ነሐሴ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በቡግና ወረዳ ቋሮና ብርኮ ቀበሌዎች እንዲሁም በዓይና ከተማ በድርቅ ለተጎዱ 2124 ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ኮሚሽኑ ከ13 ሚሊዮን 262 ሽህ ብር በላይ ወጭ በማድረግ በሦስቱ ቀበሌዎች ለሦስት ወራት የሚሆን ከ955 ኩንታል በላይ የስንዴ ዱቄት፣ ከ95 ኩንታል በላይ የምስር ክክና 3186 ሊትር የምግብ ዘይት ድጋፍ አድርጓል፡፡

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የእለት ደራሽ የምግብ ድጋፍ በማድረግ የጀመረውን ሰብዓዊ ድጋፍ በሌሎች ማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች እስከ ታኅሣሥ ወር 2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚቀጥል የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ኃይለማርያም በለጠ ተናግረዋል።

በውሃ ተቋማት ግንባታ፣ በሥነ ንጽሕና አጠባበቅ፣ በሴቶችና ሕጻናት ሥነ-ልቡና ግንባታና ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው መድኃኒት በማቅረብ፣ የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላትና የማኅበረሰብ ውይይት በቀጣይ ወራት ይከናወናሉ ብለዋል አስተባባሪው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በሰሜን ወሎ ዞን በተለይ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎችን በማከናወን በርካቶች ወገኖችን ተጠቃሚ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

መረጃው የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ነው።