ከራድዮን ዖፍ ጸዐዳ
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ከሰማየ ሰማያት የወረደውን ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በድንግልና የተወለደውን እግዚአብሔር ወልድን “ለዘተወልደ እምቅድስት ድንግል ምንተ ንብሎ ናስተማስሎ አርዌ ገዳምኑ አንባሳ ወሚመ ከራድዮን ዖፍ ጸዐዳ ንጉሥ አንበሳ እምዘርዐ ዳዊት ዘመጽአ (ከዳዊት ዘር የመጣውን፤ ከድንግል የተወለደውን ምን እንበለው የዱር አንበሳ፤ ወይስ ከራድዮን የተባለ ጸዐዳ ወፍ)” በማለት አመስግኗል፡፡ ከራድዮን ማለትም ስመ ዖፍ (የወፍ ስም) ነጭ፤ መልከ መልካም ወፍ፤ የክርስቶስ አርአያ፤ የሰውነቱ አምሳል ነው፡፡ ይህ የክርስቶስ ምሳሌ የሆነ ወፍ በሀገራችን ባዋሽ ወንዝ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊም ቅድስት ድንግል ማርያምን ሲያመሰግን “ዘይነብር ዲበ ኪሩቤል ወሱራፌል መጽአ ወኀደረ ውስተ ከርሥኪ(በኪሩቤል፤ በሱራፌል አድሮ የሚኖረው እርሱ ሰው ሆኖ በማሕፀንሽ አድሮአልና፡፡ መፍቀሬ ሰብእ አቅረበነ ኀቤሁ፡፡ ዘዚኣነ ሞተ ነሥአ ወእንቲኣሁ ሕይወተ ወሀበነ (ሰውን የሚወድ ሰው የሚወደው እርሱ የእኛን ሞት ነሥቶ የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጥቶ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር አስታረቀን)”፡፡ በማለት በዐርብ ውዳሴ ማርያም ክፍል ሁለት ላይ የገለጸውን የተዋሕዶ ሊቃውንት ሲተረጒሙ፡-
ታሪክ፡- ከራድዮን የሚባል ጸዐዳ ዖፍ አለ፡፡ ከነገሥታቱ ቤት ይኖራል፡፡ ሰው ሲታመም አምጥተው ከፊቱ ያኖሩታል፡፡ የሚሞት እንደሆነ ፊቱን ይመልስበታል፡፡ የሚድን ከሆነ ቀርቦ አፉን ካፉ አድርጎ እስትንፈሱን ይቀበለዋል፡፡ ነጭ የነበረው ይጠቁራል፡፡ ብርድ ብርድ ይለዋል፡፡ ዋዕየ ፀሐይ ሲሻ ወደ አየር ይወጣል፡፡ ሦስት ሰዓት ዋዕየ ፀሐይ ተመቶ ዋዕየ ፀሐይ ሲሰማው ወደ ባሕር ይወርዳል፡፡ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ ባሕር አድሮ የቀደመ ጠጉሩን መልጦ ታድሶ ይወጣል፡፡ ዖፍ ጸዐዳ (ነጭ ወፍ) የተባለው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ቀይሕ በትስብእቱ ጸዓዳ በመለኮቱ እንዲለው፡፡ ድውይ የተባለ አዳም ነው፡፡ ቀርቦ እስትንፋስን እንደመቀበል የአዳምን ባሕርዩን ባሕርይ አድርጓል፡፡ ደዌ በእስትንፋስ ወደ እሱ እንደተመለሰ የአዳምን ባሕርይ ባሕርይ ቢያደርግ በአዳም የተፈረደውን መከራ ተቀብሏል፡፡ በማለት አመሥጥረው ይተርጒማሉ፡፡ ቅዱስ መጽሐፍም “ውእቱ ነሥአ ደዌነ ወጾረ ሕማመነ — በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንም ተሸክሟል” (ኢሳ. 53፥.4) ሲል አረጋግጦልናል፡፡
ቅዱስ ያሬድ “ዖፍ ጸዓዳ፤ ንጉሥ አንበሳ፤ ተጠምቀ በማይ በዮርዳኖስ ቀላይ፤ በእንቲአነ ተጠምቀ ወገብረለነ ሰላመ — ነጭ ወፍ፤ ንጉሥ አንበሳ፤ በዮርዳኖስ ወንዝ በውኃ ተጠመቀ፤ ስለእኛ ተጠመቀ፤ ሰላምን አደረገልን” በማለት በምሳሌ አመስጥሮ ዘምሯል፤ አመስግኗል፡፡
ይህም ምሳሌ ጌታ አዳምን ፈጥሮ በነፍስ ሕያው አድርጎ በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ ካንዲት ዕፀ በለስ በቀር ከሰማይ በታች ከምድር በላይ ያለውን ሁሉ ብላ፥ ጠጣ፥ ግዛ፥ ንዳ ብሎ በገነት አኖረው፡፡ ሰባት ዓመት ከሦስት ወር ከዐሥራ ሰባት ቀን በሕጉ ጸንቶ ኖረ፡፡ ከዚህ በኋላ ምክረ ከይሲን ሰምቶ፤ አምላክነትን ሽቶ፤ ዕፀ በለስን በልቶ፤ ከፈጣሪው ተጣልቶ፤ ከገነት ወጣ፡፡ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ፤ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነምን ፈረደበት፡፡ ዲያብሎስም የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ በአዳምና በሔዋን ሥቃይ አጽንቶ አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ ብለው ስመ ግብርናቸውን ጽፈው እንዲሰጡት በማድረግ በሁለት እብነ ሩካብ የጻፉትን አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል ጣለው፡፡ በዮርዳኖስ የጣለውን ሲጠመቅ እንደ ሰውነቱ ተረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶላቸዋል፡፡ በሲኦል የጣለውን በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ወርዶ ነፍሳትን ሲያወጣ አጥፍቶላቸዋል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ “ወበዝንቱ ተዐውቀ ፍቅሩ ለእግዚአብሔር ላዕሌነ (በዚህም እግዚአብሔር ፍቅር እንደሆነ ለእኛ ታወቀ፤ እግዚአብሔር እኛን መውደዱ ታወቀ፡፡ እስመ ለወልዱ ዋሕድ ፈነዎ ውስተ ዓለም (ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው የባሕርይ ልጁን ወደዚህ ዓለም ሰዶልናልና አለ፡፡ በዘመነ ብሉይ የነበረው ዘመን ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኲነኔ አልፎ እውነት ምሕረት የሰፈነበት የይቅርታ ዘመን እንደመጣ፤ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ጠፍቶ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ፤ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ እንደተሰጠ ተረጋጋጧል፡፡ የምሕረት ቃል ኪዳን ተፈጽሟል፡፡
እግዚአብሔር ወልድ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ሁሉን ያስገኘ፤ ሰውን የፈጠረ፤ በሥራው ሁሉ ያለ፤ በሙሴ አድሮ ሕዝቡን ያስተማረ፤ ሕግን የሠራላቸው፤ ለኢያሱ ርስትን የሰጠው፤ ኖኅን የጠበቀው፤ አብርሃምን የመራው ከይስሐቅ ጋር የታሠረ፤ ከያዕቆብ ጋር እንግዳ የሆነ፤ ከዮሴፍ ጋር የተሸጠ፤ በዳዊት አድሮ የተናገረ፤ በነቢያት አድሮ ሕዝቡን ያስተማረ፤ እምቅድመ ዓለም ከአብ እንበለ እም (ያለ እናት) የተወለደ፤ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ፤ የዘለዓለም ንጉሥ፤ ድኅረ ዓለም ከቅድስት ድንግል ማርያም ነፍስና ሥጋን ነሥቶ ፍጹም አምላክ ወሰብእ የሆነ በሰው ባሕርይ ሰው የሆነ፤ እርሱ ነው፡፡ በመሆኑም የሥጋን አምላክ መሆን፤ የአምላክን ሰው መሆን በዚህ ተረዳን፤ ተገነዘብን፡፡
ጥምቀት ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ነው
ይኸውም “ወአመ በጽሐ ዕድሜሁ ፈነወ እግዚአብሔር ወልዶ ወተወልደ እምብእሲት ወገብረ በሕገ ኦሪት — የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፡፡)” (ገላ. 4፥4) በማለት አረጋግጦ አስረድቶናል፡፡ የለመኑትን የማይነሣ፥ የነገሩትን የማይረሳ ጌታ ቅድመ ዓለም በልብ ያሰበውን ድኅረ ዓለም በነቢያት ያናገረውን ለመፈጸም ሥጋ ለበሰ፤ ሰው ሆነ፡፡ መምህረ ትሕትና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሠላሳ ዘመን ሲሞላው አብነት ለመሆን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ በመሄድ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስእጅ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡ ተጠምቆም የባሕርይ ልጅነቱን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አስመስክሮ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ፡፡ (ማቴ. 4፥1)
ጌታ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ሄዶ አጥምቀኝ ሲለው ቅዱስ ዮሐንስ “ስመ አብ ብከ፤ ወስመ ወልድ ለሊከ፤ ወስመ መንፈስ ቅዱስ ህልው ውስቴትከ ባዕደ አጠምቅ በስምከ ወበስመ መኑ አጠምቅ ኪያከ — አብ በአንተ ህልው ነው፤ ወልድም አንተ ነህ፤ መንፈስ ቅዱስም በአንተ ህልው ነው ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ፤ አንተን ግን በማን ስም ላጥምቅህ» ቢለው፤ «ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ — ብርሃንን የሚገልጽ የቡሩክ እግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ይቅር በለን» «አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ ጼዴቅ — እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዐት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” እያልክ አጥምቀኝ አለው፡፡ (መዝ. 109/110፥4)
ቅዱስ ጳውሎስም “ወደምሰሰ ለነ መጽሐፈ ዕዳነ በሥርዐቱ እምዕድውነ — በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው» በማለት ገለጸልን (ቈላ. 2፥14)። ቅዱስ ያሬድም “ብርሃን ኮነ በልደቱ ወሰላመ ገብረ በጥምቀቱ — በልደቱ ጨለማው ተወግዶ ብርሃን ሆነ፤ በጥምቀቱም ሰላምን ሰጠን ሰላምን አደረገ አለ፤” አብ በደመና ላይ ሆኖ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር — አብ የምወልደው የምወደው የባሕር ልጄ ይህ ነው” ብሎ ሲመሰክር፤ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ጸዐዳ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ታውቋል፤ ተረጋግጧል (ማቴ. 3፥17)፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ወልድ ለአብም ለመንፈስ ቅዱስም ቃላቸው በመሆኑ አንዱ በአንዱ ህልው መሆኑን በግልጥ አሳይቷል፡፡ እግዚአብሔር የባሕርይ ስሙ፤ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የአካል ስሙ፤ አብ ወላዲ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ የግብር ስሙ፤ ልብ ቃል እስትንፋስ የኩነት ስሙመሆኑን ተረዳ፤ ተገለጠ፡፡
ጌታ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበት ምክንያት፡-
- ዮርዳኖስ ነቁ (መፍለቂያው ምንጩ) አንድ እንደሆነ ሁሉ፥ የሰው ሁሉ ነቁ አንድ አዳም በመሆኑ ነው፡፡
- ንዕማን በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል፡፡ (2ነገ 5፥14)
- ኤልያስ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ብሔረ ሕያዋን ገብቷል፡፡ (2ነገ. 2፥8-14)
- እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምድረ ርስት ገብተዋል፡፡ ((ኢያ. 3፥17)
- የኤልሳዕ ደቀ መዝሙር ምሳሩ ከዛቢያው ወልቆ ከባሕር ቢገባበት ኤልሳዕ ቅርፍተ ዕፅ አመሳቅሎ ቢመታው መዝቀጥ የማይቻለው ቅርፍተ ዕፅ ዘቅጦ መዝቀጥ የሚገባውን ብረት ይዞት ወጥቷል፡ (2ነገ. 6፥1-7) ይኽም ሞት የማይገባው ወልደ እግዚአብሔር በለበሰው ሥጋ ሞቶ ሞት የሚገባው አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ ነው፡፡
- ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ድኗል፡፡
- ብፁዕ አብርሃም አርከ እግዚአብሔር ለአምስቱ ነገሥተ ሰዶም ረድቶ ዐራቱን ነገሥተ ኮሎዶጎሞርን ድል ነሥቶ ሲመለስ ደስ ቢለው “በመዋዕልየኑ ትፌኑ ቃለከወሚመ ታርእየኒሁ ኪያሃ ዕለተ አው አልቦ ቢለው እሱንስ አታየውም ምሳሌውን ታያለህ አለው፡፡” አብርሃም ዮርዳናስን ተሻግሮ መልከ ጼዴቅ ኅብስተ በረከት ጽዋዓ አኰቴት ይዞ ተቀብሎታል (ዘፍ. 14፥18)፥ በማለት ትርጓሜ ወንጌል ላይ ታትቷል፡፡ ይህ ሁሉ ምሳሌ ምእመናንና ምእመናት አምነው ተጠምቀው ገነት፤ መንግሥተ ሰማያት ለመግባታቸው ምሳሌ ነው
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሠላሳ ዓመቱ መጠመቁ፥ አባታችን አዳም የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ ሳለ ልጅነቱን ስላስወሰደ ለዚያ ካሣ ለመሆን ነው።፡ በዚህም “አኮ ዘረከበ ጸጋ በተጠምቆቱ አላ ከመ ያብርህ መካናተ ወኀይል ማያተ ለእለ ሀለዎሙ ይጠመቁ ውስቴታ” እንዲል ሃይማኖተ አበው፡፡ (የተጠመቀውም ኀጢአት ኑሮበት፤ ከኀጢአት ለመንፃት ሳይሆን የሰው ሁሉ ጽድቅ እንደመርገም ጨርቅ ሆኖ ነበርና በጽድቁ ጽድቃችንን ሊያድስልን በጥቀቱ ጥምቀታችን ሊቀድስልን በዮርዳኖስ ተጠመቀ እንጂ በጥምቀት የሚያገኘው ጥቅም አልነበረም፤ የለምም፡፡
በመሆኑም ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕሙማነ ሥጋን በተአምራት፤ ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት ሲያድን ቸርነትን፤ ፍቅርን ርኅራኄን ትሕትናን በማስቀደም ነው፡፡ እነዚህም የክርስቶስ የባሕርይ ገንዘቦቹ ለሰው ልጅም ስጦታዎች ናቸው፡፡ “ከመ ንሕዮ በእንቲአሁ (እሱ ስለካሰልን እንድን ዘንድ) ወዝንቱ ውእቱ ፍቅሩ ለእግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ፍቅሩ ይህ ነው፡፡ፍቅር መሆኑ እኛን መውደዱ ይኽ ነው) አኮ ንሕነ ዘአፍቀርናሁ አላ ውእቱ አፍቀረነ (አስቀድሞ እኛ የወደድነው አይደለም እሱ ወደደን እንጂ) ወፈነዎ ለወልዱ ይኅድግ ለነ ኃጣውኢነ (ፍቅሩ ይህ ነው፡፡ ኀጢአታችን ይቅር ይለን ዘንድ የባሕርይ ልጁን ወደዚህ ዓለም ሰዶታልና) አኀዊነ እመሰ ከመዝ አፍቀረነ እግዚአብሔር ወንሕነኒ ይደልወነ ንትፋቀር በበይናቲነ — ወንድሞቻችን እግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁን እግዚአብሔር ወልድን እስከ መስጠት ድረስ ደርሶ እንዲህ ከወደደን እኛም እርስ በርሳችን ፍቅርን ልንይዝ ይገባናል በማለት የከራድዮን ዖፍጸዓዳ ምሳሌ ንጉሠ ይሁዳ ኢየሱስ ክርስቶስ የአንዱን በደል ሌላው እንዲያቃልለትና ይቅር እንዲለው በመፈቃቀር እንዲኖር አዟል (1ዮሐ. 4፥9-10) የጥምቀት ዓላማም ይህ ነው፡፡
ከላይ እንደተገለጸው የጥምቀት መሠረቱ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ነው፡፡ በዚህ ትምህርትና ሥርዐት ያላለፉ ወይም ይህን ሥርዐት ያልፈጸሙ ሰዎች ክርስቲያን ተብለው መጠራት እንደማይችሉ የእግዚአብሔር ሕያው ቃሉ ይነግረናል፡፡ አምነው የተቀበሉትን የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ስልጣን ሰጣቸው፡፡ (ዮሐ. 1፥12)
ጥምቀት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ዓለም መኖሩን፤ አምጻኤ ዓለማትነቱን፤ በሥጋ መምጣቱን፤ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና መወለዱን፤ በዚህ ዓለም ሠሳሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር መኖሩንና መመላለሱን፤ ይህን ዓለም ለማሳለፍ መምጣቱንና ይኽን ዓለም አሳልፎ መኖሩን የምናውቅብትና የምንረዳበት ምሥጢር ነው፡፡ ወአመርናክሙ ቦቱ ኀይሎ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወምጽአቶ ወሀልዎቶ — የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርሰቶስን ኀይልና መምጣት አስታወቅናችሁ ይላል፡፡ (2ጴጥ. 1፥16)
ስለዚህ ጥምቀት ክርስቲያን ለመሆን የክርስትናን ሃይማኖት፤ ቀኖና እና ትውፊት ተምሮ ዐውቆና አምኖ በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚጠመቁት የሃይማኖት መግለጫና ከእግዚአብሔር የሚወለዱትን ልጅነት መቀበያ ስለሆነ ነሢአ ሐዲስ ልደት፤ኅርየት (መመረጥ) ሕጽበተ ኀጢአት (ከኀጢአት መታጠብ፤ ከኀጢአት መንጻት) ይባላል፡፡ ሰዎች በሥላሴ ስም ተጠምቀው ከሥላሴ አዲስ ልደትን ተቀብለው ውሉደ እግዚአብሔር ሕዝበ ክርስቲያን ይባላሉ፡፡
ወደፊትም በጥምቀታችን በብሉይ ኪዳን የተነገረው ሐዲስ ኪዳን ተስፋ ትንሣኤ ሙታን፤ ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን እንጠብቃለን፡፡ ስለዚህ ሐዲስ ኪዳን በቀለም ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የተጻፈ፥ የኵነኔ ሳይሆን የጽድቅ አገልግሎት ፍሬ፥ ለጊዜው ሳይሆን ለዘለዓለም ጸንቶ የሚኖር፤ ፍጹም ነፃነት ያለው ለተቀበልነው ሁሉ ማለትም በነፍስ ሕያዋን፤ ዘለዓለማውያን የምንሆንበት በጥምቀት በሚገኘው ንጽሐ ሥጋ፥ ንጽሐ ነፍስ፥ ንጽሐ ልቡና ነው፡፡ “ወብነ ባሕቱ ከመዝ ተስፋ በኀበ እግዚአብሔር በእንተ ክርስቶስ፡፡ ወኢይደልወነ ነኀሊ ለሊነ ለርእስነ ወኢምንተኒ፡፡ እስመ እምኀበ እግዚአብሔር ኀይልነ ዘረሰየነ ላእካነ ለሐዲስ ሕግ ወአኮ በሕገ መጽሐፍ አላ በሕገ መንፈስ እስመ መጽሐፍ ይቀትል ወመንፈስ ያሐዩ (በክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን፤ ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳች እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም”፡፡ (2ቆሮ. 3፥-4-6)
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀቱን ለምን በውኃ አደረገው?
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አማን አማን እብለከ ዘኢተወልደ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይክል በዊዓ ውስተ መንግሥተ እግዚአብሔር — ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕፀነ ዮርዳኖስ ሁለተኛ ካልተወለደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት አይቻለውም ብየ በእውነት እንደማይቻለው እነግርሃለሁ” ይላል ሕያው ቃሉ (ዮሐ. 3፥5)፡፡ ውኃም በዙፋን ካለ ንጉሥ በማሕፀን እስካለ ፀኑስ ድረስ የሚገኝ (ርኩብ) ነውና፡፡ ውኃ እድፍን ያነጻል፤ ጥምቀትም ኀጢአትን ያነጻል፡፡ በመሆኑም ጥምቀታችን ካህናት ዕለት ዕለት በሚለውጡት ማየ ገቦ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የጥምቀትን በዓል የምታከብረውና የምትፈጽመው የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በረከተ ጥምቀት ለማሳተፍ እንጂ የተጠመቁትን ዳግም ለማጥመቅ አይደለም፡፡ ኢትዮጵውያን ሊቃውንት በውኃ ተጠምቀን ዳግም ልደት ማግኘታችን መሠረት አድርገው ሲቀኙና ሲፈላሰፉ፡-
ድኅረ ተሰብረ አጽንኦ ለሰብእናነ ልሕኲት
ለብሓዊ ክርስቶስ በማየ ሐዲስ ጥምቀት፤
ትርጒሙም፡-
«ሸክላ ሰውነታችን ከተሰበረ በኋላ ሸክላ ሠሪው ክርስቶስ በሐዲስ የጥምቀት ውኃ እንደገና ለውሶ ሠራው» በማለት ተራቀው አመስጥረው ተቀኝተውበታል፡፡ ስለዚህ በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንበት መብትና እድልን አግኝተናል ማለት ነው፡፡
በመሆኑም ጥምቀትን ስናከብር ከዚህ በታች የተጠቀሱትን እውነታዎች ተረድተን ነው፡፡
- እግዚአብሔር ወልድ በ5500 ዓመተ ፀሐይ መጋቢት 29 እሑድ ቀን በዘመነ ዮሐንስ ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በድንግልና ተፀንሷል፡፡
- እግዚአብሔር ወልድ በ5500 ዓመተ ፀሐይ ታኅሣሥ 29 ማክሰኞ በዘመነ ማቴዎስ ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በድንግልና ተወልዷል፡፡
- እግዚአብሔር ወልድ በ5530 ዓመተ ፀሐይ ጥር 11 ማክሰኞ ቀን በዘመነ ሉቃስ በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ዘካርያስ እጅ ተጠምቋል፡፡
- ጌታ በ30 ዓመቱ መጠመቁ አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ በ40 ቀን ያገኛትን ልጅነት አስወስዶ ነበርና ልጅነቱን እንደመለሰለት ለማጠየቅ በ30 ዓመቱተጠመቋል፡፡
- ጌታእግዚአብሔር ወልድ በ5534 ዓመተ ፀሐይ መጋቢት 27 ዓርብ ቀን ተሰቅሏል፡፡
- በበዓለ ጥምቀት ታቦታተ ሕጉ ከየቤተ ክርስቲያኑ ቤተ መቅደስ ከእየ መንበሩ ተነሥቶ ወደየጥምቀተ ባሕሩ (ወደ ወንዝ) የሚወርድበት ምክንያት ጌታ በእደ ቅዱስ የሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ፈለገ ዮርዳኖስ የመሄዱ ምሳሌ ነው፡፡
በአጠቃላይ ጥምቀት ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጸው “ወአመ አስተርአየ ምሕረቱ ለእግዚአብሔር መፍቀሬ ሰብእ መድኀኒነ፡፡ አኮ በምግባረ ጽድቅነ ዳእሙ በምሕረቱ አድኀነነ በጥምቀት ዳግም ልደት ወተሐድሶ በመንፈስ ቅዱስ — ነገር ግን የመድኀኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መወደዱን በተገለጠ ጊዜ እንደ ምሕረቱ መጠን ለሐዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን” (ቲቶ 3፥4-5) የሚለውን መሠረት አድርገን እኛም በዚህ ዓለም በጥምቀት ሥርዐት በሃይማኖት ይቅር በመባባል በፍቅር፥ በንጽሕና፥ በጽድቅ ጸንተን እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አዞናል፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፤ አሜን።
ሊቀ ካህናት ደረጀ መንግሥቱ
የብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ
ልዩ ጸሓፊ