‹‹ብዙዎች በጉጉት ሲጠብቋት የነበረች ይህች
ዕለት እግዚአብሔር የመረጣት ታላቅ ቀን ናት››
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በወለቴ ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን የምረቃ በዓል

ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

በቅድስት ሥላሴ ዓመታዊ ክብረ በዓል፤ የወለቴ ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤቱ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል ። ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ በ1000 ሺ ካሬ መሬት ያረፈና በአዲስ መልክ የተገነባ ግዙፍና ዘመናዊ ሕንጻ ነው።

በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተሰማቸውን ታላቅ ደስታና ምሥጋና ገልጸዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ‹‹ብዙዎች በጉጉት ሲጠብቆት የነበረች ይህቺ እግዚአብሔር የመረጣት ቀን ናት›› ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ።

ብፁዕ አቡነ እንጦንስ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በበኩላቸው ‹‹ቃሉ እንደሚያዘን የእግዚአብሔር ማደሪያ ለመሆን ክርስቲያናዊ ምግባር በመተግበር ከየትኛውም እኩይ ተግባር፣ ኃጢአትና በደል ተጠብቀን በቅድስና ሕይወት መኖር ይጠበቅብናል›› ሲሉ አስተምረዋል ። አያይዘውም ሐምሌ 7 ቀን የሚከበረውን ሥሉስ ቅዱስ ወደ አብርሃም ቤት የገቡበትን ቀን የሚያስታውስ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ የቤተ መድቅሱን ሕንጻ አሠራርና አፈጻጸም የሚያሳይ አጠቃላይ ሪፖርት በኢንጅነር ሳሙኤል ሀብቴ ቀርቧል። በሪፖርቱ ላይ የካቲት 01 ቀን 2005 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመሠረት ድጓጋይ መቀመጡና፣ በወቅቱ ብፁዕነታቸው ሦስት ዘመናዊ የሕንጻ ዲዛይኖችን ከውጪ ሀገር አስመጥተው ለውሳኔ ቀርቦ፣ አሁን በተሰራው ዲዛይን ላይ ነጭ ርግብ መጥታ እንዳረፈችበት በመጥቀስ የአመሠራጥ ሂደቱ በዝርዝር ተገልጿል ።

በማስከተልም በሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ግንባታ በገንዘብ፣ በዕውቀትና በጉልበት በማገዝ ሰፊ ድርሻ ለነበራቸው የኮሚቴ አባላትና ምዕመናን የምስጋና ሥጦታ ተበርክቶላቸዋል ።

በመጨረሻም :- ብፁዕ አቡነ መልከጼድቅ በሰንሰለታማ ተራራሮች ላይ ተከቦ የሚገኘው የወለቴ ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ለአከባቢው ግርማ ሞገስ ሁኖ የሚታይ ነው ሲሉ ደስታቸውን ገልጸው፤ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተው መርሐግብሩ ተጠናቋል።