ጥምቀት በተዋሕዶ

መግቢያ

“ወአገሐዶ ዮሐንስ ወአጥመቆ በውስተ ዮርዳኖስ ተመከረ በገዳም ወተዐውቀ ከመ እግዚአብሔር ውእቱ’ ‘ዮሐንስ ገለጠው ፤ በዮርዳኖስም አጠመቀው ፤ በገዳም ተፈተነ ፤ እርሱም የባህርይ አምላክ አንደ ሆነ ታወቀ” (ሃይ.ም.7ገጽ 30)

ጥምቀተ ክርስቶስ ለምንና እንዴት እንደ ሆነ ቅዱስ ሄሮኔዎስ “ዮሐንስ ገለጠው ፤ በዮርዳኖስም አጠመቀው….” በማለት “ጥምቀት” የመገለጥ በዓል እንደ ሆነና በሥጋ የተገለጠው ወልደ እግዚአብሔር ወልደ እጓለ እመሕያው ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን በመገለጡ ተዋናይና ምሥክር የሆነው ደግሞ መጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ነው። ጥምቀት በግእዙ ተጠምቀ ተጠመቀ ፤ ተዘፈቀ ፤ ብቅ ጥልቅ አለ ማለት ነው። በግርከኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎችም “አጲፋንያ” “ኤጲፋኒ” (epiphaneia/ἡ ἐπιφάνεια/Epyphany) የሚለው ቃል መገለጥ ፤ መታየት ማለት ነው። ትንቢቱ ሲፈጸም ፤ ጊዜው ሲደርስ የተገለጠው ወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ቅዱስ ዮሐንስ:- “ወአንሰ ኢያአምሮ ዳእሙ ከመ ያእምርዎ እስራኤል በእንተዝ መጻእኩ አነ ከመ አጥምቅ በማይ’ ‘እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ”(ዮሐ.1:31) ይላል። የጥምቀት ክብረ በዓልን ዐውድ ስንመለከት የአደባባይ በዓልና ከስሙ ትርጉም ጋር የሚዛመድ ነው። ጥምቀት ዘርፈ-ብዙ ምሥጢራት የሚተነተኑበት ኃይለ ቃል ሲሆን በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው ግን “ጥምቀት በተዋሕዶ” በሚል ርእስ በሥሉስ ቅዱስ የተገለጠውና ለአማንያን የተሰጠው “አንድነት”ን ብቻ የሚመለከት ይሆናል።

 

1. የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በጥምቀት

ሥላሴ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ የሦስትነት ስም ነው። በቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ አግዚአብሔር አምላክ ስነ ፍጥረትን መፍጠር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአንድነትና በሦስትነት ሲጠራ አንደ ነበረ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አስረግጠው ይናገራሉ። ለምሳሌ “እግዚአብሔርም አለ። ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” (ዘፍ.1:26) ፤ “እግዚአብሔር አምላክም አለ። እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” (ዘፍ.3:21) ሲል ከአንድ ቁጥር በላይ መሆኑን ሲያመለክት የሚከተሉት ጥቅሶች ደግሞ ሦስትነቱን ያረጋግጣሉ። “ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ ፤ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፥ ወደ ምድርም ሰገደ፥ እንዲህም አለ። አቤቱ፥ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ ”(ዘፍ.18:1) የሚለውና “አንዱም ለአንዱ። ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር” (ኢሳ. 6፡3) ተብሎ የተጻፈው ነው።

በባህረ ዮርዳኖስ የታየው ምሥጢረ ሥላሴ ግን ልዩ መገለጥ ነው፡፡ ይኽም ወልድ በተለየ አካሉ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ ፤ አብ በደመና ሆኖ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው›› ብሎ ሲናገር ፤ መንፈስ ቅዱስም በተለየ አካሉ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲቀመጥ መታየቱ ነው። “ወወረደ መንፈስ ቅዱስ ላዕሌሁ በሥጋ በርእየተ ርግብ…..መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ” (ሉቃ.3:22) እንደሚለው በተለየ አካል ፤ በተለየ ስም ፤ በተለየ ሥፍራ መገለጡ በጥምቀተ ክርስቶስ አንድነቱን በሦስትነት ፤ ሦስትነቱን በአንድነት የሚያሳይ ዕፁብ ድንቅ ምሥጢር ነው፡፡

ይኽ የሦስትነትና የአንድነት መገለጥ እስራኤል ዘሥጋ እንዲያውቁትና ከነርሱ ወገን ከሆነችው ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ፤ በተዋሐደው ሥጋ መከራ መስቀልን ተቀብሎ የሰው ልጅን ከዲያብሎስ ግዞት ነጻ የሚያወጣው እርሱ እንደ ሆነ የአብን ምሥክርነት ሰምተው እንዲያምኑበት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ለሊሁ ወረደ መንፈስ ቅዱስ ሠለስቲሆሙ እለ እሙንቱ እለ ይከውኑ ሰማእተ›› (ድጓ ዘጥምቀት) አንዲል፡፡

የሥላሴ ሦስትነትና አንድነት በምእመናን ሕይወት ጥልቅ ትርጉም አለው። ጥምቀተ ክርስቶስ እኛ ብዙዎች ስንሆን በእርሱ አንድ ሕዝብ መሆናችንን ፤ ልጅነት የምታሰጥና የአንድነታችን ምሥጢር የሆነችውን ጥምቀት በጥምቀቱ የመሠረተልን መሆኑን የምንማርበት ነው። “…ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን” (ሮሜ.12:5)። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ” (ዮሐ.17:23) በማለት በሥሉስ ቅዱስ ያለው አንድነት በክርስቲያኖችም ሕይወት የሚታይ መሆኑን አስተምሮናል።

 

2. የመለኮትና የትስብእት አንድነት በጥምቀት

በናዝሬት ተፀንሶ ፤ በቤተልሔም የተወለደውና በናዝሬት ያደገው የአብ ልጅ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ፅንሰቱ በተአምር ፤ ልደቱና እድገቱ እንደ ማንኛውም የሰው ልጅ ሆኖ ለእናቱ ለቅድስት ድንግል ማርያምና ለጠባቂዋ ለጻድቁ ዮሴፍ እየታዘዘ ፤ በልጅነቱ ተአምራትን እያደረገ ማደጉን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሠክራሉ፡፡ ሠላሳ ዓመት ሲሆነው ለእስራኤል ይገለጥ ፤ ዘንድ ፤ የተቆጠረው ሱባኤና የተነገረው ትንቢትም እንዲፈጸም ራሱን ዝቅ አድርጎ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡ ‹አፍቂሮ ኪያነ መጽአ ኃቤነ ዘነቢያት ሰበኩ ለነ በዮርዳኖስ ተጠምቀ›› እንዲል። የክርስትና ሃይማኖት እውነተኝነትን ከሚያረጋግጡት መካከል ኢየሱስ ክርስቶስ ገና በማኅፀነ ማርያም ሳይፀነስ ከቅድስት ድንግል  በቤተልሔም አንደሚወለድና በዮርዳኖስ እንደሚጠመቅ አስቀድሞ በቅዱሳት መጻሕፍት መረጋገጡ ነው።

ስለዚህ ትንቢተ ነቢያት፤ የዘመናት ምኞትና የአበው ተስፋ ይፈጸም ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡ የተጠመቀው ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆኖ በተዋሕዶ ነው፡፡ የመለኮትና የትስብእት ተዋሕዶ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ድል የተነሣበትና የሰው ልጅ የከበረበት ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ የክርስቶስ በፍጹም ተዋሕዶ መገለጥ የውሉደ ጥምቀትን አንድነት ፤ በኃጢአት ወድቆ በክርስቶስ ሞት የተነሣው ሰው በአግዚአብሔር ዘንድ ያለውን ሥፍራ ያሳየበት ነው። ቅዱስ ቄርሎስ “ወረደ ከመ ያዕርገነ ለነ ኀበ ሀገሩ አርያማዊ ኀበ ሀሎ አቡሁ’ ‘የባሕርይ አባቱ ካለበት ሰማያዊ ሀገሩ ያገባን ዘንድ እርሱ ወደ እኛ ወረደ” (ሃይ.አበው) እንዳለ የሰውን ልጅ ከወደቀበት ኃጢአት ለማንሳትና ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ እርሱ ወደ ምድር ወረደ። እኛን ሆኖ እኛን ለማዳን አካላዊ ቃል ሥጋን ገንዘብ አደረገ። ከቅድስተ ቅዱሳን ፤ ከንጽሕተ ንጹሐን ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ፤ ከነፍስዋ ነፍስን ነስቶ በመወለዱ የሰው ልጅን አከበረ። “እንቲአሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ ወእንቲአሁ ለሥጋ ኮነ ለቃል ፤ የቃል ገንዘብ ለሥጋ ሆነ የሥጋ ገንዘብ ለቃል ሆነ” ብሎ ቅዱስ ቄርሎስ እንደ ተናገረ። ቅዱስ ሉቃስም “…እንዘ ዘመዱ እንከ ንሕነ ለእግዚአብሔር…እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን..” (የሐ.17:27-28) በማለት እግዚአብሔር አምላክ እኛን ከፈጠረበት ይልቅ እኛን ያዳነበት ምሥጢር እጅግ ታላቅ መሆኑን ያረጋግጥልናል።

 

3. የሕዝብና የአሕዛብ አንድነትበጥምቀት

በቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ ሕዝብ የተባሉት እስራኤል ዘሥጋ ሲሆኑ እነዚህም ሱባኤን የቆጠሩ አበው ፤ ትንቢትን የተናገሩ ነቢያትና ሕዝበ እግዚአብሔርን የመሩ ነገሥታት ከመካከላቸው የተገኙ የአብርሐም ልጆች ናቸው። አሕዛብ የተባሉትም ከዚህ ታሪክ ውጭ ሆነው በአምልኮ ባዕድ ይኖሩ የነበሩት ናቸው። ሁለቱም በጥምቀት ዳግም ተወልደው የመንግሥተ ሰማያት ዜጎች ለመሆን በቅተዋል። “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” (ዮሐ.3:3) ይላልና። በጥምቀተ ክርስቶስ የሁለቱም የዕዳ ዳብዳቤአቸው ተደምስሶላቸዋል። የሁለቱም የባርነት ታሪክ ተሽሮ በአዲስ ምዕራፍ በወልደ እግዚአብሔር በማመንና በአንዲት ጥምቀት በመጠመቅ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነዋል። “ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና” (ሮሜ.3:22) በማለት ከክርስትና በኋላ አንድነት እንጂ ልዩነት እንደሌለ አረጋግጦልናል።

በዘመነ አሪት ሕዝብና አሕዛብ የሚለዩበት ልዩ መታወቂያ “ግዝረት” ነበረ። “የቍልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል” (ዘፍ.17:11)። በዘመነ ሐዲስ ግን ግዝረትን ተክቶ ለክርስቲያኖች መለያ ፤ ለመንግሥተ ሰማያት መግቢያ መሥፈርትና የመዳን ምልክት የሆነው “ጥምቀት” ነው። “ያመነ የተጠመቀም ይድናል” (ማር.16:16) እንዲል። ጥምቀት እንደ ግዝረት የአብርሐም ዘሮችን ብቻ ከአሕዛብ የሚለይ ድምበርና በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል የቆመ የቃል ኪዳን ምልክት ሳይሆን ሕዝብና አሕዛብን አንድ መንጋ አድርጎ ለእግዚአብሔር መንግሥት የመግቢያ ብቃት ሆኖ የሚያገለግል ነው። ይኽ በጥምቀተ ክርስቶስ ያገኘነው ጥምቀተ ክርስትና ከአለም መለያችን ብቻ ሳይሆን የአንድነታችን ማሳያ “አረቦን” ነው። “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና” (ገላ.3:27) ይላል።

የእግዚአብሔር ቃል የሚያረጋግጥልን ክርስቲያን ከየትኛውም ብሔር ፤ ነገድ ፤ ቋንቋ ፤ ልማድና ሥርዓት ይምጣ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቆ የመንግሥቱ ዜጋ ከሆነ በኋላ ባለቤት እንጂ ባዕድ አይደለም። የበላይነትም ሆነ የበታችነት ሥሜት አይኖረውም። አንዱን ዝቅ ሌላውን ከፍ አድርጎ የሚያይበት አለማዊ ዓይንም የለውም። ይልቁንም ለክርስቶስ አካሉ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን አንድ ክፍል ሆኖ የተገነባ ስለ ሆነ በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካሉት ሁሉ ጋር አንድ ነው። ስለዚህ በክርስቲያኖች መካከል ሊኖር የሚገባው አንድነትና የማይፈታ ምሥጢራዊ ትስስር በጥምቀት ዳግም ተወልደን የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን ያገኘነው አምላካዊ ስጦታ እንጂ በጥቅምና በጊዜ የተገደበ ፤ በጥላቻና በፖለቲካ የሚዘወር ሕይወት አይደለም።

 

4. በክርስቶስ ሞት አንድነት በጥምቀት

ብርሃነ አሕዛብ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እኛ እኛን ሆኖ የእኛን ኃጢአት በእንጨት ላይ ተሸክሞ የእኛን ሞት ከሞተው ከክርስቶስ ሞት ጋር እንደምንተባበርና ስለ እኛ የሆነውን መከራ-መስቀል የእኛ የምናደርግበትን ምሥጢር እንዲህ ሲል ይናገራል። “ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” (ሮሜ.6:4)። ሐዋርያው በዚህ ቃል የክርስቶስን ቤዛነት ለማሳየት “ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ” (1.ጢሞ.2:6) በማለት ጥምቀትና ሞትን በምሳሌነት ተጠቅሟል። በሞትና በጥምቀት ምሳሌም ክርስቲያኖች ስለሚያገኙት ድኅነትና ሰማያዊ በረከት አስተምሮናል። ይኽን እጅግ ጠቃሚና አስገራሚ ምሳሌ በጥቂቱ ዘርዘር አድርገን እንመልከት:-

4.1  የሞቱ ምሳሌ በጥምቀት

ጥምቀት ለክርስቶስ ሞትና መቃብር ምሳሌ ሆኖ መቅረቡ ሰው ሲጠመቅ ራቱቱን ሆኖ መጠመቁና ሲሞትም ራቁቱን ሆኖ መገነዙ ነው። ሰው ያለውን ሁሉ ትቶ ራቁቱን ወደዚህ ዓለም እንደ መጣ እንዲሁ ራቁቱን ወደ አለመኖር ይመለሳል። ከእግዚአብሔር ጸጋና ክብር የተራቆተውን የሰው ልጅ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ክርስቶስ ዕርቃኑን በመስቀል ላይ ዋለ። ወደ እርሱ  ክብር ሊያገባን በእኛ ሥፍራ እኛን ተክቶ እርሱ ተገኘ። “ዘዚአነ ሞተ ነሥአ ወእንቲአሁ ሕይወተ ወሀበነ” (ውዳሴ ማርያም ዘዓርብ) እንዳለ የእኛን ሞት እርሱ ሞቶ የእርሱን ዘለዓለማዊ ሕይወት ሰጠን። ይኽን ዘለዓለማዊ ሕይወት ለማግኘት የሰው ልጅ ሁሉ ክርስቶስን በማመን ፤  አምኖ በመጠመቅ የክርስቶስን ሞት የራሱ ማድረግ ነው። “ከሞቱ ጋር መተባበር” የሚለውም ክርስቶስ የከፈለለትን መከራ-መስቀል አምኖ መቀበልና በክርስቶስ ያለውን ሕይወት ወርሶ መኖር ማለት ነው። “ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው” (ቲቶ.3:6)

4.2 የአዲስ ሕይወት ምዕራፍ በጥምቀት

ከሞት በኋላ ሌላ አዲስ ሕይወት አዲስ ዓለም አንዳለ ሁሉ ከጥምቀት በኋላ ሌላ አዲስ ሕይወት ፤ አዲስ ምዕራፍ ነው። ሐዋርያው ይኽን ሲያረጋግጥልን “እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” ይላል። መጠመቅ ዳግም መወለድ የሆነውም ለዚህ ነው። “ወለደነ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ” እንዲል። ሰው አምኖ ሲጠመቅ አሮጌው ማንነቱን ትቶ ወደ አዲስ ማንነት ስለሚመጣ አዲስ ሕይወት ነው። ጥምቀት ኃጢአትን ስለምታስተሠርይ ኃጢአተኛው ከኃጢአት እሥራት ተፈቶ አሁን እንደ ተወለደ ሕጻን አዲስ ምዕራፍ የሚጀምርበት ነው። በመሆኑም ጥምቀት አዲስ ሕይወት ፤ የለውጥ ምዕራፍ ስለ ሆነ ስንጠመቅ አዲስ ስም ፤ አዲስ ዜግነት ይሰጠናል።

4.3 የማኅበረ ምእመናን አንድነት በጥምቀት

ጥምቀት ለአንድ ምእመን በእግዚአብሔር መንግሥት ፤ በክርስትና ሕይወት የመኖር ዋስትናና ሁለንተናዊ መገለጫው ነው። የክርስቶስን ሞት የራሱ ለማድረግና በክርስቶስ ሞት ምክንያትም በአዲስ ሕይወት ለመመላለስ በክርስቶስ አምኖ መጠመቅ የግድ በማስፈለጉ “ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል” (ዮሐ.3:7) ብሎ አስተምሮናል። ጥምቀት አንድን ምእመን በክርስቶስ ሞት በመተባበር ለአዲስ ሕይወት የምታበቃ ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የመግቢያ በር ቁልፍ ስትሆን በሌላ መልኩ የማኅበረ ምእመናንም የአባልነት/የአድነት መታወቂያ ፓስፖርት ናት። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካሉ ፤ ክርስቶስም የቤተ ክርስቲያን ራስዋ ሲሆን እያንዳንዱ ምእመን የክርስቶስ አካል በሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገነባ አንዱ ክፍል ነው። ስለሆነም የተጠመቁት ሁሉ ከአንዱ መንፈስ ቅዱስ የተወለዱ በመሆናቸው የክርስቶስ ማኅበር ናቸው። “ማኅበራኒሁ ለክርስቶስ” እንዲል። ቅዱስ ዮሐንስ ስለዚህ ኅብረት ሲናገር “እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው” (ዮሐ.1:3) ይላል።

በዘመናችን ክርስቲያን ክርስቲያን ወንድሙን ሲያሳድድ ፤ የእርሱ ባልሆነው የአረማውያን ጠባይ ወገኑን አፈናቃይና ገዳይ ሆኖ መታየቱ እጅግ የሚያሳዝን ነው። በውኑ በዚህ ድርጊት የተሠማሩት ወገኖች በሃይማኖቱ ስም የሚጠሩ ወይስ በሃይማኖቱ የሚኖሩ? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ግድ ይሆናል። በሃይማኖት ስም መጠራትና ሃይማኖትን መኖር የተለያዩ ናቸውና። ሐዋርያው “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ” ይላል። የክርስትና ሃይማኖት የፍቅር ሃይማኖት እንጂ የመገፋፋት ፤ የመጠላላት ሃይማኖት አይደለም። የክርስትና ሃይማኖት መሠረቱ ክርስቶስ ፍቅር ስለሆነ የምንወደድበት ማንነት ሳይኖረን እርሱ እኛን ወዶ ወደ እኛ መጣ። ‹‹አፍቂሮ ኪያነ መጽአ ኃቤነ ዘነቢያት ሰበኩ ለነ በዮርዳኖስ ተጠምቀ›› ይላልና። በሃይማኖት የሚኖሩት ክርስቲያኖችም መታወቂያቸው ፍቅር እንደ ሆነ እርሱ ባለቤቱ አስተምሮናል። “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” (ዮሐ.13:35)።

 

2. ማንነትና እኩልነት በጥምቀት

ከጥምቀት ትሩፋት አንዱ ጥምቀት የማንነትና የእኩልነት ማረጋገጫ ማኅተም ሆኖ መሰጠቱ ነው። “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና። አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና”(ገላ.3:27-28) ይለናል። ውሉደ ጥምቀት በክርስቶስ የክርስትናን ማንነት የለበሱ የቀድሞ የዝቅታና የከፍታ ማንነታቸውን አስወግደው በእኩልነት የሚያምኑና በእኩልነት የሚያመልኩ ናቸው። አንዱ ሌላውን ባርያ ፤ ጨዋ ብሎ አያገለውም። ሁለቱም በክርስቶስ አካል ውስጥ ሥፍራ ተሰጥቶአቸው በክርስቶስ ክቡር ደም የከበሩ ስለሆኑ በእነርሱ ዘንድ የክብር ፤ የማንነት ጥያቄ አይነሳም። በክርስቶስ አካል ውስጥ ሆኖ የበታችነት ወይም የባዕድነት ሥሜት የሚሰማው ምእመንም እንዳይኖር ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም” (ኤፌ.2:19)።

ይኽን የከበረና የታወቀ የክርስትና አስተምህሮን ገንዘብ ካደረግንና በሃይማኖት የምንኖረው ከሆነ ጥላቻን ፤ ግፍን ፤ መለያየትን ከመሐላችን ልናርቅ ይገባል። በክርስትና ሕይወት “አንድነት” ሲባል አንዱን በአንዱ መጨፍለቅና መዋጥ ሳይሆን “አንድነት” ማለት የእኩልነት መብት ፤ የማንነት ክብር የሚረጋገጥበት የጋራ ዋስትና የሆነ ሰንደቅ ዓላማ ነው። ይኽን “አንድነት” የነገድ ፤ የቋንቋ ፤ የጾታ ልዩነት አይገድበውም። የተጠራነው ከተለያየ ነገድና ቋንቋ ሲሆን ማንም በማንነቱ የተለየ ብልጫ ሳይኖረው በክብር ፤ በእኩልነት የሚታይበት ማኅበረ ክርስቶስ ነው። “…..ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው..” (ራዕ.5:10) ይላልና። ክርስቲያኖች ቋንቋንና ነገድን መሠረት ባደረገ ፖለቲካ መጠፋፋት ማለት የተዋጀንበትን የክርስቶስን ክቡር ደም ከንቱ ማድረግ ማለት ነው። አኮ በወርቅ ኃላፊ ዘተሳየጠነ አላ በደሙ ክቡር ቤዘወነ ወለደነ በጥምቀቱ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ የገዛን አይደለም፥ በከበረው ደሙ አዳነን እንጂ ቅድስት ለሆነች ቤተ ክርስቲያንም አካል እንሆን ዘንድ በጥምቀቱ ወለደን እንዳለ (ቅዱስ ያሬድ፤ 1.ጴጥ.1:18)።

 

ማጠቃለያ

“ጥምቀት በተዋሕዶ” በሚል ርእስ በመጠኑ ያየነው በጥምቀተ ክርስቶስ የተገለጠውን የሥሉስ ቅዱስ ሦስትነትና አንድነት ፤ የትስብእትና የመለኮት በተዋሕዶ መገለጥ ፤ የሕዝብና የአሕዛብ አንድነት እንዲሁም ጥምቀት የክርስቶስን ሞት መሞትና በአዲስ ሕይወት መመላለስ ፤ የማንነትና የእኩልነት መብት ማረጋገጫ ማኅተም መሆኑን ነው። ጥምቀተ ክርስቶስ ወደ ተስፋ መንግሥተ ሰማያት ለምታስገባን ጥምቀተ ክርስቲያን መሠረት መሆኑንም በጥቂቱ ለመገንዘብ ሞክረናል። በአንዲት ሃይማኖት ፤ በአንዲት ጥምቀት አንድ እንሆን ዘንድ ስለ እኛ የተጠመቀው አምላክ በአንድነት ለአንድነት ጠርቶናል።

በእውነት ጸድቀን ፤ በሃይማኖትና በምግባር አብበን የጽድቅን ፍሬ እንድናፈራ ዐፀደ ወይኑ በሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተክሎናል ፤ የሕይወት ውኃ የሆነውን ቅዱስ ቃሉን እያጠጣን በዓለሙ የክፋትና የፈተና ሐሩር እንዳንጠወልግ ለዘለዓለማዊ መንግሥቱ ይጠብቀናል። ‹‹እግዚእ ክርስቶስ ለሊሁ ዘተከለነ ወሰቀየነ  በማይ መንፈሳዊ ማእከለ ተኩላት›› (ቅዱስ ዮሐንስ ፈወርቅ) እንዲል። ስለሆነም ራሳችንን ከዚህ ዓመጻና ሸንገላ ከሞላበት ዓለም ፤ መጠፋፋትን ጥበቡ ካደረገው ከዚህ ክፉ ትውልድ ለመዳን ፤ ዓለሙንም  ለማዳን እንድንችል ወልደ አብ ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን!