መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም

በሰሜን ወሎ መንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ቤተክህነት የጉባላፍቶ ወረዳ ቤተክህነት ጽ/ቤት 43ኛ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤውን ትናንት በወልድያ የጁ የባሕል ማዕከልና ቤተመዘክር አካሒዷል።

ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የሀገረ ስብከታችን ዋና ሥራ አስኪያጅና ዋና ጸሓፊ ወረዳ ቤተክህነቱ ያስገነባውን ባለ 3 (፫) ወለል የገቢ ማስገኛ ሕንጻ ጎብኝተዋል፤ ብፁዕነታቸው በመሰብሰቢያ አዳራሹ ተገኝተው ጉባኤውን በመምራት ትምህርትና አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል።

በ2016 የአገልግሎት ዓመት ወረዳ ቤተክህነቱን ጨምሮ በገዳማት፣ አድባራትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የተከናወኑ የተግባራት አፈጻጸም ሪፖርትና የሀገረ ስብከቱን ዓመታዊ እቅድ መነሻ በማድረግ የተዘጋጀውን የወረዳ ቤተክህነት የ2017 ዓ.ም ዓመታዊ እቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የመረጃ ምንነት፣ አስፈላጊነትና አደረጃጀትን አስመልክቶ በሀገረ ስብከቱ የዳታቤዝ ባለሙያ ገለጻ ተደርጓል። የቤተክርስቲያኗን አጠቃላይ መረጃዎች አደራጅቶ ለመያዝ ታስቦ የተዘጋጀው ቅጽ ላይም ማብራሪያ ተሰጥቷል። በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ መመሪያ ሰጭነት በሀገረ ስብከቱ በተያዘው የአገልግሎት ዓመት ልዩ ትኩረት የተደረገባቸው ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በተመለከተ በሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሓፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ሊቀ ጳጳስ በእቅድ የተያዙ ተግባራት በሀገረ ስብከቱ፣ በወረዳ ቤተክህነቱ፣ ገዳማትና አድባራት በመደጋገፍ መሥራት እንደሚገባ የቤተክርስቲያኗ ገንዘብና ሀብትን በአግባቡ ማስተዳደር፣ ብልሹ አሠራርን መቀነስና የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ በትኩረት እንዲሠራ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል።

በመጨረሻም በወረዳ ቤተክህነቱ ከሚገኙት 182 አብያተ ክርስቲያናት መካከል በተጠናቀቀው የአገልግሎት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ሰበካ ጉባኤያትና ግለሰቦች ዕውቅና ተሰጥቷል።

ደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላን ጨምሮ በሀገረ ስብከቱ 14 ወረዳ አብያተ ክህነት እንደሚገኙ የሚታወስ ነው።

መረጃው የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ነው።