መጋቢት ፲፭ ቀን ፳፻፲፮ ዓ/ም አዲስ አበባ።

ረጅሙን የሕይወት ዘመናቸውን ቤተክርስቲያንን በሀገር ውስጥና በሰሜን አሜሪካ በቅንነትና በትህና ሲያገለግሉ የኖሩት የመልአከ ፀሐይ መኰንን ደስታ ጸሎተ ፍትሐትና ሽኝት ከልጅነት እስከ ዕውቀት ባገለገሉበት በአዲስ አበባ ገነተ ኢየሱስ ገነተ ማርያም ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።

ክቡር መልአከ ፀሐይ መኰንን ደስታ ቤተክርስቲያናችንን በምልአት ለማገልገል ራሳቸውን በዘመናዊ እና መንፈሳዊ ትምህርት ያዘጋጁና የሁሉ ወዳጅ ሆነው በስብከት፣ በማኅሌት በቅዳሴና በኖላዊነት ሲያገለግሉ የኖሩ ቅን የቤተክርስቲያን አገልጋይ ነበሩ።

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተለያዩ ካቴድራሎች በስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊነት እንዲሁም በሰሜን አሜሪካ ሲያትልና ስፖኬን በቀዳሽ ካህንነትና በደብር አስተዳዳሪነት አገልግለዋል።

ክቡር መልአከ ፀሐይ መኰንን ደስታ በሁሉም ዘንድ የሚወደዱ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ዳግም ሲከፈት ተምረው በክብር ከተመረቁ የመጀመሪያ ደቀመዛሙርት አንዱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን አጠናቀው የተመረቁና በዚህም በቅንነት ያገለገሉ አባት ነበሩ።
ክቡር መልአከ ፀሐይ መኰንን ደስታ ባደረባቸው ሕመም በሀገረ አሜሪካ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በእግዚአብሔር ጥሪ መጋቢት ፭ ቀን ፳፻፲፮ አርፈዋል።

ክቡር መልአከ ፀሐይ መኰንን ደስታ ሽኝትና ጸሎተ ፍትሐት ላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የመምሪያና የድርጅቶች ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ከልጅነት እስከ ዕውቀት ባገለገሉበት በአዲስ አበባ ገነተ ኢየሱስ ገነተ ማርያም ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።