የካህናት አስተዳደር መምሪያ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊት፣ ታሪካዊትና ብሔራዊት፣ ዓለም አፋዊት ቤተ ክርስቲያን በመሆንዋ መንጋዋን ለመጠቅ ያለባት ኃላፊነትም በዚሁ መጠን ስፋትና ጥልቀት፣ ታማኝነትና ጥቡዕነት ያለው መሆኑ በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ሑሩ ወመሐሩ ውስተ ኲሉ ምድር ወእንዘ ታጠምቅዎሙ በሉ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ›› ማቴ. ምዕ. @8 ቁ .@9 የሚለው አምላካዊ ተልዕኮ ለመፈጸም በተለይም በሥነ ምግባር የታነጹ ፣ በእውቀት የረቀቁ፣ በስብከተ ክህነት የታደሉ ሊቃውንት፣ ካህናትና ዲያቆናት በማስተማርና በማብቃት የካህናት አስተዳደር መምሪያ ግንባር ቀደም ሆኖ እየሠራ ይገኛል፡፡
የካህናት አስተዳደር መምሪያ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ተፈጻሚ የሚሆን መዋቅር ያለው ነው፡፡
በመንፈሳዊ አገልግሎት ረገድም እስከ እያንዳንዱ ክርስቲያን የሚደርስ የሚተገበር ተልዕኮ ያለው ነው፡፡
የካህናት አስተዳደር መምሪያ የዘመኑ ትውልድ በሚፈልገው መጠን ሊቃውንትንና ካህናትን፣ ዲያቆናትን፣ አገልግሎቱ ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ ከሁሉ በፊት ቀድሞ እንዲሠራ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት በትምህርተ ወንጌል እንዲበቃ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡
የካህናት አስተዳደር መምሪያ ራዕይ
- በሀገርና ከሀገር ውጭ ባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የካህናት አስተዳደርና የመንፈሳዊ አገልግሎት በየደረጃው በተዋቀሩት ተቋማት አባል የሆኑና ለመሆን እየዘጋጁ ያሉ ክርስቲያኖች ፍጹም ሃይማኖታዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል፡፡
- የቤተ ክርሰቲያን የአገልግሎት ሥርዓት በየጊዜው በልዩ ልዩ ቋንቋዎችና ሕዝቦች እንዲስፋፉ ከሁሉም የአለም ክፍሎች ዲያቆናትና ካህናት እንዲሁም ምዕመናን ከትውልድ ወደ ትውልድ ክርስትናን የሚታደጉ ማፍራት ነው፡፡
የካህናት አስተዳደር መምሪያ ተልዕኮ፡
- ‹‹ አንተ ኮክኅ ወዲበ ዛቲ ኮክኅ አሐንጻ ለቤተ ክርስቲያንየ ወእኁበከ መራኁተ ዘመንግሥተ ሰማያት›› በተባለው አምላካዊ ትእዛዝ መሠረት ካህናት፣ ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን፣ አበው መነኮሳት በተሰጣቸው የክህነት ሥልጣንን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓተ ሃይማኖትን በትክክል አውቀውና ጠብቀው የተልዕኮ ሥራቸውን በሚገባ መፈጸማቸውን፣ ከምዕመናን ጋር ያላቸው ግንኙነት፣ ሥርዓትን የተከተለ ሆኖ ምዕመናን በእነርሱ ምክርና ትምህርት አሰጣጥ በትክክል የተጠቀሙ መሆናቸውን እየተከታተለ ማረጋገጥ፡፡
- ማናቸውም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አድባራትም ሆኑ የገዳማት መነኮሳት ሁሉ ስለ ካህናትና ገዳማውያን መነኮሳት በሚወጡ ደንቦችና ውሳኔዎች መሠረት ተጠብቀው መገኘታቸው በቅርብ እየተቈጣጠረ ማስፈጸም ነው፡፡ በየገጠሩ በየደብሩና በየገዳማቱ ያለው የካህናት አገልግሎት የቤተ መቅደስ ዝግጅት በሚገባ እንዲፈጸም ማድረግ፡፡
- ሊቃውንት፣ ካህናት፣ መነኮሳት፣ በትምህርታቸው በአገልግሎታቸውም የተሻሉ ይሆኑ ዘንድ የሥልጠና ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡
- የበዓላት አከባበርና ሥነ ሥርዓት፣ የቤተ ክርስቲያን ሕግ በሚፈቅደው መሠረት መፈጸሙን በሥሩ ባሉት የመዋቅር የዕዝል የሰንሰለት መሠረት በቅርብ እየከታተለ ማረጋጥ ነው፡፡
- ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሚገኙበት በዓልና የስብሰባ መድረኮች ሁሉ በመገኘት ስነ ሥርዓት ማስከበር ነው፡፡
የካህናት አስተዳደር መምሪያ እሴቶች፡፡
- በቅድስና ምሳሌያዊ የሆነ ክህነታዊ አገልግሎት ተቋማዊ ክህነታዊ አገልግሎት በይዘት፣ በአኗኗርና በድርጊት ቅድስናን የሚመሠክር እግዚአብሔር አምላክ ያዘዘን ትእዛዝ የሚተረጉም መሆኑን ማረጋገጥ፡፡
- ጽናትና ታማኝነት በተየትኛውም ጊዜ፣ በደስታም በፈተናም፣ በማጣትም ውስጥም በማግኘትም፣ ለክርስቲያናዊ ማንነትና ለሰው ልጅ መጽናትን መታመንን አርአያ መሆን፡፡
- ኖላዊ ኄር ፡- ሊቃውንት ካህናት፣ መነኮሳት፣ በፍቅር የሆነ አገልግሎት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን በመጠበቅ በማስተማር፣ በማጽናናት፣ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ያሉት የሰው ልጆች በትምህርትና በኑሮ ምሳሌነት ለማምጣት ኖላዊ ኄር ሆነው ማገልገል፡፡
- የንሥሓ አባትነት ፡- የእግዚአብሔር አደራ የተቀበሉ ካህናት፣ ሊቃውንት፣ ዛሬ ያለው ትውልድ በእውነት መንገድ እንዲጓዝ በሥነ ምግባር፣ በሃይማኖት፣ ትምህርት፣ ማነጽ ማስተማር፣ በማዕሠረ ኃጢአት የተያዘውን በክህነት ሥልጣን መፍታት፣ ለዘለዓለማዊ ሕይወት ማዘጋጀት በሥጋሁ ወደሙ ተወስኖ እንዲኖር ማድረግ፡፡
- ለነገው ትውልድ ፍቅርን፣ ማስተዋልን፣ ጥበብን፣ አርአያ ተጋድሎን፣ ጽናትን፣ እንዲኖረው በክርስትና ላይ የተደቀነውን ፈተና የመቋቋሚያ አቅም እንዲያዳብር በእውቀት የመነጠቀ በኢኮኖሚያዊ አቅሙ የተደራጀ ትውልድ መፍጠር ክርስትናን ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግ ምሳሌ መሆን ነው፡፡