ጥር ፮ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
****
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
+++++++++++++
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስ
ኪያጅ፣የባህር ዳር፣የሰሜን ጎጃምና የዐቢይ ኮሚቴው ሰብሳቢ በጃን ሜዳ ባህረ ጥምቀት በመከናወን ላይ የሚገኘውን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ከዐቢይ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን ተዛውረው ተመለከቱ።
በጉብኝቱ ወቅት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በሰጡት አባታዊ የሥራ መመሪያ በሁሉም ንዑሳን ኮሚቴዎችና በጃን ሜዳ የተከናወኑት ሥራዎች ምስጋና የሚገባቸው መሆኑን ጠቅሰው ቀሪ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሁሉ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲከናወኑና የሚያጋጥሙ ችግሮች ካሉም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በሚደረግ ግንኙነት መፍትሔ እንዲሰጥባቸው አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል።
አያይዘውም በዓሉ ባማረና በደመቀ መልኩ ተከብሮ ይውል ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ በተለይም ወጣቶች ከቤተክርስቲያን ማዕከላዊ አስተዳደር የሚሰጡ መመሪያዎችን በሙሉዕነት በመተግበር የቤተክርስቲያናችሁን ጥሪ መፈጸምና ማስፈጸም ይኖርባችኋል ካሉ በኋላ ይሁ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጠው በዓላችን ያለምንም እንከን ባማረ ሁኔታ ተከብሮ መዋል እንዲችል ሁላችንም የሚጠበቅብንን ሁሉ በትጋት መፈጸም ይኖርብናል ብለዋል።
በጠቅላይ ቤተክህነት የተቋቋመው የጥምቀት በዓል ዐቢይ
ኮሚቴ ሲያከናውናቸው የሰነበተውን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በትላንትናው ዕለት የገመገመ ሲሆን በግምገማው በንዑሳን ኮሚቴዎች የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ቀርበው ውይይት የተደረገባቸዋል። በአፈጻጸም የተስተዋሉ ክፍተቶች በአስቸኳይ ተሟልተው እንዲፈጸሙም አቅጣጫ መቀመጡ ይታወሳል።