማሪ የአብነት ትምህርት ቤት፣ሰንበት ትምህርት ቤት፣ሰንበቴ ቤት፣ሙዚየምና ወደ ገዳሙ የሚያስገባ ወደብ የሚገነባ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።አያይዘውም ቦታው የቱሪስት ፍሰት የሚበዛበት መሆኑን ታሳቢ በማድረግም ተያያዥነት ያላቸው ሥራዎች እንደሚከናወኑ የጠቀሱት ሙሐዘ ጥበባት አጠቃላይ የግግባታ ሥራው በዘጠኝ ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል።

የገዳሙ አጠቃላይ የግንባታ ሥራን በተመለከተም በባለሙያዎች ገለጻ ተደርጓል።የቤተክርስቲያኑ ግንባታ ሥራ ኃይማኖትን፣ታሪክንና ባህልን መሰረት ያደረገ እንደሆነም በዚሁ ጊዜ ተገልጿል።ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተውጣጥተው የተገኙት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችም ለዚህ የተቀደሰ ፕሮጀክት መጠናቀቅ ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተባበር አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በዚሁ ጊዜ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላሐፉት መልዕክት የወንጪ ቂርቆስ ቤተክርስቲያንን ለማሰራት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት መሆናቸውን ገልጸው ሀይማኖት፣ታሪክና ባህልን አስተሳስሮ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በተግባር የሚሰብከውን ፕሮጀክት በማስተባበርና በመምራት ላደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።አያይዘውም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወንጪን በመሳሰሉ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ውስጥ ጥንታዊያን ገዳማትና አድባራት ታድሰውና ታንጸው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በማድረግ በታሪክ ውስጥ የሚዘከር ሥራ እየሰሩ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር በጸሎቷ ታስባቸዋለች፣ ምስጋናዋንም ታቀርባለች ብለዋል።