ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅደስ ሲኖዶስ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ጉዲይ ከመንግሥት ጋር እየተደረገ ስላለውው ውይይት እና የካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊደረግ ስለታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
በስመ አብ፤ ወወልድ፤ ወመንፈስ ቅዱስ አሏደ አምላክ አሜን!!
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ጉዲይ ከመንግሥት ጋር እየተደረገ ስላለውው ውይይት እና የካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊደረግ ስለታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
ሮሜ ፭፤፫-፬ “መከራ ትእግስትን እንዲያደርግ፤ ትእግስትም ፈተናን፤ ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን በመከራችን ደግሞ እንመካለን”
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!
በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቅርቡ ከቤተ ክርስቲያናችን ሃይማኖታዊ፤ ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ ሥርዓት ፍጹም ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በመደራጀት የቤተ ክርስቲያንን መብትና ጥቅም የጎዳ ተግባር መፈጸሙ ይታወሳል፡፡ የተከበረውን የአበው ሐዋርያዊ ሢመተ ኤጲስ ቆጶስነት ሥርዓት በመፈጸማቸው ምክንያት በተፈጠረው የቤተ ክርስቲያንን ሉዓላዊ ክብርና ልዕልና የማቃለል፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውለታ የዘነጋ፣ ሕልውናዋን እና አንድነቷን ለመናድ የተደረገ ከፍተኛ ጥቃት በመፈጸሙና መንግሥትም የቤተ ክርስቲያናችንን ሕግና ሥርዓት፣ እንዱሁም ተቋማዊ ሕልውና እንዱያስከብር እና እንዲያከብር በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡
ከዚህም ውስጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በየካቲት ፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መንግሥት በዚሁ አካሄድ ሕግ እየጣሰ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር እና ልእልና እያዋረደ የሚቀጥል ከሆነ ቤተ ክርስቲያን መንግሥት የጣሰውን ሕግ መሠረት በማድረግ መብቷን የማስከበር እስከ አሁን ድረስ ፍጹም ሰላማዊ የሆነውን እንቅስቃሴዋን አድማሱን በማስፋት በየካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ለማድረግ ያቀደችውንና ያሳወቀችውን ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ያለማንም ከልካይነት በራሷ አደባባይ የምታከናውን መሆኑን ስታሳውቅ ቆይታለች፡፡
በዚሁ መሠረት መንግሥት ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው የሰጠውን ቀነ ገደብ ከግምት ውስጥ በማስገባትና ጥሪውን በመቀበል በየካቲት ፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ለአስቸኳይ ውይይት ዝግጁ መሆኑን በተመረጡ የሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት መልዕክቱ ሲደርሰን ካለው ወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታ አንጻር ጥሪውን በመቀበላችን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የተመራ ዐሥራ ሁለት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣ የኤፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃሊፊዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱም የተነሱት ነጥቦች በዋንኛነት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ፤ ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ ሕግን መሠረት ባደረገ መልኩ ጠብቃ የምትሠራ እና ከዚህ ውጭ ምንም አይነት ድርድር የሌለው መሆኑን ገልጻለች፡፡ በዚህም መነሻ መንግሥት
የቤተ ክርስቲያንን አቋም በመቀበል ወደፊትም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት እና ሉዓላዊነትን በጠበቀ መንገድ እንደሚሠራ አረጋግጧል፡፡
በዚህ የፈተና ጊዜ ውስጥ የቅዱስ ሲኖዶስን መመሪያ በመቀበል ራስን ለቤተ ክርስቲያን ሕልውና መስዋእት አድርጎ በማቅረብ፤ በክርስቶስ ደም የከበረችውን ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ እና ለማስጠበቅ ከጸጉር መላጨት እስከ ገመድ መታጠቅ በእንባና በዋይታ መሊው ሕዝበ ክርስቲያን ሀዘናችሁን የገለጻችሁበት መንገድ ለቤተ ክርስቲያን ሕልውና ማስጠበቅ መሠረት ሁኗል፡፡ በዚህም ሂደት ሕይወታቸውን በሰማእትነት፤ አካላችሁን ለአካል ጉድት፤ ኑሯችሁን ለፈተና ፤ ለስደት፤ ለእንግልት እንዱሁም ለእስራት አሳልፋችሁ የሰጣችሁ ልጆቻችን ቅዱስ ሲኖዶስ ሁሌጊዜም ውለታችሁን ሲያስታውስ የሚኖር ሲሆን የጉዳት ሰለባ ለሆኑቱም መንግሥት የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለይቶ በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንደሚያደርግ እና አሁን ላይ እስር፤ ወከባ፤ እንግልት እየተፈጸመባቸው ያለት ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የሀገረ ስብከት ሠራተኞች፤ አገልጋይ ካህናት እና በተለያዩ አደረጃጀቶች የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች ችግሩ በአስቸኳይ እንዲቆምና የታሠሩትም እንዲፈቱ፤ አገልግሎታቸውን በሰላምና በነጻነት መስጠት እንዲችሉ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በትናትናው እለት ከመንግሥት ጋር ባደረግነው ውይይት መንግሥት የቤተ ክርስቲያኒቱን አቋም ሙሉ በሙሉ የተቀበለ ቢሆንም ይህንን ለማስፈጸም የሚያስችል የአፈጻጸም የድርጊት
ጊዜ የሚያስፈልግ በመሆኑ እሁድ የካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም እንዲካሔድ የተወሰነው ሀገር ዓቀፍ እና ዓለም አቀፍ የአደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ለተወሰነ ጊዜ እንዱራዘም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ በዚሁ እለትም ሁለም ሕዝበ ክርስቲያን በየአጥቢያችሁ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ዐውደ ምሕረት ላይ ባለመቅረት የተለመደውን የእለተ ሰንበት የሥርዓተ ቅዳሴ፤ የጸሎት፣ የምሕላ እና የትምህርተ ወንጌል ከወትሮው በተለዬ የመንፈሳዊ ሥርዓት በማከናወን እንድታሳልፉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
የተከበራችሁ ውድ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤
ቅዱስ ሲኖዶስ በየካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የጠራውን ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ለተወሰኑ ቀናት እንዲተሊለፍ ያደረገው የአቋም ለውጥ አድርጎ ሳይሆን አስቀድማ ቤተ ክርስቲያናችን በሮቿን ለሰላም ክፍት በማድረግ ባስተላለፈችው ጥሪ እና በአስቀመጠችው ቀነ ገደብ መሠረት በመንግሥት በኩል ወዲያውኑ ችግሩን ለመፍታት ፍላጎት በማሳየቱ ምክንያት ብቻ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ ነገር ግን መንግሥት የገባውን ቃል እና የወሰነውን ውሳኔ የማይፈጽም ከሆነ መንፈሳዊ ተጋድሏችን የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ይህ ሂደት በባህሪው ረዥም ተጋድሎ እና ጽናት የሚጠይቅ በመሆኑ እስከ አሁንም በፍጹም አንድነት እና መደማመጥ የቅዱስ ሲኖዶሱን ድምጽ እየሰማችሁ በአንድነት እና በሕብረት እንደቆማችሁት ሁሉ ወደፊትም የቅዱስ ሲኖዶስን ድምጽ በትጋት እንድትጠብቁ እያሳሰብን በሕግ የተያዙት ጉዳዮችም የሕግ ሂደታቸውን ተከትለው የሚቀጥሉ መሆኑን እና እኛም
በልዩ ሁኔታ የምናሳውቃቸው መሆኑን እንገልጻለን፡፡
መንግሥትም የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ተቀብል የውይይት መድረክ በማዘጋጀት የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በማክበር በውሳኔው መሠረት የሚፈጸም መሆኑን ስላረጋገጠልን ቤተ
ክርስቲያን ታመሰግናለች፡፡ በተጨማሪም በዚህ የፈተና ወቅት በየደረጃው የምትገኙ በሀገር ውስጥ እና በመላው ዓለም የምትገኙ የቤተ ክርስቲያናችን የሥራ ኃላፊዎች፤ ሉቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ መነኮሳት፤ አገልጋይ ካህናት፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፤ ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ማህበራት እና መላው ምእመናንና ምእመናት እንዱሁም ከቤተ ክርስቲያኗ ጎን የቆማችሁ እና አጋርነታችሁን የገለጻችሁ የሃይማኖት ተቋማት፤ የሕግ ባለሙያዎች፤ ግለሰቦች፤ የማህበረሰብ አንቂዎች፤ የጥበብ ሰዎች፤ የሰብዓዊ መብት ተቋማት እና በዚህ ሂደት ውስጥ ድጋፍ ስትሰጡ የነበራችሁ የተለያዩ አካላት ቤተ ክርስቲያን እያመሠገነች ወደፊትም ልዩ ዕውቅና የምትሰጥ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡
በመጨረሻም ቅዱስ ሲኖዶስ በጀመረው ፍጹም ሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ከመንግሥት ጋር የደረስንበትን ውጤት በየጊዜው የምናሳውቃችሁ ስለሆነ እንደዚህ ቀደሙ ፍፁም በሆነ መንፈሳዊ ጨዋነት የቅዱስ ሲኖዶስን መሌእክት እንድትጠባበቁ፤ አሁንም ቢሆን ያለመዘናጋት ቤተ ክርስቲያናችሁን በጥብቅ ሁኔታ እንድትጠብቁ እና ቤተ ክርስቲናችሁ ላይ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ሁለ በተዋረድ ላለው መዋቅራችሁ እንድታሳዉቁ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
ያዕቆብ መሌእክት ፩፤፪-፫ “ወንድሞቼ ሆይ የእምነታችሁ መፈተን ትእግስትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፤ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደሙሉ ደስታ ቁጠሩት”
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
የካቲት ፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም
አዱስ አበባ ኢትዮጵያ