በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
“ሰላምየ አኀድግ ለክሙ ወሰላመ አቡየ እሁበክሙ፡- ሰላሜን እተውላችኋለሁ፥ የአባቴ ሰላምም እሰጣችኋለሁ” (ዮሐ.14፡27)
ሀገራዊ ሰላምን፣ መረጋጋትንና አንድነት ማስፈንን አስመልክቶ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ በተላለፈው ውሳኔ መሠረት ከቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፤
ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና ደኅንነት የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ቀዳሚ ተልእኮዎች ናቸው፡፡ በሃገራችን ሰላምን ለማስፈን ቅድስት እናት ቤተ ክርስቲያን ከቀድሞ ጀምሮ ብዙ ጥረት ስታደርግ ኑራለች፡፡ አሁንም ሊኖራት የሚገባውን ተግባራዊ ሚና መወጣት ይኖርባታል፡፡
በተለይም ሰላም በመንፈሳዊ፣ በማኅበራዊ፣ በግለሰብ፣ በተቋም፣ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ክበብ ውስጥ ያለውን የተሣሠረ ሁለንተናዊ ትርጉም ከግምት ውስጥ ያስገባ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡
ለሰላም መደፍረስና መታጣት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በማንሳትና ያስከተሉትን የሰው ልጅ እልቂት፣ ሞትና ስደት፣ የአብያተ ክርስቲያናትና የመንፈሳዊ ቅርሶች ውድመት፣ የካህናትና የሊቃውንት ስደትና መከራ፣ የቋሚና የተንቀሳቃሽ ንብረቶች ውድመት፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነት መናጋት፣ በዜጎች መካከል ጥላቻ መስፋት፣ መተማመን መጥፋት፣ የኑሮ ዋስትና ማጣት፣ በስጋት መኖር፣ የማያባራ መከፋፈል፣ የሰብአዊ ክብር ማጣት፣ የመብት ጥሰት፣ የኑሮ ውድነትና የሕዝቦች መፈናቀል በአደባባይ እየታዩ ያሉ ሰብኣዊ ሰቆቃዎች ናቸው፡፡
“ብፁዓን ገባርያነ ሰላም እስመ እሙንቱ ውሉደ እግዚአብሔር ይሰመዩ፡- የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” (ማቴ.5፡9) በማለት ጌታችን ያስተማረው ትምህርት የቤተ ክርስቲያን መመርያ ነው፡፡
የቤተ ክርስቲያን የሰላምና የአስታራቂነት ድርሻ፣ የሃገር አንድነትና የሕዝብን ሰላም ለመጠበቅ በታሪኳ ያደረገችው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡
የቤተ ክርስቲያን ታላቅነት፣ የአበውን ተቀባይነትና የሊቃውንቷን ሰላምን የማስፈን ክሂሎት፣ ችግርን የመፍታት ጥበብ አሁንም ተጠናክሮ መተግበር ይኖርበታል፡፡
የሰላምን ወሳኝ ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባትና ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የሰላምና የዕርቅ ሰነድ በማዘጋጀት የመሪነት ተሳትፎ እንድትፈጽም ገለልተኛና ሰውን ማእከል በማድረግ ታገለግላለች፡፡
ካህናትና መላው አገልጋዮች የሰላም ልዑካን እንዲሆኑ፤ ሰላምን ግንባር ቀደም ሐዋርያዊ ተልእኮዋ አድርጋ ትንቀሳቀሳለች፡፡
በሃገራዊ የሰላምና የዕርቅ ጥረቶች አዎንታዊ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚያስችል ይፋዊ ውክልና እንዲኖራት፣ በሥነ ምግባርና በግብረ ገብነት ትምህርት የራስዋን ኃላፊነት እንድትወጣ፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሃገራዊም ሆነ በራስዋ መዋቅር በሰላም ዙርያ አስተዋጽኦዋን ለማሳደግና የሚጠበቅባትን ለመወጣት ትችል ዘንድ የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሚገባ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ለቤተ ክርስቲያን መመርያዋ ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርን አጥብቀህ ተከተል ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ያዘዘው መመሪያ ነው፡፡ (፪ኛ ጢሞ. ፪፡ ፳፪)
ሰላምን ሳታዳላ በሩቅም በቅርብም ላሉት ትሰብካለች፡፡
• “ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ” እንዲል (ኤፌ.፪፡፲፯)፡፡
ለቤተ ክርስቲያን ሰላም መሣርያዋ፣ ሕይወቷ፣ ጸሎቷ፣ ቀኖናዋና ዶግማዋ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ “ሰላም ከሌላችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የለም” በማለት የሰው ልጅ ሰላማዊ እንዲሆን ታስተምራለች፡፡
ጥላቻን አጥብቃ ትቃወማለች፡፡ “ጥልን በመስቀሉ ገደለ” የሚለውን መልእክት እንደ ሰንደቅ የምትጠቀምበት መለያዋ ነው፡፡ ስለዚህ በሰዎች መካከል የተከሰተውን ጥላቻ በተሰጣት መንፈሳዊ ጥበብ ማስወገድ ተልእኮዋ ነው፡፡
በሰላም ግንባታ ኢትዮጵያውያንን ያለ ልዩነት በማሳተፍ ቤተ ክርስቲያን የሰላም ሚናዋን በጥበብና በማስተዋል በቋሚነት ትሠራለች፡፡
ሰላምን ያሳጡን ጦርነቶችና ግጭቶች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙና በአጭሩ እንዲቋጩ ጥሪዋን ታስተላልፋለች፤ እምቢ ባዮችንም በማውገዝ ዘላቂ መፍትሔ የሚገኝባቸውን ሂደቶችን ትቅይሳለች፡፡
የሰላም ሰነዶችን በማዘጋጀት አስቸኳይ የሆነ ሃገራዊ የሰላም ንቅናቄ በፍጥነት እንዲጀመርና በዚህም ውስጥ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ሥልት ተቀይሶ ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረግ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡
ቤተ ክርስቲያን የራስዋ የሰላም ከፍተኛ ልዑክ ኖሯት በመዋቅሯ ሁሉ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ የሰላም ሥምሪት ለማድረግ የሚያስችል ንቅናቄ ታደርጋለች፡፡
በሃገራዊ የሰላም ጥረቶች፣ የውይይትና የምክክር መድረኮች ባለድርሻ እንድንሆን ከሚመለከተው ጋር ተቀራርቦ መሥራት የሚቻልበትን አሠራር ትዘረጋለች፡፡
በማኅበራዊ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የቤተ ክርስቲያን የሰላም ጥሪ ተቀባይነት እንዲኖረው በትጋት ትሠራለች፡፡
በሰብአዊ ድጋፍና በእርዳታ ማስተባበር ለወገኖቻችን መድረስ እንዲቻል ልጆቿን አስተባብራ ትንቀሳቀሳለች፡፡
በመግቢያችን እንደተጠቀሰው “ፈኑ እዴከ አንሥእ ኃይለከ” ብለው የለመኑ ነቢያትን የሰማ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታችንን እንደሚሰማን ከልባችን በማመን በእርሱ ያለንን ትምክህታችን ይህ በመሆኑ ከጽኑ ተስፋና ፍቅር ጋር እንድንፈጽመው አደራ እንላለን፡፡
በተጨማሪ ይህንን መንፈሳዊ ሥርዓትና መደበኛ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ሁሉም በቅንነት እንዲረዳው በጥብቅ እናሳስባለን፡፡
ዓለማውያን ምሁራን ሃገሮቻቸውን ለመጠበቅ፣ የሕዝባቸውን አንድነት ለማስቀጠል፣ የተረጋጋና እርስ በርሱ የሚተማመን ማኅበረሰብን ለማጽናት በሕግ የሚያስቀጡ “የጥላቻ ንግግርን” የሚያስቀር አዋጅ ያወጣሉ፡፡ ሃገራችንም የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃን የሚከለክል አዋጅ አላት፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ጥላቻንና ሐሰተኛ ትርክቶችን ታወግዛለች፡፡
የአሁኑ ጸሎተ ምኅላ የሚደረገው አለመግባባት በምክክር፣ በውይይት፣ በመደማመጥ እንዲፈታ፤ መከራን በመረዳዳት እንድንሻገር፣ እንደየ ኃላፊነታችን የሚጠበቅብንን ለመወጣትና የሕዝባችንን ጥያቄ ለመመለስ እንድንችል፣ ችግራችን ሁሉ ተፈትቶ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ከሃሊው አምላክ እንዲያግዘን በአንድነት ለመጮኽ ነው፡፡
ስለዚህ ይህ ዓላማው መንፈሳዊ ብቻ የሆነ የጾም፣ የጸሎትና የምኅላ አዋጅ መሆኑን ተረድታችሁ የሚድያ፣ የትምህርትና የፍትሕ፣ መሰል ተቋማት በሚያስፈልገው ሁሉ እንድትተባበሩን በዚሁ አጋጣሚ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም አባታዊ ማሳሰቢያን እናቀርባለን፡፡
በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን በታሪክም ሆነ በትውልድ የሚያኮራ ውጤታማ ሥራን እንድትሠራና ከቃል ወደ ተግባር እንድትሸጋገር ለማድረግ ይህ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሕዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
አፈጻጸም ፦
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
ሀገራዊ ሰላምን፣ መረጋጋትንና አንድነትን ለማስፈን የታወጀውን የጾምና የጸሎተ ምኅላው አፈጻጸም በቅደሱ ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት ከዚህ በመቀጠል አቀርባለሁ፡፡
ቀደም ሲል ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በመላው ዓለም ለሚገኙ ሕዝበ ክርስቲያን የታወጀውን አዋጅ አስተላልፈዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ያለፈውን በይቅርታና በምህረት ዘግተን በእውነተኛ ንሥሓ ልቅሶና በምህላ፣ በጾምና በጸሎት ወደ ፈጣሪ እንድንቀርብ፣ በመካከላችንም ፍቅርና አንድነት እንዲመጣ ይኽንን ጾመ ነቢያት ወይም የገና ጾም በልዩ ሁኔታ እንድንጾም መንፈሳዊ አዋጅ ተላልፏል፡፡
ይኽ ጥንታዊ የአዋጅ ጾም ሁለት አበይት ታሪኮችን የያዘ ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል ቅዱስ አብርሃም ሶርያዊ የተባለ ጻድቅ አባት በጸሎት፣ በጾምና በምኅላ ተራራን ከመሬት ከፍ በማድረጉ ኃይለ ጸሎቱና ክብረ አምለኩ የሚዘከርበት ነው፡፡ በሁለተኛው ክፍል ነቢያት የጌታችንን ሰው መሆን እያፈለጉ፣ ድህነትንና ሰላምን በመሻት መጾማቸው ይዘከራል፡፡ (፩ኛ ጴጥ ፩፡፲) እኛም ይኽንን አብነት አድርገን ታላቋ ቤተ ክርስቲያን፣ ኃላፊነቷን እንድትወጣ ስለችግራችን፣ ስለሀገር ሰላምና ስለ ሕዝቡ ደኅንነት በአንድነት ሆነን ወደፈጣሪያች እንድንጮኽ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጥቅምት ወር ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም ወስኖ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ሀገራችን እንድትፈወስ፣ የወገን በወገን ደም መፋሰስ እንዲቀር፣ ያለፈውን በይቅርታና በንሥሓ ዘግቶ ለወደፊቱ ብሩህ ዘመንን እንዲመጣ በንሥሓና በፍጹም ለቅሶ፣ በቁመትና በሰጊድ፣ በሰፊሕና በአንቅአድዎ፣ ወደፈጣሪ እንድንቀርብ የምልኣተ ጉባኤውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ ቋሚ ሲኖዶስ በኅዳር ወር ፳፻፲ወ፮ዓ/ም የሚከተለውን ዝርዝር አፈጻጸም አውጥቷል፡፡
፩ኛ. የጾሙ የመጀመሪያ ሳምንት ከቅዳሜ ኅዳር ፲፭ እስከ ኅዳር ፳፩ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም በሁሉም የሀገራችን ክፍልና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባለችበት በመላው ዓለም የንሥሓ፣ የጾም፣ የጸሎትና የምኅላ ሳምንት እንዲሆን፤
፪ኛ. በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ በአጥቢያ አለቆችና በገዳም አበምኔቶች መሪነት ሁሉም ዲያቆናት፣ ቀሳውስት፣ መነኰሳት፣ ሰባክያንና ሊቃውንት በሙሉ በየመዐርጋቸው ልብሰ ተክህኖና ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት ዩኒፎርማቸው ለብሰው፣ ሁሉም ምእመናን ጋር በአንድነት በዐውደ ምህረት ጸሎተ ምኅላውን እንዲያደርሱ፤
፫ኛ. በላው ሕዝበ ክርስቲያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ እናቶች አባቶች አረጋውያን ሁሉ የቻለ በቤተ ክርስቲያን፣ ያልቻለ በያለበት ሆኖ የተጣላ ታርቆ፣ በፍቅርና በአንድነት፣ በእውነተኛ ንሥሓና ጸጸት በምኅላው እንዲሳተፍ፤ በማእከል የሚደረገው ጸሎተ ምኅላ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ገዳም ሆኖ በመገናኛ ብዙኀን የቀጥታ ሥርጭት ለመላው ዓለም እንዲተላለፍ፤
፬ኛ. በመጀመሪያው የሱባኤ ቀን ኅዳር ፲፭ ቀንና፣ በሰባተኛው ቀን ኅዳር ፳፩ ቀን በጸሎተ ምኅላው በሚደረግበት ጊዜ ታቦቱ ከመንበሩ ተነሥቶ በዐውደ ምኅረት በቀሳውስት እንዲከብር ሆኖ፤ በሁሉም የምኅላው ቀናት ሥዕለ ማርያም፣ ወንጌልና መስቀል ወጥቶ በአራቱ መዐዝን ሥርዓተ ጸሎተ ምኅላው ከጸሎተ ወንጌል ጋር በየቀኑ በነግህና በሠርክ የሥራ ሰዓትን በማይነካ ሁኔታ እንዲፈጸም፤
፭ኛ. በየዕለቱ የሚነበቡት የወንጌል ክፍሎችን ስለ ሰላም፣ ስለንሥሓና ጸጸት፣ ስለ ፍቅርና አንድነት፣ ስለ በጎነትና መደማመጥ፣ ስለመሰማማትና ጥላቻን ስለማራቅ እንዲሆን፤
፮ኛ. በሰፊህና በአንቀዓድዎ፣ በሰጊድና በአስተብርኮ፣ ምኅላው ከደረሰና፣ ጸሎተ ወንጌል ደርሶ ዕለቱ ወንጌል ከተነበበ በኋላ በአንድነት የንሥሓ መዝሙር በመዘመር፣ ሕዝበ ክርስቲያን ስለሀገራቸውና ስለሰው ልጆ ደኅንነት እያሰቡ ወደቤታቸው እንዲሄዱ፤
፯ኛ. ከመጀመሪው ሳምንት በኋላ እስከ በዓለ ልደት ድረስ የሰርክ ምህላ ሳይቋረጥ መደበኛው ሥርዓተ ጾምና ጸሎት እንዲቀጥል፣ የቤተ ክርስቲያንን ታላቅነት፣ የአበውን ተቀባይነት በሚገለጽ፣ በቀጣይም ሁሉም ኦርቶዶክሳውያን በመንፈሳዊ ጽናት የሰላም ልዑካን ሆነው እንዲቀጥሉ በሚያደርግ ሁኔታ እንዲፈጸም፤
፰ኛ. አስቀድሞ የደረሰውንና፣ እየደረሰብን ያለው ችግር የጦርነትና የግጭት ብቻ ሳይሆን የረሀብ፣ የድርቅ፣ የኑሮ ውድነት፣ የመፈናቀልና የስደት ጭምር ስለሆነ ከጸሎትና ምኅላችን ጎን ለጎን መረዳዳትና መተዛዘን፣ ርኅራሄና መደጋገፍ አብሮ እንዲፈጸም፤
፱ኛ. ይኽንኑ መልእክት መላው ዓለም እንዲውቀው፣ በተለይም የኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በጸሎት እንዲያስቡን፣ የጸሎታችንና የምኅላችን መነሻ ምክንያቱ የሀገራችን ወቅታዊ ችግር ቢሆንም የምንጸልየው ለመላው ዓለም መሆኑ ተገልጾ በደብዳቤ እንዲላክ እንዲደረግ፣ በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ ጥብቅ መመሪያ አስተላልፏል፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን በእንባና በንሥሓ የምናቀርበውን ጸሎተ ምኅላችንን በምህረቱ ተቀብሎ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን፣ ሕዝባችንን ይጠብቅልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ
ኅዳር ፲፩ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም፡
አዲስ አበባ፡ ኢትዮጵያ