ሚያዚያ ፭ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
=============
የኢ.ኦ.ተ.ቤ. ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ “ኦሮቶዶክሳዊያን ብዙኀን መገናኛ ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን” በሚል ርዕስ በዛሬው ዕለት የሥልጠና፣ የምክክርና የውይይት መድረክ በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል አካሂዷል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ ሦስት መሠረታዊ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በቡድን ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን እነርሱም፦
1ኛ <<ኦርቶዶክሳውያን ማኅበራዊ ሚዲያን
ለሐዋርያዊ አገልግሎት እንዴት እንጠቀም››
በሚል ርእስ በመምህር ዶ/ር አካለወልድ ተሰማ፤
2ኛ ‹‹የሚዲያ ተቋማት ከሕግና ከሥነ–ምግባር
አንጻር በኦርቶዶክሳዊ መነጽር›› በሚል ርእስ በአቶ አያሌው ቢታኒና በዲ/ን ዘካርያስ ወዳጅ፤
3ኛ “የኦርቶዶክሳዊያን እቅበተ እምነት በዘመነ ማኅበራዊ ሚዲያ “በሚል ርእስ በዲ/ን ታደሰ ወርቁ፤ቀርበዋል። የቀረቡትን ጥናታዊ ጽሑፎች መሰረት በማድረግም በየቡድኑ የተነሡት ሀሳቦች በነገው ዕለት በቡድን አወያዮቹ አማካኝነት ቀርበው በሥልጠናው ላይ ጽሑፍ ባቀረቡ ሊቃውንትና ምሁራን መልስና ማብራሪያ የሚሰጥባቸው ከመሆኑም በላይ በብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና በሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ማብራሪያ የሚሰጥባቸው ይሆናል።

በነገው ዕለት “የኦርቶዶክሳውያን የማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛ ሙያተኞች የአሠራር ሥነምግባር ምን መምሰል አለበት›› በሚል ርእስ በአቶ ነጻነት ተስፋዬ ጥናታዊ ጽሑፍ ይቀርብና ይህን መሠረት በማድረግ በየ ቡድኑ ውይይት ተደርጎበት የሚቀረበውን ሀሳብ መሠረት በማድረግም የአቋም መግለጫ የሚዘጋጅ ሲሆን የአቋም መግለጫው ሰኞ ጠዋት በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በተገኙበት ይነበብና በሥልጠናው ላይ ለተሳተፉ የምስክር ወረቀት ከተሰጠ በኋላ የማስታወሻ ፎቶግራፍ በመነሣት የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ይሆናል።

የኢ.ኦ.ተ.ቤ. ሕዝብ ግንኙነት መምሪያም በሥልጠናው ላይ ከተሳተፉ ኦርቶዶክሳውያን የብዙኀን መገናኛ ባለሙያዎች ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችለውን የግንኙነት መስመር በመዘርጋት ወጥ፣ ተዓማኒና ተቋማዊ መረጃዎችን በማቀበል ለአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እድገት የሚሠራ ይሆናል። በዚህም የመረጃ መዛባት፣ ከተልዕኮና ከመንፈሳዊ እሳቤ ውጪ የሚሰራጩ መልዕክቶችን መበራከት በማስቀረት ተቋማዊ አሠራርን የሚዘረጋ ይሆናል።

በቀጣይ አንድ ወር ውስጥም በየ አህጉረ ስብከቱ የሚገኙ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊዎችን ወደ ማዕከል በማስመጣት ተመሳሳይ ስልጠና እንዲሰጣቸው ከተደረገ በኋላ የግንኙነት መስመራችንን በማጠናከር ተቋማዊ የመረጃ ልውውጥን በመፍጠር ወጥና አስተማማኝ ሥርዓትን በመዘርጋት የሕዝብ ግንኙነት ሥራችን ተጨባጭ ውጤት የሚያስመዘግብ እንዲሆን ይደረጋል።

የዛሬው ዕለት የተደረገውንና በነገው ዕለት የሚካሔደውን ሥልጠና፣ ምክክርና ውይይት መነሻ ተደርጎ የሚዘጋጀው የአቋም መግለጫም በመምሪያችን በሚገባ ተደራጅቶ በየመምሪያዎቹ ምላሽ እንዲያገኝ በማድረግ ክፍቶችን የመሙላትና በኦርቶዶክሳውያን የብዙኀን መገናኛ ተቋማትና በመምሪያችን መካከል ተቋማዊ መተማመንን በመፍጠር የወደፊት ሥራዎቻችን የተቃና እንዲሆኑ በማድረግ ለአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ተልዕኮ መፋጠን የምንተጋበትን መደላድል እንፈጥራለን።

የኢ.ኦ.ተ.ቤ. ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
ፎቶ EOTC TV