በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና በሰሜን አሜሪካ የኒዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ሔኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
የሰላም አለቃ፣የምሕረት አባት የሆነው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስት የሆነችውን በዓለ ትንሣኤውን አክብረን ይህንን የረክበ ካህናት ቀኖናዊና ሲኖዶሳዊ ጉባኤ እንድናካሂድ ስለሰበሰበን ክብርና ምስጋና፣ አምልኮና ውዳሴ ለእሱ በማቅረብ፣እንኳን ደኅና መጣችሁ ለማለት እንወዳለን፡፡ “ወይእዜኒ ንትልዋ ለሰላም በዘይት ሐነጽ ቢጽነ፡-እንግዲያው ስለሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምታነጽበትን እንከተል” (ሮሜ. ፲፬፥፲፱)፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
በቅዱሳት መጻሕፍት በግልፅ እንደተቀመጠው እኛ የምናገለግላት ቤተክርስቲያን በምድር ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት ማእከል ናት፤ የተመሠረተችውም በደመ ክርስቶስ ነው፡፡
የእግዚአብሔር መንግሥት ማእከል የሆነችው ቤተክርስቲያን ልትሰራው፣ልትጠብቀውና ልትፈጽመው የተሰጣት ዓቢይ ተልእኮ አለ፤ እሱም በእግዚአብሔርና በሰው፣ በሰውና በሰው መካከል ፍጹም ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ነው፤
ይህ ዓቢይ ተልእኮ የሰማይና የምድር መዝሙር ሆኖ ሁሌም በመደበኛ ይዘመራል፤ጌታችንም ከሞት ከተነሣ በኋላ ያሰማው የመጀመሪያ ድምፅ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” የሚል ነው፡፡
የጌታ ምርጥ ንዋይ የተባለው ቅዱስ ጳውሎስም ”ሰላም የሚቆምበትን እንከተል” ሲል የሰላምን ተቀዳሚ አስፈላጊነት በአጽንዖት አስተምሮናል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ሰላምን በቀዋሚ ምሰሶ አምሳላዊ ንጽጽር ገልፆአታል፡፡
ይህም ማለት ምሰሶ የቤትን ጣራ በቀዋሚነት ተሸክሞና ቀጥ አድርጎ እንደሚይዝ፣ሰላምም በተመሳሳይ የሰዎችን መንፈሳዊና አካላዊ ሕይወት ቀጥ አድርጋ የምትይዝና የምትጠብቅ መሆኗን ለመግለፅ እንደሆነ እንገነዘባለን።
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
እኛ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከኛ በታች ያሉ ውሉደ ክህነት፣እንዲሁም በእግዚአብሔር የልጅነት ጸጋ የከበሩ ምእመናንና ምእመናት ሁሉ፣ የቤተክርስቲያን መደበኛና ቀዋሚ ተልእኮ የሆነውን ሰላም የመጠበቅ፣ የማስጠበቅ፣ የማሥረጽና የማስቀጠል ኃላፊነት እንዳለብን ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡
በእግዚአብሔርና በሰው፣ በሰውና በሰው መካከል አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ጠንክሮ የማስተማር፣ የመምከርና የማስታረቅ ኃላፊነት የእኛ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር ዛሬ የተሰበሰብነው የተሰጠን አምላካዊ ተልእኮ ምን ያህል በተግባር አከናውነናል? ምን ሰርተናል? ምንስ ይቀረናል? ተልእኮአችንን ለመፈጸም በምናደርገው ጉዞስ ምን ችግር አጋጠመን? ችግሩን ለመፍታትስ ምን እናድርግ? የሚሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች በማንሣት በዝርዝርና በጥልቀት በማየት ተልእኮአችንን በኣግባቡ ለመወጣት ነው፡፡
የቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናም ከበዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያአምስተኛው ቀን የረክበ ካህናት ዓቢይ ጉባኤ እንዲደረግ ያዘዘበት ዋና ምክንያት ይህንን እንድናደርግ ነው፡፡
ሁላችንም እንደምንገነዘበው በአሁኑ ጊዜ ቤተክርስቲያናችን እንደ ቤተክርስቲያን፣ሕዝባችንም እንደ ሕዝብ በፈተና ውስጥ እያለፉ ያሉበት ጊዜ ነው፡፡
በመሆኑም ከምንም ጊዜ በላይ በአሁኑ ጊዜ በልዩ ትኩረት የምናያቸው ጉዳዮች እንዳሉ መገንዘብ ይኖርብናል፤የቤተክርስቲያናችንና የሕዝባችን ችግሮች የተራዘሙ እንዳይሆኑ ለቤተክርስቲያናችን ምጥዋን ሆነን የምንሰራበት ጊዜ አሁን እንደሆነ በውል ማወቅ ይኖርብናል፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!!
ጌታችን፡- “እንደ ርግብ የዋሆች፣ እንደ እባብም ብልሆች ሁኑ” ብሎ ያስተማረንን ጥበብ በዚህ ጊዜ በሚገባ መጠቀም ይኖርብናል፡፡በቤተክርስቲያን አጋጥመው ያሉ ችግሮች በዚህ ጥበብ ካልሆነ በቀር በመሳሳብና እልክ በመጋባት የሚፈቱ አይደሉም፡፡
በተለይም በትግራይና በኦሮምያ አካባቢዎች ያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎች ከቤተክህነት አልፈው የሕዝብም ጭምር እየሆኑ ስለመጡ የሕዝቡን ጥያቄ በትክክል በማዳመጥ ሃይማኖቱንና ቀኖናውን በጠበቀ መልኩ በጥበብና በፍቅር ጥያቄአቸውን አክብረን መቀበል ያሻል፤ ጉዳታቸውንም መካፈል ይገባናል፡፡በአጠቃላይ አባትና እናት ለልጆቻቸው ሊያደርጉት የሚገባውን በማድረግ ልናቀርባቸውና ልናቅፋቸው ይገባል፡፡
እኛ ያጐደልነው፣የተሳሳትነውና ያስቀየምነው ካለም ይቅርታ ለመጠየቅም ሆነ ንስሐ ለመግባት ድፍረቱ ሊኖረን ይገባል፡፡ ታረቁ፣ ይቅር በሉ፣ንስሐ ግቡ ብለን የምናስተምር እኛ ይቅርታ ለመጠየቅና ንስሐ ለመግባት ዓቀበቱ ሊከብደን አይገባም፡፡የተከሠተው ችግር በዚህ ክርስቶሳዊ ጥበብ ሊቃለል እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡
በሌላ በኩል በሀገራችን ያለው የሰላም ሁኔታ በአንድ ወገን የተረጋጋ ሲመስል በሌላ በኩል ደግሞ የመንገጫገጭ ሁኔታ እየተከሠተ እንደሆነ እያየን ነው፡፡ይህም ሂዶ ሂዶ ቤተክርስቲያንንና ሕዝብን፣ ሀገርን ልማትን መጕዳቱ የማይቀር ነው፡፡
በመሆኑም ቤተክርስቲያን ያለ ሀገርና ያለ ሕዝብ ህልውና የላትምና ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት፣ የሕዝቦቿን አንድነትና ልማት ለማረጋገጥ፣ በሃይማኖታዊ መርሕና መንፈስ፣በገለልተኛ አቋምና በሁሉም ዓቃፊነት ስልት ለሰላም ጠንክረን መስራት ይኖርብናል፡፡
ከዚህም ጋር የዛሬው ጉባኤ የቤተክርስቲያናችንን ዓቢይ ተልእኮ ለመፈጸም እንደመሳሪያ ሊያገለግሉ ይችላሉ ተብሎ ታምኖባቸው የተጀመሩትን ወሳኝ ስራዎች በዝርዝር በማየት ውሳኔ የምናሳልፍበት ጉባኤ ይሆናል፡፡
ከዚህም ሌላ በተፈጠረው አላስፈላጊ ከባድ ጦርነት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የፈራረሱ አብያተ ክርስቲያናትና የተፈናቀሉ ምእመናን ልጆቻችንን በፍጥነት ደርሰን የምናጽናናበትንና የምንደግፍበትን ሁኔታ በዚህ ጉባኤ ማየት ይኖርብናል፡፡
በመጨረሻም
በአሁኑ ጊዜ ኣላስፈላጊ በሆነ የእርስ በርስ ግጭት እየተሳተፉ ያሉ ወገኖች ግጭቱን ኣቁመው በሰላማዊ ውይይት ችግሮችን ለመፍታት እንዲጥሩ ኣባታዊ ጥሪያችንን በአጽንዖት እያስተላለፍን የ፳፻፲፭ ዓ.ም የረክበ ካህናቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በጸሎት የተከፈተ መሆኑን ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት እናበስራለን።
እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክልን!
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ !!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር !!!
አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ
ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
አዲስአበባ – ኢትዮጵያ