ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በሀገረ ስብከታቸው የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ አጠናክረው ቀጥለዋል።

ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም
***
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የሀገረ ስብከቱና ፣የቤተመጻሕፍት ወመዘክር፣የማኅበራት ማደራጃ  መምሪያ ሊቀ ጳጳስ በአላማጣና አካባቢው የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ አገልግሎት አጠናክረው በመቀጠል ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም  በዋጃ አካባቢ በሚገኘው ደብረ ሣሌም ቦታ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ሲደርስሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በዚሁ ጊዜም በአካባቢው በነበረው በጦርነት ምክንያት በሞተ ሥጋ  ለተለዩ አሥራ አምስት ሰዎት ጸሎት አድርሰዋል።በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በሕዝበ ክርስቲያኑ አማካኝነት እየተሰራ የሚገኘውን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተዛውረው የተመለከቱት ብፁዕነታቸው ሕዝበ ክርስቲያኑ  በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ  ችግቹን ችሎና ታግሶ ይህን የመሰለ ሕንጻ ቤተክርስቲያን መስራቱ ከሰማዕትነት የሚያስቆጥረው መሆኑን ገልጸው ለሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ማሰሪያ አንድ መቶ ሺህ ብር በመለገስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል።በዚሁ ጊዜም ሕዝበ ክርስቲያኑ አንድነቱን አጽንቶ የቅዱስ ሲኖዶስን መመሪያ ጠብቆና አክብሮ በመገኘቱ አመስግነዋል።

በመቀጠልም አዲስ ወደ ተሰራው አየር ማረፊያ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የተጓዙት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የዋዜማ ሥርዓተ ቡራኬ በማድረግ የማጽናኛ ትምህርት የሰጡ ሲሆን በማግስቱ ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱን በማክበር ትምህርተ ወንጌልና ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል።በዚሁ ጊዜ ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክትም ሕዝበ ክርስቲያኑ በጦርነት ውስጥ ሆኖ ይህንን የመሰለ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ሰርቶ ማስመረቁ ከሰማዕትነት በላይ መሆኑን አይተናል አድንቀናልም ብለዋል።

በዚሁ ጊዜም የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴውና ምዕመናኑ የብር መስቀል ለብፁዕነታቸው አበርክተውላቸዋል።
ብፁዕነታቸውም የሃያ ሺህ ብር የበረከት ስጦታ አበርክተዋል።በመጨረሻም በብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።

ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በዚህ መልኩ የቀጠሉት ብፁዕነታቸው ዛሬ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ ኮረም ከተማ የተጓዙ ሲሆን ግራት ካህሱን አለፍ እንዳሉ ከአምስት መቶ በላይ በሚሆኑ መኪናዎችና ባጃጆች እንዲሁም በእግር ጭምር በመሆን ሕዝበ ክርስቲያኑ በተለይም ደግሞ ወጣቶች በነቂስ ወጥተው ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ብፁዕነታቸውም የኮረም ከተማን ተዛውረው ከባረኩ በኋላ በኮረም  ቅድስት ማርያም  ቤተክርስቲያን ኪዳን አድርሰዋል።በአውደ ምህረቱም ሦስት ሊቃውንት ቅኔ አበርክተውላቸዋል፤ካህናቱና ምዕመናንም በወረብ፣ በዝማሬና በእልልታ በአክብሮት ተቀብለዋቸዋል።
ብፁዕነታቸውም ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋናቸውን በማቅረብ ችግሮቹ ተወግደው ተወልደው ባደጉበት አገር ከሚወዳቸውና ከሚያከብራቸው ሕዝባቸው ጋር ለመገናኘት በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ እግዚአብሔርን አመስግነዋል ።

በዚሁ ጊዜም ብፁዕነታቸው “ምንም እንኳን በሞት ጥላ ብሆንም አንተ ከእኔ ጋር ነህና አልፈራም”በሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል መነሻነት ሰፊ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል።በጦርነቱ ለሞቱ ወገኖችም ጸሎት ያደረጉት ብፁዕነታቸው  አዲስ ለሚታነጸው የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያንም የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል።ለሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ግንባታ የሚውል የአንድ መቶ ሺህ ብር ስጦታ ያበረከቱት በብፁዕነታቸው ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ቤተክርስቲያን አንዲት ስለሆነች የቤተክርስቲያናሁን አንድነት እንደጠበቃችሁና የቅዱስ ሲኖዶስን ድምጽ በአንድነት እንደቆማችሁ ሁሉ አሁንም ይህንኑ ተግባራችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ አደራ እላለሁ ብለዋል።

በመጨረሻም ሁተሰበሰበው ሕዝበ ክርስቲያን ቃለ በረከትና ቃለ ምዕዳን በመስጠት የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ህኖ ብፁዕነታቸው ወደ መንበረ ጵጵስናቸው አቅንተዋል።

ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል የጥምቀት በዓልን ለማክበር ጋምቤላ ገቡ፤ከአሥር ሚሊየን ብር በላይ ንዋያተ ቅዱሳን ይዘው ተጉዘዋል።

ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል የጋምቤላ ፣ የቄለም ወለጋ፣ የአሶሳ እና የደቡብ ሱዳን አሁጉረ ስቅከት ሊቀ ጳጳስ የጋምቤላ ክልልና የቤንሻንጉል ጉምዝ አሶሳ አህጉረ ስብከት የኃማኖት ተቋማት ሰብሳቢና የልማትና የሰላም አምባሳደር ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ተነስተው በመኪና ጉዞ በማድረግ ከ10,000,000 ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ልዩ ልዩ ንዋተ ቅድሳትን በመያዝ ወለጋ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን እየባረኩና የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን በማስከፈትና የንዋተ ቅድሳት ድጋፍ በመድረግ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም ጋምቤላ ገብተዋል ።

ቅዱስ ፓትርያርኩ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ለሚያስገነባው ባለ ሰባት ወለል ሕንጻ የመሠረት ደንጊያ አስቀመጡ።

በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት እና የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሚመራው ፣የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የካህናት ማሰልጠኛ ሆኖ ከዘመናዊ ትምህርት ቤት እስከመንፈሳዊ ኮሌጅና ኃላም ከፍተኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነገረ መለኮት ወይም ቲዎሎጂ ትምህርት ማስተማሪያ ፣የጥናትና ምርምር ማዕከል ሆኖ ለ60 ዓመታት ያህል መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠቱ ይታወቃል።

የደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያምና ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ካቴድራል በ22 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው የእንጀራ ማምረቻ በቅዱስ ፓትርያርኩ ተመረቀ።

የእንጀራ ማምረቻው በሒደት ከስድስት ሺህ እስከ አስር ሺህ እንጀራ የሚያመርት መሆኑ ተገልጽዋል።

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ፣ የቤተ መጻሕፍት ወመዘክርና የማኅበራት ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ አላማጣ ከተማ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።

ጥር ፬ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
****
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
——————-

ከሦስት ዓመታት በፊት የቋሚ ሲኖዶስ ተረኛ መሆናቸውን ተከትሎ ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት የመጡት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በአዲስ አበባ ለመቆየት በመገደዳቸው ወደ ሀገረ ስብከታቸው ሳይሔዱ መቆየታቸው ይታወሳል።

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላም በአካባቢው ያለው ችግር ከመሰረቱ ባለመፈታቱ ምክንያት በራያና አካባቢው የሚገኙ ኦርቶዶክሳዊያን ምዕመናን የሚባርካቸው፣ የሚያስተምራቸውና የሚያጽናናቸው አባት ማጣታቸውን ተከትሎ ለቅዱስ ሲኖዶስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በአባትነት ተመድበው እንዲመጡላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በጊዜያዊነት የራያና አካባቢው  ስድስቱ ወረዳዎች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ እንዲመሩት የሰጠውን ውሳኔ ተከትሎ ጽሕፈት ቤቱ ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩና በ42ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሪፖርት ማቅረቡም ይታወቃል።

ይህን ተከትሎ ጽሕፈት ቤቱን በማቋቋም፣ በማደራጀትና ሰራተኞችን በመመደብ በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውኑ የቆዩት ብፁዕነታቸው ጥር 3 ቀን 2016 ዓ/ም. የጥምቀት በዓልን ለማክበር፤ በጦርነትና በድርቅ የተጎዳውን ሕዝበ ክርስቲያንም ለማጽናናት  አላማጣ ከተማ ገብተዋል።

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ  አላማጣ ከተማ ከመግባታቸው በፊት በቅርበት በምትገኘው ቆቦ ከተማ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ምዕመናንና ምዕመናት በአይሱዙ መኪናዎች፣ በቤት መከናዎች፣ በባጃጃጅና በእግር በማጀብ ደማቅ፣ ናፍቆት የተሞላበት፣ ጥልቅ የአባት ፍቅር የታየበትና በዓይነቱ ልዩና ደማቅ አቀባበል። አድርገውላቸዋል።

በአላማጣ ከተማ በሚገኘው ጥንታዊውና ታሪካዊው አላማጣ ደብረ መድኃኒት መድኀኔዓለም ካቴድራል በተደረገላቸው ደማቅ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ በአላማጣና አካባቢው የስድስቱ ወረዳ ቤተክህነት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ሥዩማን ሀብቱ አየነው የእንኳን ደህና መጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተገኙ በብዙ መቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ምዕመናንና ምዕመናት “እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋም።” በሚል ርዕስ  ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ልዑል እግዚአብሔር እንኳን በሰላምና በጤና አገናኘን ካሉ በኋላ ከሦስት ዓመታት በፊት ለቋሚ ሲኖዶስ አገልግሎት ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት በተጓዝኩበት ወቅት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት መንገድ በመዘጋቱ አገልግሎቴን አጠናቅቄ ወደ አገሬ መመለሾ ባለመቻሌ በዚያው ለመቆየት ተገድጃለሁ ብለዋል። ልጆቼ ስትራቡ፣ ስትጠሙ፣ ስትታረዙ፣ ስትሰቃዩና ስትሰደዱ አብሬአችሁ ባለመሆኔ እጅጉን ሳዝን፣ ሳለቅስና ወደ ፈጣሪዬ ሳለቅስ ከርሜአለሁ። ያለፉትን ሦስት ዓመታትም በጾም፣ በጸሎትና በናፍቆት በመቆየት ዳግም የምንገናኝበትን ጊዜ ስናፍቅ ከርሜአለሁ ብለዋል።

በአላማጣና አካባቢው በአጠቃላይም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በሞተ ሥጋ የተለዩንን አባቶችካህናት፣ ዲያቆናት፣ ወንድሞችና እህቶችን ልዑል እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ከደጋጎቹ አባቶቻችን ጎን ያኑርልን ካሉ በኋላ ላደረጋችሁልኝ ታሪካዊና ደማቅ አቀባበል ልባዊ ምስጋናዬን እያቀረብኩ ለወደፊቱ በእምነታችሁ ጸንታችሁ፣ አንድነታችሁን አጽንታችሁ እንድትኖሩ አባታዊ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፤ በማለት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተው የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።

በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የአቀባበል ሥነሥርዓት ዙሪያ ዝርዝር መረጃዎችን ለማድረስ በአካባቢው ኢንተርኔት ባለመኖሩ ምክንያት በፎቶግራፍ የተደገፈ መረጃ ለማድረስ ባንችልም ለወደፊቱ የተጠናከረ መረጃ ስናገኝ መረጃውን የምናደርስ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን።

የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የጥምቀት በዓል ጥንታዊ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ ሁኔታ ሰላማዊና ደማቅ በሆነ መልኩ እንዲከበር ሁሉም ወገን በኃላፊነት መንፈስ እንዲሠራ ብፁዕ አቡነ  አብርሃም አሳሰቡ።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሼል አስኪያጅ፣ የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓልን በማስመልከት “ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም” (መዝሙር ፴፬፥፲፫) የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ኀይለ ቃል መነሻ በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት የጥምቀት በዓል ጥንታዊና ሃይማኖታዊ መሰረቱን በጠበቀ መልኩ ሰላማዊ በሆነና በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ በኃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባው ገልጸዋል።

የብፁእ አቡነ ጴጥሮስ ሐዋርያዊ ጉዞ በቤተ ክርስቲያን ሕግ እና ሥርዓት መሠረት የተፈቀደ ነው።

ጥር ፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
*****
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””

ብፁእ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የኔዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ወደ ሀገረ ስብከታቸው የጥምቀትን በዓል ለማክበር መጓዛቸው ይታወቃል። ጉዟቸውን በተመለከተ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተናፈሰ ያለው ወሬ እጅግ የተሳሳተ ሲሆን የብፁእነታቸው ሐዋርያዊ ጉዞ በቤተ ክርስቲያን ሕግ እና ሥርዓት መሠረት በቋሚ ሲኖዶስ የተወሰነ እና በቅዱስ ፓትርያርኩ የተፈቀደ መሆኑን የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አስታውቋል።

የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤቱት እንደገለጸው ብፁእነታቸው ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ እና መደበኛ የጽ/ቤት ሥራቸውን እንደሚመሩ አሳውቋል።

የ2016 ዓ.ም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት የቅዱስ ፓትርያርኩ የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር በጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ ተከናወነ።

ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም ፣ አዲስአበባ -ኢትዮጵያ

የሰላማችን ሰንደቅ ዓላማ የሆነው ወልድ ወይም ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ተወለደልን

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ልደቱ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወስድስቱ ዓመተ ምሕረት፡፡