የካቲት 1 ቀን 2017.ዓ.ም.
+ + +
ለበርካታ ዓመታት ከክርስቲያናዊ ተራድኦና ልማት ኮምሽን ጋር በመተባበር የአስቸኳይ የምግብና ምግብ ያልሆኑ ርዳታ በማቅረብ፣ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ላይ ዘርፈ ብዙ ቁሳቁሶችን በማገዝ ፣ ለአርሶ አደሮች የምርጥ ዘር በማቅረብ፣ በፕሮጀክት የታቀፉ የአርሶ አደሩን ምርታማነት የሚጨምሩ ሥራዎችን በማገዝ፣አቅመ ደካማ እናቶችን በከብት ርባታ ራሳቸውን እንዲደግፉ በመርዳት፣ በጤና ፣ በሕፃናት ምገባ እና በአቢያተክርስቲያናት አጸድ ልማት ዙሪያ በመሥራት እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ክንውኖችን ሲያከናውን የነበረው የሲውዲን ቤተክርስቲያን የልማት ክንፍ ኀላፊዎች ከጥር 29 ቀን 2017ዓ.ም እስከ የካቲት 1 ቀን 2017ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቆይታ ለማድረግ የመጡ ሲሆን በቆይታቸው ማገባደጃ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ለማግኘት በልማት ኮምሽን የበላይ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል አማካኝነት ፕሮግራም እንዲያዝላቸው ተደርጎ ከቅዱስነታቸው ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮምሽን፣ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ድርጅት ሊቀ ጳጳስ
ኤሪክ ሌይሰን የአክትስ ቸርች ኦፍ ሲውዲን የግሎባል ዳይሬክተር
ካሪክ ሁግሰን የአክትስ ቸርች ኦፍ ሲውዲን የፖሊሲ አማካሪ
አቶ ብርሃኑ ይስማው የአክትስ ቸርች ኦፍ ሲውዲን በኢትዮጵያ ተወካይ
ኢንጂነር ይልቃል ሸፈራው የልማት ኮምሽን ኮምሽነር
መልአከ ሕይወት አባ ሐይለ ገብርኤል ነጋሽ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ እና ሌሎችም በኮምሽኑና በብፁዕ ወቅድስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት የሚገኙ ሠራተኞች ተገኝተዋል።
በውይይቱ ድርጅቱ ለዓመታት በሰበአዊ ርዳታ፣ በቤተክርስቲያን አጸድ ጥበቃ፣ በልማት እና በኢኮኖሚ፣ በጤና እና በሕፃናት ምገባ ላይ ያደርገው የነበረውን እግዛ እውቀና የሰጠና ከዚህ በኋላም በልዩ ልዩ ሥፍራ አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎችን ለማገዝ የሚያስቸል ነው ።
መርሐ ግብሩን የመሩት የኮምሽኑ ኮምሽነር ኢንጂነር ይልቃል ሽፈራው ሁሌ እንደምናደርገው በደብዳቤና በሪፖርት ከመገናኘት ባሻገር እንዲህ ገጽ በገጽ ተገናኝተን መነጋገሩ ለሥራችን ሠፊ መንገድ ይከፍታል ብለን እነዚህ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችን ይዘን መጥተናል። ከድርጅቱ ጋር የነበረን የሥራ ግንኙነት ከቅዱስነትዎ የተሰወረ ስላልሆነ እነዚህን የሥራ ኃላፊዎች እንዲባርኩልን በማለት ቅዱስነታቸውን ጋብዘዋል።
ቅዱስነታቸውም ንግግራቸውን ሲጀምሩ የሚፈናቀል፣ የሚሰደድ፣ የሚራብና የሚጠማ እንዲሁም በመድኃኒት እጦት የሚሰቃይ ሰው ባለበት ዘመን እጁን ለእርዳታ የሚዘረጋ ሰው መኖሩ የእግዚአብሔር ቸርነቱ እንዳልተለየን ትልቅ ማሳያ ነው። በርግጥም እናንተ የቸርነት ሰዎች ወደ ሀገራችን በመምጣት በልዩ ልዩ ዘርፍ ስለምትረዱን እናመሰግናለን። ያኔ በሰላም በምንንኖርበት ዘመን ከጎናችን እንደነበራችሁ ሁሉ አሁንም ግማሹ በጦርነት፣ ሌላው በኑሮ ውድነት እየተሰደደ ባለበት ዘመን ከጎናችን በመሆናችሁ የዘመናት ታማኝ አጋዦቻችን መሆናችሁን ተገንዝበናል። በመሆኑም ስለምታደርጉልን ማንኛውም ትብር ሁሉ በጣም እናመሰግናለን። የሰው ልጅ ሰውነቱ የሚለካው ለወንድሙ በሚያደርገው እገዛ ነው። ዓለማችን ካልተረዳዳች ልትቀጥል አትችልም። ይህ ገብቷችሁ መረዳዳትን ሥራችሁ አድርጋችሁ ከእኛም ጋር ስለምትሠሩ በጣም እናመሰግናለን ብለዋል።
የቅዱስነታቸውን የምስጋና ቃል የሰሙት ሚስተር ኤሪክ ስለተደረገልን አቀባበል እናመሰግናለን ከዚህ በፊት እናደርገው እንደነበረው እርሱን እንቀጥላለን። ይህ ዘመን ክርስቲያኖች አንድነት ፈጥረው እንዲንቀሳቀሱ ያስገደደ ዘመን ነውና እኛም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጋር ተባብረንና አንድነት ፈጥረን እየሠራን በመሆኑ ደስታችን ወደር የለውም ብለዋል።
በመጨረሻም ይህንን ሥራ በሲውዲን እያንቀሳቀሱ ላሉ ኀላፊዎች በክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮምሽን የተዘጋጀ ስጦታ በቅዱስነታቸው ተበርክቶ የውይይቱ ፍጻሜ ሆኗል።