መስከረም ፲፯ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
++++++++++++
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የመስቀል በዓል በድምቀት እንዲከበር፣ በሰላም እንዲጠናቀቅ በየተሰጣቸው የሥራ ዘርፍ አስተዋጽኦ ያደረጉት አካላት በርካቶች መሆናቸውን አውስተዋል፡፡ ከሁሉም በቅድሚያ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ላደረገ እግዚአብሔር ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ የተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የጸጥታ አካላት አስፈላጊ
ውን ጥበቃና ክትትል በማድረግ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጀምሮ በከተማ አስተዳደሩ በተዋረድ በኃላፊነት ያሉ፤ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር መድረኩን ከማስዋብ ጀምሮ ለሠሩት በጎ ሥራ ምስጋናቸውን አቅርበው በአገልግሎት ዘርፍ ለተሰማሩት ሁሉ ለፖሊስ ባንድ፤ በዝማሬ፣ በውዳሴ በዓሉ ላይ መንፈሳዊ ትርዒት ላቀረቡ አገልጋዮች ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ለተለያዩ ማኅበራት፤ እንዲሁም ለተረኛው ደብር ለደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እና በበዓሉ ለተሳተፉ ለመላው ኦርቶዶክሳውያን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በዓሉ በተዋበና በደመቀ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ ዝናብና ቁር ሳይበግረው በጽናትና ፍጹም በሆነ መንፈሳዊነት በዓሉን ማክበሩ እጆግ የሚያስደንቅ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው መርሐ ግብሩ በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ መጠናቀቅ እንዲችል ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት ልጆቻችንና በበዓሉ ላይ ልዩልዩ መንፈሳዊ ትርኢት ስያቀርቡ የነበሩ በሙሉ ላሳዩት ጨዋነት የተሞላው መታዘዝ ቅድስት ቤተኮርስቲያናችን ልባዊ ምስጋናዋን ታቀርባለች። ብለዋል።
ሕዝበ ክርስቲያንኑ በዓሉ ወደ ሚከበርበት መስቀል አደባባይ በሚጓዝበት ወቅት ፍጹም ጨዋነትና መንፈሳዊነትን በተላበሰ መልኩ ለመንግስት የጸጥታ አካላት ትብብር በማድረግ፣ራሱም ጸጥታ አስከባሪና ተባባሪ በመሆን ያሳየው ድንቅ ትብብርም የሚደነቅ ነው ያሉት ብፁፅነታቸው በዓሉን ከሚያውኩ ተግባራት በማራቅም ቤተክርስቲያን ከበዓሉ አስቀድማ ያስተላለፈቻቸውን የጥንቃቄ መልዕክታት በሚገባ በመፈጸም ታዛዥነቱን በማስመስከሩ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተሰማትን ደስታ ትገልጻለች ብለዋል።
በሌላ በኩል በዓላችን ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ የፌዴራልና የክልል የደህንነት፣የአዲስ አበባ ከተማ ፓሊስ ኮሚሽን እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ እንዲሁም ሌሎች የጸጥታ አካላት ሙያዊ ግዴታችሁን በሚገባ በመወጣት ያደረጋችሁት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነውና ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ልባዊ ምስጋናዋን ስታቀርብላችሁ በከፍተኛ ደስታ ነው።
እግዚአብሔር አምላክም ሥራችሁን ሁሉ ይባርክ ካሉ በኋላ ማመስገን የሚገባንን ማመስገንም መንፈሳዊ ግዴታችን ነው ብለዋል።
ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምስጋናቸውን የገለጹት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በዓሉ እጅግ ደማቅ በሆነ መልኩ እንዲከበር የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማለትም የስቴጅ፣የክብር እንግዶች ወንበር፣አካባቢውን የማስዋብ ሥራና የድምጽ ማጉያዎችን ወጪ በመሸፈን እንዲሁም ለከተማ አስተዳደሩ ያቀረብናቸውን ጥያቄዎች ሁሉ በፍጥነትና በቅንነት ምላሽ በመስጠት ላደረገልን ትብብር እያመሰገንን በተለይም ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ቀልጣፋ አመራር በመስጠት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን ካሉ በኋላ ይህ አይነቱ መተጋገዝና የጋራ በሚያደርጉን ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የመስራቱ ልምዳችንም የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው መሆኑንም በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን ሲሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በዓሉ ባማረና በደመቀ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘትድ በጠቅላይ ቤተክህነትና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የተደራጁት ዐበይትና ንዑሳን ኮሚቴዎችም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ከፌዴራልና ከክልል የጸጥታ ተቋማት ጋር በጥምረት የሰራችሁት ስራዎች እጅግ ውጤታማና ስኬታማ በመሆናቸው እንኳን ደስ አላችሁ በሰራችሁት ውጤታማ ሥራም ቤተክርስቲያን ኮርታለች ሲሉ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓላችን በተዋበ፣
በተሳካና በደመቀ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ላደረጋችሁልን ተቋማት በሙሉ በተለይም በዓላችን ፍጹም መንፈሳዊ በዓል መሆኑን በዓለም መድረክ በማሳየት ደረጃ ዝናብና ቁር ሳይበግራችሁ በጽናት በመቆም በዓላችሁን በሚገባ ላከበራችሁ ኦርቶዶክሳዊያን ልጆቻችን በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን አደረሳች፤ በዓለ መስቀሉ የሰላም፣የደስታና የፍቅር በዓል ይሁንላችሁ በማለት አባታዊ መልዕክታቸውን አጠናቀዋል።©Eotc tv