“ትምህርተ ጥምቀት፣በክልኤ ኪዳናት”

ኪዳን፦ የቃሉ ትርጕም የፍቅር የስምምነት፣ የአንድነት መሐላ፣ ከጥፋት የሚጠብቅ ከለላ& ሰውና እግዚአብሔርን የሚያገናኝ የተጻፈ ውል፣ሰላማዊ ሕግና ትምህርት ማለት ነው ፡፡(ኪ.ወ.ክ)

ክልኤ ኪዳናት፦በሚል የተጠቀሱት ሁለቱ ቃላት ደግሞ የሰው ልጅ ክፉውንና በጎውን ለይቶ በማወቅ፣ ከክፉው በመራቅ እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲኖር፣ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ኑሮው እንዳይናጋ የሚያስተምሩት ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን ናቸው፡፡

እነዚህም ኪዳናት ከአንዱ እግዚአብሔር በተለያዩ ዘመናት ለተለያየ ሕዝብ የተሠጡ፣ሁለንተናዊ ሐሳቡን የያዙና ወሰን የሌለው ፍቅሩን የሚገልጡ ራሳቸውን ችለው በተስፋ የቆሙ፣በመሐላ የጸኑ መሆናቸው ግልጽ ነው ፡፡

ሁለቱም በጥላና በአካል ፣በጊዜያዊና በዘላለማዊ፣በሥጋዊና በመንፈሳዊ ላይ የተመሠረተ ልዩነት ያላቸው ቢሆንም በየዘመናቸው የእግዚአብሔር ያልሆነውን ሕዝብ የእርሱ እንዲሆን ያደረጉና  የሚያደርጉ ኪዳናት ናቸው፡፡

የእርሱ ያልሆነው ሕዝብ በኪዳኑ አማካኝነት ሕዝቡ እንደሚሆን “ወእትካየድ ኪዳነ ምስለ ኩሉ ወእብሎ ሕዝብየ ለዘኢኮነ ሕዝብየ ወውእቱ ይብለኒ እግዚእየ ወአምላኪየ — ከሁሉም ጋር ቃል ኪዳንን  አደርጋለሁ ለሰባ ዘመናትና ከዚያም በፊት  ወገኔ ያልሆነውን ወገኔ እለዋለሁ እርሱም ጌታየና አምላኬ አንተነህ ይለኛል”  ተብሎ በነቢዩ ሆሴዕ .ተነግሯል ፡፡(ሆሴ -2$24)

በመሆኑም በምሳሌና በፍጻሜ ያላቸውን የትርጕም ይዘት ከልዩነታቸው ጋር የባዕድ (የግል) ምልከታ በሌለበት ከቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ሳንወጣ በንጽጽር ጠቅለል አድርገን እንመለከታለን ፡፡

ከርእሰ ትምህርቱ ጋር የሚገናኘውን ሐሳብ ብቻ በመለየት የምናብራራው ትምህርተ ጥምቀት በቤተ ክርስቲያናችን መተርጕማን እይታ ስምንት ወገን (ዐይነት) ሲሆን አራቱ ምሳሌያት፣አራቱ ደግሞ አማናውያት መሆናቸውን . ሐተታ ትርጓሜው ያመለክታል፡፡ (ትር.ወን.ማቴ 3፥3-7)

የምሳሌውም ሆነ የአማናዊው ጥምቀት መሰረተ ሐሳብ መንፃት ፣መለወጥ፣መተባበርና ወደ አዲስ ሕይወት መግባት የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡(ማር.1÷4-8፤ዮሐ.3÷25፤ሐ.ሥ.22÷16፤1.ቆሮ.1÷13)
አራቱ ምሳሌያትና አራቱ  አማናውያት ጥምቀታትም በየአርዕስታቸው ሲታዩ፦

  • የኖኅ መርከብ፣ (ዘፍ. 7፥17፤1ጴጥ3፥20-21)
  • . ባሕረ ኤርትራናደመናው ፣.(1ቆሮ 10፥1-2).
  • ግዝረት ፣ (ዘፍ17፥ 10)
  • ጥምቀተ ዮሐንስ፣(ማቴ 3፥4)
  • የጌታ ጥምቀት፣(ማቴ3፥16)
  • አንብዐ ንስሐ .፣
  • ደመ ሰማዕታትና ባሕረእሳት የሚሉት ናቸው፡፡

ከዚህ በላይ በስምንት አርዕስት የተገለጹት፣ከትርጓሜ ሐተታው የተገኙት የምሳሌያቱና የአማናዊው አስተምህሮ የክብር ስፍራውን እንደያዘ ሆኖ ለምሳሌያዊውና ለአማናዊው ጥምቀት ትንተና የበለጠ በሚቀርበው“ጥምቀት ሦስት ወገን ነው” በሚለው፣በሌላኛው የትምህርት አቀራረብ ማለትም ፦

  • ጥምቀተአይሁድ፣
  • ጥምቀተዮሐንስ፣
  • ጥምቀተ ክርስቶስበሚሉት ንዑሳን አናቅጽ ምሳሌያቱን በጥላነታቸው፣ አማናዊውን በአካልነቱ  እናያለን፡፡

ጥምቀተ አይሁድ፣ትምህርቱና የአፈጻጸም ሥርዓቱ፦

“ኀጥአ ኢታሕዩ…ኀጢአተኛውን ይቅር አትበል…ሕጉ የተሰጠበትን ተራራ ጫፍ እንዳትነኩ ተጠንቀቁ ተራራውን የነካ ፈጽሞ ይሞታል፡፡እንስሳ ወይም ሰው አይድንም„እያለ በሚያስጨንቅና በደልን በሚያበዛ ሁኔታ በተሠራው በመጀመሪያው ኪዳን (ሕግ).በሥጋ ሥርዓት ይፈጸም የነበረው ጥምቀተ አይሁድ ሥርየተ ኀጢአትን  ማሰጠት የማይችል በመሆኑ የሥጋ ርኩሰትን እንጂ የነፍስ እድፈትን አያነጻም ነበር ፡፡ (ዘጸ.19፥10-13፤ዕብ.9፥10)

ኦሪት በድን የዳሰሰ፣ መቃብር ያፈለሰ ሰው እስከ ሠርክ ርኵስ ነው ስለምትል ለአይሁድ የመንጻት ሥርዓት የሚጠቅሙ ወንጌላዊው “ወሀለዋ ህየ መሳብክት እለ ዕብን በዘያጥህሩ ቦቶን …አይሁድ እንደሚያደርጉት የመንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር”በሚል የገለጻቸው ስድስት ጋኖችና ሌሎችም ንዋያተ ንጽሕ  ነበሩአቸው፡፡(ዮሐ.2÷6)

በእያንዳንዱ ድርጊቶቻቸው፣በዕለታዊ ኑሮአቸው. በመታጠብ ለመንጻት ይፈጽሙት የነበረው ሥርዓትም አዲስ ልደት ለምናገኘበት አማናዊ ጥምቀት ቀጥተኛ ምሳሌ መሆኑ የማያጠያይቅ ክሡት  ግብር ነው፡፡

በመሆኑም እግዚአብሔር ለርስቱ የመረጠው ወገን የመሆን ማሳያ እንዲሆን፣ ከሕዝቡ ተለይቶ ላለመጥፋትና በሕይወትም ለመኖር ጭምር የልብ መገረዝ በሌለበት አፍአዊ በሆነ የሥጋ መገረዝ ብቻ የራስንና የመላ ቤተሰብን ሸለፈት ማስወገድ በጊዜው  ሕጉ የሚጠይቀው ግዴታ ነበር፡፡

በእዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር ላቆመው ኪዳን ምልክትነት እንዲፈጸሙ በሕግና በነቢያት ጥቅልሎች (መጻሕፍት) የታዘዙት የመንጻት ድርጊቶች  በከፊል  የሚከተሉት ናቸው፡፡

እነርሱም፦

  • ሕዝበ እስራኤል በአንዱ እግዚአብሔር ለማመናቸውና ለመታዘዛቸው ምልክት እንዲሆን ሸለፈትን መገዘር፣(ኢያ.5÷2)
  • ለቤተ መቅደስ የሰን መታጠቢያዎችን  ማሠራት፣ (1 ነገ.7፥27-45)
  • የሕዝቡን ኃጢአት ተሸክሞ ወደ በረሃ የሚለቀቅውን  እንስሳ ለግል ጥቅሙ ያዋለ (የወሰደ) ሰው ሲገኝ ወደሰፈሩ ከመግባቱ በፊት  በውኃ እንዲታጠብ  ማድረግ፣(ዘሌ16፥26)
  • አጥንቱ የተሰበረውን፣የተገደለውንና የሞተውን ሰው መቃብር የነካ በውኃ በተነከረ ነጭ አበቦች ባሉት ጭራ በሚመስል ሁስጱ (መልካም መዐዛ ባለው ተክል) እንዲረጭ ማድረግ ፣(ዘኁ19፥6–12)
  • ወደ ይሁዲ እምነት የሚመጣውን ሰው አስቀድሞ በውኃ ማጥመቅ ፣(ዘሌ 14፥9)
  • ካህናቱ ልብሰ ተክህኖውን ለብሰው የመታረቂያ መሥዋዕት ለማቅረብ ወደመገናኛው ድንኳን ሲገቡ እንዳይሞቱ ከጠራ ናስ በተሠራ ሰን ላይ በተሞላ ውኃ የመታጠብ ሥርዓትን መፈጸም ፣(ዘጸ 30፥18-20)
  • አሮንና ልጆቹ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ ከታጠቡ (ከተጠመቁ ) በኋላ በጎ መዓዛ ባለው የተቀደሰ ቅብዐ ዘይትን መቀባት እንደኦሪቱ ትምህርት፣እንደ መቅደሱ ሥርዓት በመፈጸም መንጻት ይጠበቅባቸው  ነበር፡፡

ከላይ በተገለጸው መንገድ  ፍጹም ለሆነው ትምህርተ ጥምቀት ምሳሌ በመሆን ባገለገለው መለኮታዊ ኃይል በሌለው ውኃ በመጠመቅ ይፈጸም የነበረው የአይሁድ ጥምቀት (የመንጻት ሥርዓት) በየምኩራባቱ ሁሉ ዕለት ዕለት ሲፈጸም ቆይቷል፡፡

 ምንም እንኳን ጥምቀቱ ውሳጣዊ ቅድስናን የማያጎናጽፍ፣ ምሳሌያዊና አፍአዊ መነጻትን  ብቻ የሚያስገኝ ቢሆንም ሃይማኖተ አይሁድና ትምህርቱ የክርስትና አበባ የበቀለበት ግንድ፣የአማናዊ ጥምቀት ምሳሌያዊ ዐውድ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡(ዮሐ.4፥22)

ጥምቀተ አይሁድና ትምህርቱ የክርትና አበባ የበቀለበት ግንድ  በመሆን ልጅነት ለሚያሰጠው ጥምቀት በምሳሌነቱ ቢጠቅምም ዘላቂ የሆነ የሕይወት ዋስትና መስጠት ያልቻለ መንፈቀ ፍጻሜ (የግማሽ ድኅነት ሥርዓት) በመሆኑ ሰውን በምልዐት የማጽደቅ ኃይል  አልነበረውም፡፡

ከአማናዊ ጥምቀቱ፣ ከርቱዕ ሥርዓቱ የማነሱም ምክንያት“ኦሪትሰ ጽላሎት ይእቲ ለእንተ ትመጽእ ሠናይት…ኦሪትና ሥርዓተ ጥምቀቷ ለምትመጣው በጎ ነገር (ልጅነት ለምታሰጠው ጥምቀት) ጥላ ናትና ነው፡፡(ዕብ 10፥1)

በመሆኑም በእግዚአብሔርና በእነርሱ መካከል የሚጠብቁት ቃል ኪዳን ሆኖ እንደተሰጣቸው የሚያምኑት ሁሉ (ሕዝቡ) ሕጉን በትምህርት ሰምተው ጥምቀቱን እንደ ሥርዓቱ ቢፈጸሙትም ሊለውጣቸውና ሊያድናቸው ስለአልቻለ የሕጉን አጥር ጥሰው& እግዚአብሔርን ረስተው እስከ ክርስቶስ መምጣት ሁሉም በደለኛ ሆኖ በሞት ግዛት ውስጥ ቆይቷል፡፡(ዘፍ.17÷10-11)

ከላይ እንደተገለጸው በምሳሌነት ይፈጸም የነበረው. የአይሁድ ጥምቀትና የዮሐንስ ጥምቀት ጥምቀተ ክርስትና የሚያስገኘውን ድኅነት አስቀድሞ የሚያመለክት ጽላሎት ነበር፡፡(1ቆሮ 10፥1-4)

ጥምቀተ ዮሐንስ

ጥምቀተ ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ„የሚለውን አዋጅ በማወጅ፣ የጌታን መንገድ በመጥረግ ሕዝቡን ለአማናዊ ጥምቀት ለማዘጋጀት የሚፈጸም፣ ወደፊት የሚመጣውን የሚያመለክት የንስሐ ጥምቀት ነበር፡፡ (ማቴ 3፥3-7)

“መንገዴን ያዘጋጅ ዘንድ መልእክተኛዬን አስቀድሜ እልካለሁ„ ተብሎ በነቢዩ ሚልክያስ አስቀድሞ እንደተነገረው የዮሐንስ ጥምቀት በትክክል ሕዝቡን ለጌታ ለማዘጋጀት በቤተ ራባ በማዕዶተ ዮርዳኖስ ይፈጸም የነበረ ጥምቀት እንደሆነ ሰማዕተ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ “የእኔ ደስታ ዛሬ ተፈጸመ እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ይገባል፡፡ ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው„በማለት የመሲሑን መምጣት ይናፍቁ የነበሩ ደቀመዛሙርቱንና አስቀድሞ በአፈ ነቢያት ተነግሮለት የተቀበለውን የምስክርነት መክሊት ከነትርፉ በማስረከቡ ታውቋል ፡፡(ሚል 3፥1@ ዮሐ1፥23፤ 3፥29–31)

ስለራሱ ማንነትም “አንተ ማነህ?„ብለው የአይሁድ ካህናትና ሌዋውያኑ ሲጠይቁት “እኔ ጥርጊያውን አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ ነኝ„ በማለት አርከ መርዓዊ (የሙሽራው ሚዜ) በሙሽራው ድምጽ ደስ የሚሰኝ &የደስታው ተካፋይ  እንደሆነ በግልጽ መስክሮአል፡፡

በመሆኑም የአይሁድ ጥምቀትና የዮሐንስ ጥምቀት ዓላማቸው በምሳሌነታቸው መሸጋገሪያ ድልድልይ ሆነው ወደ ፍጽምት ጥምቀት መርቶ ማድረስ ስለነበር ጊዜው ሲደርስ ሥጋን የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ያይ ዘንድ ሥርየተ ኀጢአት  ለምታሠጠው ”አኃቲ ጥምቀት“ሥፍራቸውን ለቀዋል፡፡

ምክንያቱም„ እስመ ግዝረትሰ ወኵሉ ትእዛዘ ኦሪት አምሳላት እሙንቱ …ግዝረትና ሁሉም የኦሪት ትእዛዛት ለፍጽምት ጥምቀት፣ለክርስቶስ ሕማማትና ለሞቱ ምሳሌዎች ናቸውና„ የአይሁድ የሥጋ ግዝረት በስሙ ለተጠመቁት ስለማያስፈልግ ነው ስፍራቸውን የለቀቁት ፡፡ (ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ )

በአጠቃላይ የአይሁድ ጥምቀት ለሥጋ መንጻት፣የዮሐንስ ጥምቀት ለንስሐ  ሲሆን የክርስቶስ ጥምቀት ደግሞ ለድኅነት መሆኑን መጻሕፍት አምላካውያት በስፋት ያስገነዝባሉ፡፡(ዮሐ1፥29)

ጥምቀተ ክርስቶስና በእርሱ የተገኘው ፍጹም ድኅነት ፦

ከላይ በምሳሌ ሲገለጽ፣በትንቢት ሲነገር የመጣው ጥምቀተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አንድነትና ልዩ ሦስትነት የተገለጠበት ዐቢይ ምስጢር ፣ ከአይሁድ ጥምቀትና ከዮሐንስ ጥምቀት ፈጽሞ የተለየ ሥርየተ ኀጢአትን የሚያሰጥ ማኅተመ ሕይወት ነው፡፡(ማቴ 3፥16-17)

በሕግ መጻሕፍት፣ በትንቢተ ነቢያት እንደሚመጣ አስቀድሞ  የተነገረለት መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በሥጋ ሰብእ ተወልዶ ፣ግእዘ ሕፃናትን  ጠብቆ በየጥቂቱ አድጎ በሠላሳ ዘመኑ ተጠምቆ የኀጢአት ሥርየትን ፣የነፍስ ድኅነትን እንድናገኝ ይህን ድንቅ ምሥጢር ገለጠልን፡፡

በጥምቀቱም “ተመልሶ ይምረናል ኀጢአታችንንም ወደ ባሕሩ ይጥለዋል„ ተብሎ የተነገረው ቃለ ነቢይ ልጅነትን በሚያስገኝ፣ጸጋን በሚያሰጥ ሁኔታ ከብሮና ተቀድሶ አማናዊ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡ (ሚክ 7፥19)

ለፍጥረቱም የነበረው የእግዚአብሔር ፍቅር ተገልጦ፣የሰው ልጅ የመዳን ጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ አግኝቶ፣ በትእዛዛት ተጽፎ የነበረው የዕዳ ጽሕፈቱ ተደምስሶ አዲስ የሕይወት መንገድ እንደተከፈተለት በጥምቀቱ የተገኘው ክብረ ሥጋና ክብረ ነፍስ ይመሰክራል፡፡(ዮሐ.3፥3-6)

በግብረ ኀጢአት ጎስቁሎ የነበረው ባሕርያችንም መታደስን አግኝቶ ውበቱ የተገለጠው፣ ለመንፈሳዊ ሀብታት በር በሆነው  እርሱ በሠራልን በዚህ አማናዊ ጥምቀት ነው፡፡

በመሆኑም በማዳኑ ክሂሎት፣ በይቅርታው ብዛት የተሰጠን፣ወደ አዲሱ ሕይወት የገባንበት ጥምቀት ሥጋዊ ሳይሆን መንፈሳዊ፣ አፍአዊ ሳይሆን ውሳጣዊ መሆኑን ታላቁ የነገረ መለኮት ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲናገር “ ተሐጽቦሰ ዘዝየ አኮ ዘሥጋ ዳዕሙ ዘነፍስ…የአሁኑስ መታጠብ የሥጋ ያይደለ የነፍስ መንጻት ነው” ብሏል፡፡

በሌላ በኩል ሞቱን በሚመስለው ጥምቀቱ አሮጌው አዳማዊ ሰውነቱ ከነሥራው ተወግዶ ከውኃና ከመንፈስ የተወለደው ሁሉ “አዲሱ ሰው„ የተባለ ክርስቶስን እንደለበሰ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ማኅበረ ምእመናን በጻፈው መልእክቱ “ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው ፡፡ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል„ በማለት ወደር በማይገኝለት ምህሮ “የምሥራቹን„ ፍጹም በሆነ የልብ ደስታ ገልጦታል፡፡(2ቆሮ 5፥17)

በአስተርእዮተ እግዚአብሔር የተገኘውን  ሰላምና ይህን የምሥራች . የሚያበሥር መልእክተኛ ሲመጣ ማየት፣ድምፁንም መስማት ደግሞ እንዴት ደስ እንደሚያሰኝ ከመልእክቱ ይዘት መረዳት ይቻላል፡፡

አሮጌው ነገር አልፎ “አዲስ ፍጥረት„ የመሆንን የምሥራች የሰሙት  ሁሉ የልብን ክፉ ሐሳብ በማስወገድ፣በማያቆስለው ሥርዓት በመጠመቅ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ በአማናዊ ጥምቀት በመሳተፍ ሀብተ ውልድና፣ሕይወተ ልቡና አግኝተው ከሥጋዊ ግብር የተለዩ መሆናቸውን እናስተውላለን  ፡፡

ከሥጋዊ ግብር ተለይተው የሚኖሩት ውሉደ ጥምቀትም በምን ዐይነት ሁኔታ እንደተወለዱና ባሕርያቸውም ምን እንደሚመስል  ታላቁ መጽሐፍ ሲነግረን “እለ ኢኮኑ እምነ ዘሥጋ ወደም ወኢ እምሥምረተ በእሲ ወብእሲት አላ እምእግዚአብሔር ተወልዱ…እነርሱ ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር አልተገኙም ሴትና ወንድ ተስማምተው ከሚሠሩትም ሥራ አልተወለዱም” ይለናል፡፡(ዮሐ1÷13)

በመሆኑም ከማይጠፋው ዘር የተወለዱት ውሉደ ጥምቀት የተወለዱበትን ምሥጢር በሥጋዊ አስተሳሰብ ልንደርስበት (ልንረዳው)የማንችለው በመንፈሰ ኅሊና ብቻ የሚታይ ረቂቅ ኃይልና የጽድቃችን ማኅተም ነው፡፡(1ጴጥ 1፥23)

ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ይህን ረቂቅ ልደት ከድንግል ማርያም የሥግው ቃል መወለድ ምሥጢር ጋር እያነጻጸረ ሲያስተምር፦ “ወተወልዶሰ እምጥምቀት ይመስል ልደተ እምድንግል በከመ ክርስቶስ ተወልደ እማርያም ወእምድኅረ ተወልደ እምኔሃ ተረክበ አንቀጸ ሥጋሃ እጽወ በማኅተመ ድንግልናሃ ወከማሁ ዘሂ ተወልደ እምከርሠ ጥምቀት ወጺኦ እማይ ኢተረክበ አሠረ  በዓቱ ወጸአቱ ውስተ ከርሠ ምጥማቃት…በጥምቀት መወለድስ ከድንግል መወለድን ይመስላል፡፡ክርስቶስ ከድንግል ማርያም እንደተወለደ ከእርሷም ከተወለደ በኋላ አንቀጸ ሥጋዋ በድንግልናዋ ማኅተም ታትሞ እንደተገኘ ምሥጢሩም ረቂቅ እንደሆነ እንደዚሁ ከጥምቀት ማሕፀን የተወለደ ሰው ከውኃ ወጥቶ ወደ መጠመቂያው ውስጥ የመግባቱና የመውጣቱ ምልክት አይገኝም፣ በሥጋዊ ግብርም አይያዝም„ በሚል የገለጠበት ምሳሌያዊ የትምህርት አቀራረብ እጅግ የረቀቀና የሚደንቅ ነው፡(መጽ.ምሥጢር )

ዳግመኛም ይኸው ሊቅ ጥምቀተ ክርስቶስ ዕርቃናችንን የከደነ፣ ልጅነትን የተጎናጸፍንበት ድንቅ ምሥጢር መሆኑን ሲነግረን፦ወህየንተ ቆጽለ በለስ ዘሰፈየ አዳም ወገብረ ሎቱ መዋርዕተ ወከደነ ዕርቃኖ ወከማሁ አነሂ ተከደንኩ በመርዓ ጥምቀቱ ዘውኅዘ እምገቦ ወልድኪ …አዳም ሰፍቶ፣ መከለያ አድርጎ ዕርቃኑን በሰወረበት የበለስ ቅጠል ፈንታ እንዲሁ እኔም ከልጅሽ ጎን ከፈሰሰው የጥምቀት ውኃ ተከደንሁ ልጅነትንም አገኘሁ” እያለ ስብሐተ ጥምቀቱን በመቅረዘ ትርጓሜው ከፍ አድርጎ አመስጥሮታል፡፡(አርጋኖን ዘሰኑይ)

በመሆኑም ከሥጋ ወላጆቻችን አንድ ጊዜ እንድምንወለድ ሁሉ ዳግመኛ ጥልቅ በሆነ ምሥጢር የምንወለድበት ጥምቀተ ክርስትናም ንጽሐ ነፍስን ፈጽሞ የሚያሰጥ በመሆኑ  አንድ ጊዜ ብቻ የሚፈጸም የማይደገም ምሥጢር ነው፡፡

ጥምቀተ ክርስትና የማይደገም ምስጢር ስለመሆኑ የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት፦

ጥምቀተ ክርስትና አንድ ጊዜ ፈጽሞ ጥሙቃንን በቀጥታ ውሉደ እግዚአብሔር እንዲሆኑ የሚያደርግ  የሕይወት ማሕፀን በመሆኑ ክሂለ አንጽሖ እንዳልነበረው የአይሁድ ጥምቀት በየጊዜው የሚፈጸም ሥርዓት አይደለም፡፡

በአንድ ጊዜ መጠመቅ ፍጹም የሆነ ድኅነትን እንደሚሰጥ ያልተረዱ፣እውቀት ከማጣታቸው የተነሳ የተጎዱ አንዳንድ ስሑታን ግን እንደ አይሁድ ሥርዓት ዳግመኛ ይጠመቃሉ፣ ያጠምቃሉ፡፡(ሆሴ 4$6)

መያጢተ ጸጋ ወጽድቅ ከሆነችው ከፍጽምት ጥምቀት ባሕርይ ጋር የማይስማማው ይህም ድርጊት በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ሲታይየቀና ሥርዓት እንዳልሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “አሐዱ እግዚአብሔር፣አሐቲ ሃይማኖት ፣ወአሐቲ ጥምቀት…አንድ ጌታ፣ አንዲት ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት „በማለት አስተምሮናል፡፡(ኤፌ 4፥5)

በተመሳሳይ የምሥጢር አንድነት ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም“ ሁለተኛ መጠመቅስ ልዩ ልዩ የሚሆን ጥምቀት የአላቸው የአይሁድ ሃይማኖት ጥምቀት ነው፡፡እናንተም ሁለተኛ ልትጠመቁ ትወዳላችሁ?…ወይእቲ ምዕረ አሐቲ…እርሷ ፈጽማ የማትደገም አንዲት ናት” በማለት ገልጦታል ፡፡

ሁለተኛ መጠመቅም  ክርስቶስን መስቀል  እንደሆነ ሲናገር “ዳግመኛ እጠመቃለሁ የሚል ሰው ጌታን ስለ እርሱ ሁለተኛ ይሰቅለው ዘንድ ይወዳል”፡፡ ምክንያቱም “እስመ ማየ ጥምቀት ስቅለት ውእቱ…ጥምቀት በሞቱ የተገኘ የሞቱ ምሳሌ ነውና” ይላል፡፡ (ድር.9)

በጉባኤ ቁስጥንጥንያ የተገኙት ቅዱሳን አባቶቻችንም በአንቀጸ ሃይማኖት ፍጽምት ጥምቀት አንድ ጊዜ በሚፈጸመው ሥርዓቷ ልጅነትን በማሰጠት ለመንግሥተ ሰማያት የምታበቃ ስለሆነች  ከማይደገሙት ምሥጢራት መካከል  መሆኗን “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት …የኀጢአት ሥርየትን በምታሰጥ አንዲት ጥምቀት እናምናለን፡፡„ በሚለው ትምህርትና  ቀኖና አጽንተውታል፡፡(ጸሎተ ሃይማኖት)

በአጠቃላይ ለሕጽበተ ዳግም ልደት  የተሰጠን ጥምቀተ ክርስቶስ የጽድቅ ሁሉ ፍጻሜ  መሆኑን እንድናስተውል “መጽአ ወተጠምቀ እምኃበ ዮሐንስ ከመ ይፈጽም ኵሎ ጽድቀ…ጽድቅን ሁሉ ሊፈጸም  ወደእኛ መጣ በዮሐንስም ዘንድ ተጠመቀ„በማለት ባለመኃልዩ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በማያሻማ ሁኔታ ገልጦታል፡፡(መዝሙር ዘሰንበት)

ከዚህም ጋር የትምህርተ ምስጢራትን ልዩነት በክልኤ ኪዳናት በውል ተረድተን በሚያሰጡት ሀብታት እንድንቀደስ “መፍትው እንከ ነገረ ኅቡአት ከመ ታእምሩ …ሀብተ መንፈስ ቅዱስ የሚያሰጡ ምስጢራትን በውል ልትረዱ ይገባል„ ተብሎ ተጽፎአል ፡፡ (መጽሐፈ ኪዳን)

በመሆኑም ነገረ ኅቡአትን የተረዳችው፣ የገሃነም ደጆች ላያነዋውጧት በዐለት ላይ የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምታምነው እምነትና የምስታስተምረው ትምህርት  በብዙ ኅብረ ምሳሌያት አስቀድሞ የታየና የተነገረ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር የተመሳከረ  ፍኖተ ጽድቅ ነው፡፡(መድሎተ ጽድቅ)

ስለሆነም በሐሊበ ንጽሕ የሚያድጉት ልጆቿ በጥምቀት የሚገኘውን የጽድቅ ጥሩር ለብሰው በመንፈስና በእውነት እያመለኩ፣ የዲያብሎስን ሽንገላ እየተቃወሙ፣ እንዲኖሩ የመዳን በር የሆነውን ምሥጢረ ጥምቀት ሐዋርያዊ በሆነው ትውፊቷ እየፈጸመች፣ ተዝካረ ጥምቀቱን በየዓመቱ ለበረከት እያከበረች በደሙ ለዋጃት ሙሽራዋ ሁለንተናዋን በማስገዛት ትኖራለች፡፡( ዮሐ 4፥23 ፤ኤፌ 5፥24፤ 6፥11-14)

በመጨረሻም በሕጽበተ ዳግም ልደት የተወለድነው  እኛ ኦርቶዶሳውያን ለጠላት አሠራር የተጋልጥን እንዳንሆን እግዚአብሔር ከእኛ በሚፈልገው ልክ በአንድ ልብ ሆነን& አንድነታችንን አጽንተን በሰማይ ላለችው ማኅበር አረቦን (ምልክት) የሆነች ቤተ ክርስቲያንችንን በትረ ክህደታቸውን ቆርጠው ከተነሱ& ለመንጋው ከማይራሩ ጨካኞች በትጋት እንድንጠብቅ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ እርሱ ይርዳን  ፡፡(የሐ.ሥ 20፥ 28 ፤ 2ቆሮ 13፥11)

 

መንክር ስብሐተ ጥምቀቱ

መጋቤ ብርሃናት አባ ተክለያሬድ ጎርጎርዮስ

የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ

 ዋና ኃላፊ