መስከረም 16/2017 ዓ.ም
በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላ ከተማ የመስቀል ደመራ በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ክብር ተከበረ ።
በዕለቱም የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ የርቀትና ኦን ላይን ኮሌጅ ዲን ሊቀ ህሩያን አባ ገ/ሐና ፣የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ብርሃኑ ክፍሌ ፣ የሀገረ ስብከቱ የየክፍል ኃላፊዎች ፣የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ዝናቡ ወልዴ፣ የዲላ ከተማ ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሽፈራው፣ የጌዴኦ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበባየሁ ኢሳይያስ፣ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ የሰንበት ት/ቤት ዘማሪያን የዲላ ከተማና አካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ተገኝተዋል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ያደረገልንን የማዳን ሥራ መስበክ ለክርስቲያኖች ቀዳሚ ተግባር መሆኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የጌዴኦ ኮሬ ቡርጂ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ክቡር መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ በሚከበረው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የቅዱስ መስቀል የደመራ በዓል ላይ በመገኘት የእንኳን አደረሳችሁ መግለጫ አስተላልፈዋል።
ክቡር ሥራ አስኪያጁ በመግለጫቸው “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው” ብሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልእክቱ የጻፈውን በመጥቀስ እኛ ክርስቲያኖች ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ያደረገልንን የማዳን ሥራ መስበክ ለእኛ ክርስቲያኖች ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል።
በመጨረሻም ለበዓሉ መሳካት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉትን የመንግሥት አካላት የፖሊስ ኃይሎችን ፣ የሃገረ ስብከቱን የየክፍል ሃላፊዎችን ፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ሰራተኞችን ፣ የየአድባራቱን አስተዳዳሪዎች ፣ ካህናቱን እንዲሁም በበዓሉ የተገኙ ምዕመናንን በማመስገን መግለጫቸውን አጠናቀዋል።
የዕለቱን ትምህርትና ያስተማሩትና መልዕክት ያስተላለፉት የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ የርቀትና ኦን ላይን ኮሌጅ ዲን ሊቀ ህሩያን አባ ገ/ሐና ሲሆኑ ለሚፈሩኸ ምልክትን ሰጠኻቸው በማለት ስለ ቅዱስ መስቀል ክብር በሰፊው አስተምረዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ዝናቡ ወልዴ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ለዘመናት ታሪክን ቅርስን የጠበቀች የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መሆኗን ገልጸዋል።
የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሽፈራው በመልዕክታቸው የመስቀልን ክብር አንስተው የደመራን ትርጉም በመዘርዘር ይኸን የቅዱስ መስቀል በዓልን ማክበራችን በህላዊና መንፈሳዊ ዕሴታችንን ማስቀጠል ይገባናል በማለት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትን አስተላልፈዋል።
በበዓሉ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እና የሰንበት ት/ቤት አንድነት ያሬዳዊ ወረብን አቅርበዋል። በሊቀ ህሩያን አባ ገ/ሐና ቡራኬና ጸሎት ተደርጎ በሀገረ ስብከቱ ሥራአስኪያጅ በመልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ እና በክቡር የዞኑ አስተዳደር የጋራ የደመራ መለኮስ ሥነ ሥርዓት ተከናውኖ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።