ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን በተመለከተ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚዘዋወረው ዘገባ ከእውነት የራቀ ነው።
ሰሞኑን በአንዳንድ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን በማስመልከት የሚሰራጩት ዜናዎች ፍጹም ከእውነት የራቁና ሕዝበ ክርስቲያኑን ለማደናገር የሚነዙ ሐሰተኛ ዘገባዎች ናቸው።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በመንፈስቅዱስ ፈቃድና በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተጣለባቸውን ከባድ ኃላፊነት በብቃት፣በትጋትና በውጤታማነት እየተወጡ የሚገኙ ሲሆን ወደፊትም የጀመሯቸውን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና አስተዳደራዊ ተግባራትን የበለጠ በማጠናከር ቅድስት ቤተክርስቲያን የገጠሟትን ፈተናዎች ሁሉ በጽናት በመቋቋም በመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው ጸሎትና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ኃላፊነታቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን በማክበር እንገልጻለን።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ቅድስት ቤተክርስቲያን የጣለችባቸውን ከባድ ኃላፊነት በመተው ከጠቅላይ ሥራ አስኪያጅነታቸው ሊለቁ እንደሆነ በአንዳንድ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እየተገለጸ ያለው ዘገባም ፍጹም ሐሰት መሆኑን በድጋሚ እየገለጽን ምዕመናን በአንዳንድ ማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የሚነዛው መረጃ የሐሰት መሆኑን በመረዳት ለብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የሥራ ስኬት በጸሎትና በተለያዩ መንገዶች ስታደርጉ የቆያችሁትን ድጋፍ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት
ግንቦት ፳፩ ቀን ፳፻ ፲ወ ፭ ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ