በመቅደላ ጦርነት ወቅት በእንግሊዝ ወታደሮች ከተዘረፉ የብራና መጻሕፍትና ልዩ ልዩ ንዋየ ቅድሳት መካከል እንደሆነ የሚገመት አንድ ጽላት እና የተለያዩ ቅርሶች በበጐ አድራጊዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የርክክብ ሥነ ሥርዓት በታላቋ ብሪታንያ ለንደን ከተማ ተከናወነ።

በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለንደን (UCL) መምህር የሆኑትና ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያና በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤክርስቲያን ጉዳይ ላይ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ጃኮፖ ግኒስኪ በመቅደላ ጦርነት ዘመን ከአገር እንደወጣ የሚገመትና በእርሳቸው እጅ የነበረ ጽላት ወደ ሀገሩና ወደ መንበረ ክብሩ እንዲመለስ ከፍተኛውን አስተዋጽዖ እንዳበረከቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን በመወከል ጽላቱን የተረከቡት የልዑካን ቡድኑ ተወካይ ቀሲስ ዶ/ር አባተ ጐበና ምስጋናቸውን በልዑካኑ ስም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል በዶምቢዶሎ ሎና በቄለም ወለጋ ልዩልዩ የልማት ሥራዎችን አከናወኑ ለችግረኛ ተማሪዎችም የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አየረጉ።

ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል የጋምቤላ፣የአስሳ፣የቄለም ወለጋና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በደምቢዶሎ ከተማ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ አገልግሎት በደምቢዶሎ ከተማ ቀበሌ03 በአርባ ቀናት ተሰርቶ የተጠናቀቀውን የቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስቲያን መስከረም 6ቀን 2016ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱን ማክበራቸውን የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ሕዝብ ግንኙነት ክፍል በላከልን ዘገባ ገልጿል።

የጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥሪ ተላለፈ።

መስከረም ፲ ቀን ፳፻፲፮ ዓ/ም
አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ ከሚያደርጋቸው የምልአተ ጉባኤ ስብሰባዎች አንዱ የሆነው የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ መሆኑ ይታወቃል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የዘንድሮው የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ከጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፲፮ ዓ/ም ጀምሮ እንደሚካሄድ በመግለጽ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ጳጳሳት ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፲፮ ዓ/ም በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ እንዲገኙ መንፈሳዊ ጥሪውን አስተላልፏል።
ከጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ በፊት ባሉት ዕለታት አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ጳጳሳት፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች፣የአህጉረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሰበካ ጉባኤያት ምክትል ሊቃነ መናብርትና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ተወካዮች በተገኙበት ይከናወናል።

በውጭ አገር ለምትገኙ አህጉረ ስብከት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተላለፈ መልዕክት

ለሁለተኛ ጊዜ በውጭ አገር ለሚገኙ አህጉረ ስብከት ጥሪ ተላልፏል።ስለሆነም በተላለፈው ጥሪ መሰረት ዝርዝራችሁ ከዚህ ደብዳቤ ጋር የተለጠፈው አህጉረ ስብከት በአስቸኳይ ሪፖርታችሁን እንድታቀርቡና በገጉባኤው ላይ እንድትሳተፉ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ
መስከረም ፲ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ


የመስቀል ደመራ በዓል የቅድመ ዝግጅት ሥራ በአምስት ማዕከላት በመከናወን ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል የቅድመ ዝግጅት ሥራውን እያከናወነ ነው።

በዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የደረሰውን ዝርፊያ በተመለከተ አሰፈላጊው ክትትል እየተደረገ ነው።

መስከረም ፮ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
*****
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
“”””””””””””””””””””
በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም በትላንትናው እለት ማንነታቸው ባልታወቁ ዘራፊዎች የደረሰበትን ዝርፊያ በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አስፈላጊውን ክትትልና ማጣራት በማድረግ ላይ የምትገኝ ሲሆን በጉዳዩ ዙሪያም ከሚመለከታቸው የመንግሥት የጸጥታ አካላት ጋር እየተነጋገረችበት ነው።

በገዳሙ በተካሔደው ዝርፊያም ከገዳሙ ጥንታዊያን ቅርሶች ጋር በተያያዘ የደረሰ ምንም ዓይነት ጉዳት የሌለ መሆኑን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ ባደረገው ማጣራት አረጋግጧል።

በገዳሙ ከዝርፊያው ጋር በተያያዘ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ ከገዳሙ፣ከሀገረ ስብከቱና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተገቢውን ማጣራት እያደረገ ሲሆን ዝርዝር ሁኔታውን በተመለከተ በቅርቡ በመገናኛ ብዙሃን የምናሳውቅ መሆኑን እየገለጽን ሕዝበ ክርስቲያኑ ከቤተክርስቲያናችን ማዕከላዊ አስተዳደር የሚሰጠውን ማብራሪያ በትዕግስት እንዲጠባበቅ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት

የቅድስት ልደታ ጤና ኮሌጅ በተከታታይ ዓመታት ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።

የቅድስት ልደታ ጤና ኮሌጅ በተከታታይ ዓመታት ያስተማራቸውን ተማሪዎች ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በተገኙበት አስመረቀ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የ፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር የዝግጅት ሥራ ግምገማ ተካሔደ ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት በ፳፻፲፭ ዓ/ም የሥራ ዓመት በነበረው የሥራና የአገልግሎት አፈጻጸም ዙሪያ አጠቃላይ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሠራተኞች በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አሥኪያጁ በብፁዕ አቡነ አብርሃም መሪነት በጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ ሠፊ ውይይት አደረጉ።

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዓውደ ዓመት ዘዕስራ ምእት ዐሠርቱ ወስድስቱ ዓመተ ምሕረት

ጳጉሜን ፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
*******
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !!

👉 በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤

👉 ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤

👉 የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤

👉በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፡፡

ዘመንን በዘመን እየተካ ፍጥረቱን የሚመግብና የሚመራ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ !

“ወኀለይኩ መዋዕለ ትካት፤ ተዘከርኩ ዓመተ ዓለም ወአንበብኩ፤ የድሮውን ዘመን አሰብሁ፤ ዓመተ ዓለምን አስታወስሁ፤ አነበብሁም” (መዝ.፸፮ ፥ ፩)፤

አዝማናትና ዓመታት የሚረሱ ሳይሆኑ ሲታወሱ የሚኖሩ እንደሆኑ ቅዱስ ዳዊት በቅዱስ ቅብእ አማካኝነት ባደረበት መንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ያስተምረናል፤ እውነት ነው ዓመታት በግድ ያለውድ መታሰባቸው አይቀርም፤ ትዝታቸውም አይጠፋም፤ ትዝታቸውም በመልካም ወይም በመጥፎ ሊሆን እንደሚችል የሚያጠራጥር አይደለም፤
አዝማናትና ዓመታት እንደ ሌላው ፍጥረተ እግዚአብሔር ሁሉ፣ ለፍጥረታት አገልግሎትን ሊሰጡ መልካም ሆነው የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በሰዎች ስሑት ተግባርና አስተሳሰብ ከመልካምነት ወደ ጎጂነት መቀየራቸው የምናስተውለው እውነት ነው፤

አዝማናት ወይም ዓመታት ሰው በሰላም አርሶና ነግዶ ላቡንም አንጠፍጥፎ፣ ጣዕመ ሕይወቱን በአግባቡ ሊመራባቸው ፈጣሪውን ሊያመልክባቸው፣ ሊማርባቸውና ዕውቀት ሊገበይባቸው፣ ሲሳሳትም ንስሐ ገብቶ ሊታረምባቸው የተሰጡ ጸጋዎች ናቸው፤ ሰው አዝማናትን በዚህ ሲጠቀምባቸው መልካም ይሆናሉ በመልካምም ይታወሳሉ፤

ነገር ግን ሰው በቂምና በበቀል፣ በጥላቻና በመናናቅ እንደዚሁም ማቆሚያ በሌለው የራስ ወዳድነት ክፉ መንፈስ ተይዞ እርስ በርስ የሚጋጭባቸው፣ እግዚአብሔርንም ቸል የሚልባቸው፣ ለሥጋዊና ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ዘላቂ የጋራ ጥቅም የማይጠቀምባቸው፣ ሁለንተና ሕይወቱን በንስሐ የማይታደስባቸው፣ በፍቅርና በሰላም የማይኖርባቸው ከሆኑ ዓመታቱ መጥፎዎች ይሆኑበታል፣ በመጥፎም ይታወሳሉ፣ ይህ እውነታ በዓለም ታሪክም ሆነ በሀገራችን ታሪክ በተደጋጋሚ መፈጸሙን በውል የምናውቀው ሓቅ ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት !

የሩቅን ዘመን ትተን ባለፉት ጥቂት አዝማናት ያየናቸው ዓመታት በመልካም ትዝታ የሚታሰቡና የሚዘከሩ እንዳልነበሩ ንጹሁ ኅሊናችን ምስክር ነው፡፡ ስሕተቶች እንዴት ተፈጥረውና አድገው ከባድ ችግር ላይ እንደጣሉንም አእምሮአችን አይስተውም፤ እንደባለ አእምሮ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አውቀን፣ አክብረንና ጠብቀን ብንመላለስ ኖሮ የሆነውን ክፉ ነገር ሁሉ ማየት አንችልም ነበር፤

ትልቁ የእግዚአብሔር ፈቃድ ከቂም ከበቀል ርቀን ስራችንን በፍቅርና በስምምነት፣ በትዕግሥትና በምክክር እንድንሰራ ነው፤ ከዚህ ወጥተን የቂምና የበቀል ቊርሾ እየመዘዝን እሱንም በመርዛም ኃይለ ቃል እያጀብን በነጐድን ጊዜ ግን ራሳችንን በራሳችን ክፉኛ ከመጉዳታችንም ሌላ የዓለም አጀንዳ ለመሆን ተገደድን፤

ይህን ክፉ ተግባር የፈጸምንባቸው ዓመታት በክፉ እንጂ በመልካም የማይታሰቡ ሆነው አልፈዋል፤ አሁንም ክፉው አስተሳሰባችንና ተግባራችን በአስተማማኝ የተቀረፈ መስሎ አይታይም፤ ከሚገርመው ነገር የችግሩን መንሥኤ ከልብ ሲያጤኑት አሁን እየተፈጸመ ላለው ጥፋት የሚመጥን የችግር ፍሬ ነገር አይገኝበትም፤ ችግር ቢኖርስ እውን በውይይት የማይፈታ ነበርን ? ተብሎ ቢጠየቅም መልስ አይገኝለትም፤

በወሰንና በርእዮተ ዓለም ምክንያት የምናደርገው ክርክርስ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን የሚለውን መርሕ በትክክል ከተገበርን የሚያከራክረው ምኑ ነው? የሀገሪቱ ሕግስ ይህንን መፍታት አይችልም ነበርን ? በወሰን ምክንያት ጠብ የሚነሣውስ መላዋ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆንዋን እየረሳን ይሆንን ? በአንድ የበላይ መሪ፣ በአንድ የሀብት ቋት የምንተዳደር የአንድ ኢትዮጵያ ልጆች አይደለንም ወይ?
ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሶ እየሰራ እንዳይኖር የከለከለ ሕግና ሥርዓትስ አለወይ ? ካለስ እሱን በምክክር ፈትቶ ስለታላቋ ኢትዮጵያ ብቻ በጋራ መቆም አይበልጥም ወይ? እውነቱ ይህ ከሆነ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተፎካካሪዎች፣ ልኂቃን፣ የስቢክ ማኅበራትና ምሁራን የሆናችሁ፣ የሆነው ሁሉ ትክክል አልነበረምና እባካችሁ ወደ ልባችሁ መለስ በሉና ምርጫችሁን ኢትዮጵያ፣ ሰላምና አንድነት ብቻ አድርጉ፤ ሌላው ሁሉ በዚሁ ስር ነው ያለው፣ በሂደትም ደረጃ በደረጃ እየተስተካከለ ይመጣል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት !

ያለፈው ዓመት ያሳረፈብንን ሁለንተናዊ ተጽዕኖ በሚገባ አስተውለን፣ ዳግም ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይሸጋገርብን ካላደረግን አዲሱ ዓመት ለኛ የሚሰጠን ትርጉም ምንድን ነው ? ባለፉት ዓመታት በሃይማኖት፣ በባህል በታሪክ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም በሕዝባችን ሥር የሰደደውን የእርስ በርስ መጠራጠር ከልብ መርምረን ወደ ድሮው እኛነታችን ካልተመለከትንስ አዲስ ዘመን እያልን ማክበራችን ምን ፋይዳ አለው? ይህንን ሁሉ በአዲሱ ዓመት በማጤን ያለፈውን ጎጂ ነገር በመተው፤ ጠቃሚውን ግን ይበልጥ በማጠናከር አዲሱን ዓመት መቀበል አለብን፤

ከሁሉ በላይ ለሀገራችንና ለሕዝባችን የሚጠቅመው ምንድነው? በሚለው በምር መስራት አለብን፤ በመለያየት፣ በመፎካከር፣ በመበቃቀል፣ በመናናቅ፣ የራስን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ በመጣር፣ ጊዜ አገኘሁ ብሎ ኃይልን በመጠቀም፣ የሕዝብን ጥቅም ማስከበርና የሀገርን አንድነት ማስቀጠል አይቻልም፤ ሀገራችንንና ሕዝባችንን ወደ ዕመቀ ዕመቅ እየከተቱ ያሉ እንደዚህ ያሉ አስተሳሰቦች ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ ከአሮጌው ዓመት ጋራ አብረው መወገድ አለባቸው፤

በአዲሱ ዓመት የሰው ሕይወትን የሚቀጥፉ የመሳሪያ አፈ ሙዞች በሙሉ ወደ መጋዝን መግባት አለባቸው፤ ችግሮችን በውይይት፣ አሊያም በሕግ እየተፈቱ የሀገርና የሕዝብ ሉዓላዊነት ነጻነትና አንድነት መረጋገጥ አለበት፤ ሀገርንና ሕዝብን ለዘለቄታው በአንድነት የሚያስቀጥሉ የሕግ የበላይነትን ማክበር፣ እኩልነትን ማረጋገጥ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ፣ የተጐዳውን መደገፍ፣ ሆድ የባሰውን ማለዘብ፣ የተጠቃውን ማጽናናት ሲቻል ነው፡፡

በአዲሱ ዓመት ይህንን ለማድረግ በቊርጥ ከተነሣን ሰላማችን ወደነበረበት ይመለሳል፡፡ ሀገራችንም በበረከት ትሞላለች፤ ስለዚህም ኢትዮጵያውያን የሆናችሁ ልጆቻችን ሁሉ ይህንን ጥሪያችንን ተቀብላችሁ የጥፋት መሳሪያችሁንም አስቀምጣችሁ ወደ ሰላም ማእድ ቀርባችሁ በወንድማማችነት መንፈስ ችግራችሁን በክብ ጠረጴዛ በውይይት በመፍታት የሀገሪቱንና የሕዝቡን አንድነት እንድታስቀጥሉ ሁሉን በሚያይ እግዚአብሔር ስም እንማጸናችኋለን፡፡

በመጨረሻም
አዲሱ ዓመት የሰላምና የፍቅር፣ የዕርቅና የይቅርታ የተፈናቀለው ወደቀየው የሚመለስበት፣ ሆድ የባሰው የሚጽናናበት፣ ፍትሕና ርትዕ የሚሰፍንበት የመሳሪያ ድምፅ የማይሰማበት ፍጹም የተግባቦት ዓመት እንዲሆንልን እየጸለይን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን ለዚህ ቅዱስ ጥሪ አዎንታዊ መልስ እንድትሰጡ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም በድጋሚ እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር አምላክ አዲሱን ዓመት የሰላምና የተግባቦት ዓመት ያድርግልን ፤

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ
ተክለ ሃይማኖት
መስከረም ፩ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም.
ዋሽንግተን ዲሲ – አሜሪካ

የመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት በ ፳፻፲፭ ዓ/ም አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት አካሄዱ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት በ፳፻፲፭ ዓ/ም የሥራ ዓመት በነበረው የሥራና የአገልግሎት አፈጻጸም ዙሪያ አጠቃላይ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሠራተኞች በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አሥኪያጁ በብፁዕ አቡነ አብርሃም መሪነት በጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ ሠፊ ውይይት አደረጉ።