ሕዳር 12 ቀን 2017ዓ.ም.
+ + +
በሀገራችን ኢትዮጵያ በሽዎች የሚቆጠሩ በቅዱስ ሚካኤል ስም የተሰየሙ አብያተ ክርስቲያናት ሲኖሩ በሁሉም በሚባል ደረጃ ሰላማዊ የሆነ በዓል መከበሩን በየሥፍራው የደረሱን የሕዝብ ግንኙነት መረጃዎች ያመላክታሉ። በዓሉ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ ያደረገውን መልአካዊ ድርሻ ታሳቢ በማድረግ የሚከበር ሲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች በሚገኙበትና የመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል መታሰቢያ በሚደረግበት ቦታ ሁሉ ታቦተ ህጉ ከመንበረ ክብሩ ወጥቶ ሕዝቡን ይባርካል።
በሁሉም አህጉረ ስብከት በዚህ ስርዓት መሠረት በዓሉ የተከበረ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን የሲዳማ ፣ የጌዲኦ፣የሰሜን ወሎ ፣ የከሚሴ፣ የምስራቅ ሐረርጌ፣ የመተከል እና የድሬ ዳዋ አህጉረ ስብከት ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኀላፊዎች በየሀገረ ስብከታቸው የቅዱስ ሚካኤል በዓል አከባበር ምን እንደሚመስል ለመምሪያችን ሪፖርት ከላኩልን አህጉረ ሰብከት መካከል ናቸው።
ከሪፖርቱ እንደተመለከተነው የአህጉረ ስብከት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በዓሉን የመሩት ሲሆን ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ባለ ሥልጣናት ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች በክብረ በዓሉ እንደታደሙ ተገልጿል።